በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሰኔ 3, 2014 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 3,000
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 16,477
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,324
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 19
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 102
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 20
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል አምስት ውጊያዎች ተመዝግበዋል። ሁሉም ውጊያዎች የተከሰቱት በጉጂ ዞን ነው። በዚህ ዞን በሁለቱ ወገኖች መካከል በጎራ አዶላ ወረዳ በሞርሞራ ቀበሌ፣ በአዶላ ወረዳ አቡሎ ቀበሌ፣ በዋደራ ወረዳ ዋደራ ከተማ እና በጉሚ ኢልዳሎ ወረዳ መልካ ጉባ ቀበሌ ውጊያዎች ተመዝግበዋል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉደቱ ቆንዳላ ወረዳ ሊቂጢ ቀበሌ በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዱን አስታውቋል። ስምንት የኦነግ ሸኔ አባላት የተገደሉብት እና 15 የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት መንደሩን ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣጡትን አስታውቋል (የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ሰኔ 3, 2014)። በርካታ የጦር መሳሪያዎችና የቡድኑ ንብረቶችም ተይዘዋል።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች የተሳተፉበት አንድ የውጊያ እና ሁለት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሁሉም ኩነቶች የተከሰቱት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነው። ግንቦት 29 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች በዞኑ ውስጥ ባልታወቀ ቦታ ከፌዴራል ፖሊስ ሃይሎች ጋር ተዋግተው የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። ውጊያው የተከሰተው የፋኖ ታጣቂዎች ቀደም ሲል ከአካባቢው የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው። በተመሳሳይ ቀን የፋኖ ታጣቂዎች በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሳሞ ኢላሙ፣ ሲዳቲ እና ጃሞ ዶባ በተባሉ አካባቢዎች ቁጥራቸው በውል የልታወቀ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ አርሶ አደሮችን ገድለዋል። ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተጎጂዎች በቅርቡ ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች ናቸው። ሰኔ 3 ቀን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ማካኖ ቀበሌ የፋኖ ታጣቂዎች ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ በነበሩ ሁለት ታዳጊዎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ታጣቂ ቡድኑ አንዱን ታዳጊ ገድሎ ሌላውን ካቆሰለ በኃላ ከብቶቻቸውን ወስዷል።
በክልሉ የመንግስት ሃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃትም ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ሸዋ ዞን በጮቢ ወረዳ የሎ ባካካ እና ቆሪቻ ጮቢ ቀበሌዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አርሶ አደሮችን ገድለዋል። በተመሳሳይ መልኩ በምዕራብ ሸዋ ዞን በባኮ ጥቤ ወረዳ አሁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አርሶ አደሮችን ገድለዋል።
በአማራ ክልል ሰኔ 3 ቀን በደሴ ከተማ ሚካኤል ጀርባ በሚገኘው ስልክ አምባ ትህምርት ቤት አካባቢ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ የተጣለ ከባድ መሳሪያ ፈንድቶ ሦስት ተማሪዎች ቆስለዋል (የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን፣ ሰኔ 3, 2014)።
በአማራ ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ግንቦት 27 ቀን የአፋር ብሔር ታጣቂ አባላት እና የአካባቢው የጸጥታ ሃይሎች መዋጋታቸውን ቀጥለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 27, 2014)። ሁለቱ ወገኖች ውጊያ የጀመሩት ግንቦት 25 ቀን በወረዳው ወርቁ አዲስ አካባቢ የአፋር ብሔር ታጣቂዎች በንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረስ በጀመሩበት ወቅት ነበር። ይህ የሆነው ግንቦት 23 ቀን አንድ የአፋር ብሔር ተወላጅ የሆነ ሰላማዊ ሰው በአርጎባ ልዩ ወረዳ ከሚገኘው መዲና ገበያ እየተመለሰ እያለ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው መገደሉን ተከትሎ ነው (የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ከግንቦት 20 እስከ 26, 2014 ይመልከቱ)።
ግንቦት 27 ቀን በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ በሶያማ ከተማ ገበያ የቡርጂ ብሔር ተወላጆች ከጉጂ ዞን የመጡ ዘጠኝ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ደብድበው የገደሉ ሲሆን ሌሎች 21 ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል። ተጎጂዎቹ ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሱሮ ባርጉዳህ ወረዳ ወደ አካባቢው እቃዎችን ለመግዛት እና ለመሸጥ የመጡ ናቸው። ይህ ጥቃት የተፈፀመው አንድ የቡርጂ ብሔር ተወላጅ ማንነቱ ባልታወቀ ቀበሌ ከጉጂ ዞን በመጡ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ተገድሏል የሚል ወሬ ከተናፈሰ በኋላ ነው። ነገር ግን እንደ አካባቢው ባለሥልጣናት ከሆነ ይህ ግለሰብ የተገደለው በኦነግ-ሸኔ ነው (ዲደብሊው አማርኛ ግንቦት 29, 2014)። ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 29 ቀን የቡርጂ ብሔር አባላት በሶያማ ከተማ በመሰባሰብ በሰላማዊ ኦሮሞዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ አውግዘዋል። በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ተቃውሞ በኦሮሞ ተማሪዎች ተካሂዷል።
በተጨማሪም በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሶስት ውጊያዋች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ባለፈው ሳምንት የኮሬ ብሔር ታጣቂዎች እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከደራሼ ብሔር ታጣቂዎች ጋር በደራሼ ልዩ ወረዳ ሆልቴ ቀበሌ እና በአማሮ ወረዳ ቡኒቲ፣ አቡሎ እና አልፋቾ ቀበሌዎች ላይ ተዋግተዋል። በእነዚህ ውጊያዋች የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ እና 15 ሰዋች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።
ባለፈው ሳምንት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ሊቀ መንበር በካማሺ ዞን ጉህዴን ረብሻ ለመፍጠር አሲሯል በሚል ታስረዋል። ግንቦት 24 ቀን የጉህዴን አባላት ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር በካማሺ ዞን ሚዥጋ ወረዳ ሶጌ ከተማ ውስጥ ተዋግተዋል። በማግስቱም በካማሺ ከተማ የክልሉ ልዩ ሃይል በጉህዴን ታጣቂዎች ተከበው ነበር (በእነዚህ ኩነቶች ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ከግንቦት 20 እስከ 26, 2014 ይመልከቱ)። የጉህዴን ፓርቲ ሊቀመንበር እና ዘጠኝ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 300 የፓርቲው አባላት ከግልገል በለስ ማረሚያ ቤት የተፈቱት በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። እነዚህ የፓርቲው አባላት የተፈቱት የካማሺ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ለውይይት ከተቀመጡ በኋላ ነው። እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት በዞኑ ያሉ የታጠቁ ሃይሎች ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ የታሰሩ አባላቶቻቸው እንዲፈቱ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበው ነበር። የጉህዴን አባላትም እጃቸውን ሰጥተው ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ተስማምተዋል። በመሆኑም በመጋቢት 10 ቀን የክልሉ መንግስት እና የጉህዴን የፖለቲካ እና የትጥቅ ክንፍ አመራሮች የሰላም እና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት በዞኑ አድርገው ነበር (ስለካማሺ ባህላዊ የሰላም እና ዕርቅ ሥነ ሥርዓት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 3, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014 ይመልከቱ)። ይሁን እንጂ ባህላዊውን የሰላምና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት ተከትሎ አንዳንድ የጉህዴን አባላት ትጥቅ አንፈታም በማለታቸው ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአካባቢው ውጥረት ነግሷል (ሪፖርተር፣ ግንቦት 28, 2014; ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 28, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል አንዳድ ቦታዎች ጦርነት መቀስቀስ
በጋምቤላ ክልል ሰኔ 2 ቀን በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 01 ኒውላንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጋምቤላ ነፃነት ግንባር /ጋነግ/ አባል በአካባቢው መደበቁ ጥቆማ ደርሷቸው አካባቢውን እየፈተሹ የነበሩ የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በትምህርት ቤቱ ተደብቆ ከነበረ ጋነግ አባል ጋር ተዋግቷል። በውጊያው አንድ የክልሉ ልዩ ሃይል አባል ቆስሏል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጋነግ የተሳተፈበት ሁለት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ጋምቤላ ከሌሎች ክልሎች አንፃር አንጻራዊ ሰላም ካላቸው ክልሎች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል። ባለፈው ሳምንት የክልሉ መንግስት ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ የክልሉን ሰላም ለማስቀጠል ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደረግ መግለጫ አውጥቶ ነበር። የክልሉ መንግስት ያወጣው መግለጫ ጋነግ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ላይ ስጋት መፍጠሩን አመላክቷል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አገልግሎት፤ ሰኔ 5, 2014፤ የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አገልግሎት፣ ሰኔ 4, 2014፤ የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አገልግሎት፣ ሰኔ 6, 2014)።
ሰኔ 7, 2014 ዓ.ም ጠዋት በጋምቤላ ከተማ እንዲሁም በምዕራብ ኦሮሚያ በጊምቢ እና ደምቢ ዶሎ ከተሞች ጦርነት ተቀስቅሷል። የኦሮሚያ እና የጋምቤላ ክልል መንግስታት እንደገለፁት ከሆነ ጥቃቱ በኦነግ-ሸኔ እና ጋነግ የተቀናጀ ነው። ማክሰኞ ምሽት (በኢትዮጵያ) ውጊያው ተጠናቋል። እንደ ኦነግ-ሸኔ – እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተብሎ የሚታወቀው – ቃል አቀባይ በጋምቤላ በተደረገው ዘመቻ ቡድኑ “በከተማው ውስጥ ያሉ የጦር መሳሪያዎች ማከማቻዎችን” በቁጥጥር ስር አውሏል (ትዊተር @ኦዳተርቢደብሊውቢኦአይ፣ ሰኔ 7, 2014)። የጋምቤላ ክልል መንግስት በከተማዋ የነበረው ጦርነት ጋብ ማለቱን እና የመንግስት ሃይሎች “ታጣቂውን ቡድን ለማጥፋት” እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቋል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት፣ ሰኔ 7, 2014)። በደምቢ ዶሎ እና ጊምቢ የተቀሰቀሰው ውጊያም በሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል በርካታ ሰአታትን ከፈጀ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ተጠናቅቋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 7, 2014)።
ይህ በቅርቡ የተደረገው ጦርነት ብዙዎች ያልጠበቁት ነው። በመጀመሪያ ጥቃቱ የተፈጸመው መንግስት ለሁለት ወራት የቆየ የኦነግ-ሸኔን አቅም ለመቀነስ ጥረት ካዳረገበትና አሳክቺያለው ካለው እንቅስቃሴ በኃላ ነው (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት-ኢትዮጵያ፣ ሰኔ 7, 2014)። እንደ ኦሮሚያ ክልል መንግስት ኦነግ-ሸኔ “ከእንግዲህ ብሔራዊ ስጋት” አልነበረም (ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 14 , 2014)። ሁለተኛ ከዚህ ቀደም ጋነግ በግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ አልነበረም በተጨማሪም የጋምቤላ ክልል በአጠቃላይ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት ክልል ነበር።
ይህ ጥረት ቢደረግም በቅርቡ በደምቢ ዶሎ፣ በጊምቢ እና በጋምቤላ የተከሰቱት ውጊያዎች ኦነግ-ሸኔ አሁንም ለመንግስት ከፍተኛ ስጋት እንደሆነ እና በቅርብ የተካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻዎች የቡድኑን አቅም መቀነስ እንዳልቻሉ ያረጋግጣል። በተጨማሪም ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በመካከላቸው ብዙ ስብሰባዎች እና የተቀናጁ ስልጠናዎች ቢደረጉም ይህ በቅርቡ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ሁለቱ ከተሞች የተካሄደው ዘመቻ በሁለቱ አማፂ ቡድኖች የተደረገ የመጀመሪያ ትልቁ “የጋራ” ዘመቻ ነው (ኦኤልኤ ኮሙኒኬ፤ ጥቅምት 21, 2014)።
ጋነግ ከ2013 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ በኋላ በመስከረም/ጥቅምት 2014 የተመሰረተ አዲስ ድርጅት ነው። ቡድኑ የምርጫውን “ህገ-ወጥ አሰራር እና ብልሹ አሰራር” በመጥቀስ በትጥቅ ትግል የጋምቤላ ክልል መንግስትን ለመጣል ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል (የኢትዮጵያ አውቶኖመስ ሚዲያ፣ ጥቅምት 21, 2014)። ቡድኑ ልክ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት እና የኮንፌደራሊስት ሃይሎች ህብረት ግንባር ፀረ-መንግስት አጋርነት ውስጥ እንዳሉት ‘የተከፋፈለ’ ድርጅታዊ ጉዳዮች አሉት። በዋሺንግተን ዲሲ የህብረቱ አባላት ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጋነግ ግንባሩን ወክሎ ስምምነቱን የፈረመው ተወካይ የጋነግ አባል እንኳን እንዳልነበረ የሚገልጽ ማስታወቂያ አውጥቷል (የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ሠራዊት ፣ ህዳር 7, 2014)። በዚህ ሳምንት በክልሉ ርዕሰ መዲና ላይ የተቀናጁ ጥቃቶች እነዚህ የመከፋፈል ጉዳዮች መፍትሄ ማግኘታቸውን ሊያመላክት ይችላል።
መንግሥት የድርድር ኮሚቴ በማቋቋም ከትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው በይፋ ቢገልጽም፣ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች ታጣቂ ድርጅቶች ጋር እንዲህ ዓይነት የድርድር ዕቅድ አልወጣም (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት-ኢትዮጵያ፣ ሰኔ 7, 2014)። ኦነግ-ሸኔ እና ጋነግ በሃገራዊ ምክክሩ ላይ እንዳይሳተፉ አልተከለከሉም። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ሂደቶች ግን እንደማይካተቱ ይጠቁማሉ። ይህ የቅርቡ ጥቃት ወደፊት በድርድር ጠረጴዛ ላይ ቦታ ለመያዝ እየሞከሩ መሆኑን ሊያመላክት ይችላል። ባለፈው ሳምንት የሃገራዊ ምክክሩ ኮሚሽን አባላት በጋምቤላ ነበሩ (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት፣ ሰኔ 3, 2022)። ሃገራዊ ምክክሩ እየተቃረበ እና ከትህነግ/ህወሓት ጋር ድርድር እየታቀደ ባለበት ወቅት መንግስት ለእነዚህ አነስተኛ ፀረ-መንግስት ድርጅቶች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።