በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሰኔ 24, 20141እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 3,068
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 17,245
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 7,794
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 18 እስከ 24, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 26
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 179
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 9
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውጥረት ተባብሷል። በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ሃይሎች – በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል፣ ፌዴራል ፖሊስ እና ቀበሌ ታጣቂዎች – መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ከኦነግ-ሸኔ ጋር በተያያዘ ከተመዘገቡት አብዛኛዎቹ ኩነቶች የተመዝገቡት በሰሜን ሸዋ ዞን ነው። በዚህ ዞን ስድስት የውጊያ ኩነቶች እና አራት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ኩነቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከሰኔ 19 እስከ 24 ድረስ ኦነግ-ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል እና ከቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በሃሙማ ጊንዶ (ራቾ/እሮብ ገበያ) ቀበሌ ተዋግቷል። በመጀመሪያው የውጊያ ቀን የአማፂ ቡድኑን ወታደራዊ አዛዥ ጨምሮ 13 ታጣቂዎች መገደላቸው ተነግሯል። ኦነግ-ሸኔ ወታደራዊ አዛዡ በአካባቢው ታጣቂዎች መገደሉን ካወቀ በኃላ በደራ ወረዳ ሀሙማ ጊንዶ፣ ግንዴ በርበሬ እና ባቡ ድሬ ቀበሌዎች በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። በዚህም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። በኦነግ-ሸኔ እና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ውስጥ በቀጠለው ጦርነት 33 ታጣቂዎችን እና ሁለት የቀበሌ ታጣቂዎችን ጨምሮ 35 ተዋጊዎች መሞታቸው ታውቋል። ሰኔ 23 ቀን ኦነግ-ሸኔ በሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ መዲሃኒ አለም ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይም ጥቃት ሰንዝሯል። ቡድኑ ቤቶችን አቃጥሏል ህፃናትንም አፍኖ ወስዷል። በዚህ ጥቃት የደረሰው ጉዳት አይታወቅም።
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ቢጤ ዳባ ቀበሌ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ቢላ ስዮ ወረዳ ቢሎ እና ጎቤ መንደሮች፣ በጉጂ ዞን ጉሚ ኢዳሎ ወረዳ መልካ ጉባ እና ቡልቡል ቀበሌዎች፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ ዳዋ ዲምቱ ቀበሌ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ ሃሮ ጎባ ቀበሌ፣ እና በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ተንዜ ቀበሌ ውጊያዎች ተመዝግበዋል። ኦነግ-ሸኔ በጉጂ ዞን ጉሚ ኢዳሎ ወረዳ በመልካ ጉባ እና ቡልቡል ቀበሌዎች በነበረው ውጊያ ከ20 በላይ የመንግስት ወታደሮችን መግደሉን ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት 45 የአማፂ ቡድኑን አባላት መግደሉን እና ሁለት ታጣቂዎችን ከበርካታ መሳሪያዎች ጋር መያዙን ተናግሯል።
ኦነግ-ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ውጪ በተከሰተ ኩነትም ተሳትፏል። ሰኔ 20 ቀን የኦነግ-ሽኔ እና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ መራ ቀበሌ የአማራ ባለሃብቶች ንብረት የሆኑ ሁለት የእርሻ ካምፖችን በመውረር 80 የቀን ሰራተኞችን አፍነው ወስደዋል። አማፂ ቡድኖቹ ሁለቱንም ካምፖች አቃጥለው የእርሻ መሳሪያዎችን አውድመዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ የሚታወቀውን የጋራ ዘመቻ በማካሄድ የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችውን ጋምቤላ ከተማን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተዋግተው ነበር (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 4 እስከ 10, 2014 ይመልከቱ)።
ኦነግ-ሸኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ከገደለበት የቶሌ ጭፍጨፋ በኃላ በሀገሪቱ ውሰጥ ውጥረት እየጨመረ መጥቷል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 11 እስከ 17, 2014ን ይመልከቱ)። ሰኔ 18 ቀን በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቶሌ የተከሰተውን የሰላማዊ ሰዎች ግድያ በማውገዝ በደብረ ማርቆስ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በተመሳሳይ ቀን ወደ 200 የሚጠጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በአዲስ አበባ በምዕራብ ኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ ተቃውሞ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ “ሞት ይበቃል” እና “አማራ እየሞተ የምትኖር ኢትዮጵያ የለችም” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ሰልፈኞች በአዲስ አበባ ከስድስት ኪሎ ወደ አምስት ኪሎ በሚወስደው መንገድ ላይ ድምፃቸውን እያሰሙ በሚጏዙበት ወቅት አምስት ኪሎ አካባቢ ሲደርሱ የፌዴራል ፖሊሶች መንገድ በመዝጋት ሰልፈኞችን በመደብደብ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ቢያንስ ሶስት ሰዎች ቆስለው የካቲት 12 ሆስፒታል ገብተዋል። በተመሳሳይ ሰኔ 20 ቀን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር “በምዕራብ ኦሮሚያ ኦነግ-ሸኔ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እና መንግስት ለዜጎች ጥበቃ አለማድረጉን” በማውገዝ በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞ አድርገዋል። የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተኮሰ ሲሆን ሰልፈኞችንም ደብድቧል። መንግስት እነዚህ እርምጃዎች የተወሰዱት “ሰልፎቹን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት ለመፍጠር የሚሞክሩ ሰርጎ ገቦችን” ለማስቆም ነው ብሏል። የመንግስት የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አንዳንድ ሚዲያዎች በሀገሪቱ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር የሃሰት መረጃ እያሰራጩ በመሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲጠነቀቁ ሲል መግለጫ አውጥቷል (የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሰኔ 20, 2014)። ነገር ግን ሰልፎቹ ቀጥለዋል። ሰኔ 23 ቀን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች በቶሌ ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፉ በሰላም ቢጠናቀቅም የጸጥታ ሃይሎች ሰልፉን አስተባብረዋል ያሏቸውን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። የከተማ አስተዳደሩ እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሰኔ 24 ቀን አንዳንድ ነዋሪዎች ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። በዚህ ሁከት ቢያንስ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 27, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2014).
በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር ሰኔ 21 ቀን ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ በቀበሌ 3፣ 11፣ 13 እና 14 አራት ፍንዳታዎች ደርሰዋል። እንደ ፖሊስ ገለፃ ፍንዳታዎቹን ፈጽመዋል የተባሉ ስድስት ሰዎች እንዲሁም ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 14 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ፖሊስ መኖሪያ ቤታቸውን ሲፈተሽ የተለያዩ መሳሪያዎችን፣ ቦምቦችን እና የመገናኛ መሳሪያዎችን ይዟል። ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ሰዎች “ህዝቡን እያሸበሩ ነው” ሲል ከሷቸው (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 21, 2014)። ሰኔ 23 ቀን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት “ለደህንነት ሲባል” በከተማዋ በሚገኙ ባጃጆች ላይ የምሽት ሰዓት እላፊ አውጇል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ፣ ሰኔ 23, 2014)።
በአማራ ክልል ሰኔ 22 ቀን በኦሮሚያ ልዩ ዞን በባቲ ከተማ አቅራቢያ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል፣ የክልሉ ፖሊስ እና የአካባቢው ታጣቂዎች ማንነታቸው ካልታወቀ ታጣቂ ቡድን ጋር ተዋግተዋል። ቢያንስ ሶስት የመንግስት ወታደሮች መገደላቸው ተዘግቧል።
በአዲስ አበባ ሰኔ 23 ቀን ሁከት ፈጣሪዎች በልደታ ክፍለ ከተማ ጦር ሃይሎች አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ላይ ድንጋይ በመወርወር የፅህፈት ቤቱን መስታወቶች ሰባብረዋል። ይህንን ድርጊት ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።
በመጨረሻም በአማራ ክልል የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች “የጠላት እንቅስቃሴ በመኖሩ” ምክንያት በተጠንቀቅ እንዲዘጋጁ የክልሉ መንግስት ጠይቋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 23, 2014)። ከግንቦት ጀምሮ በክልሉ ውስጥ መንግስት “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በመካሄድ ላይ ነው (ለበለጠ ዝርዝር ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 6 እስከ 12, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014ን ይመልከቱ)። በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ሃይሎች እና በመንግስት ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በርካታ ውጊያዎች ተመዝግበዋል። በተጨማሪም የትህነግ/ህወሓት መሪዎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስፈላጊ ከሆነ በአካባቢው የሚደርስ ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል (ትግራይ ቲቪ፣ ሰኔ 21, 2014፤ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ሰኔ 26, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት ነግሷል
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በሱዳን እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ውጥረት እንደገና ነግሷል። የቅርብ ጊዜው ውጥረት የተባባሰው የሱዳን መንግስት ሰባት የሱዳን መከላከያ ሠራዊት አባላትን እና አንድ ሰላማዊ ሰውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ገድሏል ሲል ከወነጀለ በኃላ ነበር (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 20, 2014)። ሰኔ 15 ቀን በአወዛጋቢው አል ፋሽጋ ክልል ውስጥ በአል ኩሬይሻ አካባቢ በሚገኘው ከአል አሲራ በስተምስራቅ በሚገኝ አካባቢ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት አባላት ማንነቱ ካልታወቀ የኢትዮጵያ ሃይል ጋር ከተዋጉ በኋላ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት አባላት መጥፋታቸው ተነግሮ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰኔ 20 ቀን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ግራር ውሃ (ገላል ውሃ) መንደር ላይ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ከባድ መሳሪያ ተኩሷል። በማግስቱ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት በሱዳን ድንበር ኢትዮጵያ በኩል በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ሶስት መድፍ ተኩሷል። አንዱ መድፍ በአብደራፊ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ወድቋል። ሰኔ 22 ቀን የሱዳን መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ድንበር ላይ ባልታወቁ ቦታዎች ሌላ ዙር የመድፎችን ተኩሷል። በዚህ ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የእርሻና የእርሻ ካምፖች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በእነዚህ መድፎች ምክንያት በሰዎች ላይ የደረሰ ምንም አይነት የተዘገበ ጉዳት የለም።
በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የአል ፋሽጋ ድንበር አካባቢ ለረጅም ጊዜ አከራካሪ ግዛት ሆኖ ቆይቷል። እ.ኤ.አ. በ2008 በትህነግ/ህወሓት እና በሱዳን ባለስልጣናት መካከል በተደረገው ድርድር “ፋሽጋ ትሪያንግል” ተብሎ የሚጠራውን መሬት በህጋዊ መንገድ የሱዳን አድርጎ የነበረ ሲሆን ከኢትዮጵያ የመጡ የአማራ ተወላጅ ገበሬዎች ድግሞ በአካባቢው በእርሻ ስራቸው እንዲቀጥሉ እንደሚፈቀድላቸው ገልጿል (አሻርክ አል-አውሳት፣ ሚያዚያ 4, 2012)። እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ በአካባቢው በየወቅቱ ውጊያዎች እና ጥቃቶች ይከሰቱ የነበረ ቢሆንም ይህ ስምምነት በጥቅምት 2013 ዓ.ም የሱዳን ወታደሮች በስፍራው ከተስማሩ በኃላ ፈርሷል። እነዚህ ሃይሎች በሰሜን ትግራይ ክልል ከትህነግ/ህወሓት ጋር በሚደረገው ጦርነት የፌዴራል መንግስትን ለመርዳት የአማራ ሃይሎች ከስፈራው ለቀው ወደ ሌላ ስፍራ ከተሰማሩ በኃላ ከአል ፋሽጋ ሰሜናዊ አካባቢዎች የአማራ ገበሬዎችን እና የትግራይ ገበሬዎችን በማባረር ተከሷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 12, 2014፤ ሰለ አል ፋሽጋ የድንበር አካባቢ ግጭት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦን የአል ፋሽጋ ድንበር ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።
በሱዳን እና በኢትዮጵያ ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ በአብዛኛው የፋኖ ታጣቂዎችን፣ የአካባቢው ታጣቂዎችን እና በአማራ ክልል ትዕዛዝ ስር ያሉ ልዩ ሃይሎችን ጨመሮ ከአማራ ክልል የተውጣጡ ኢ-መደበኛ እና መደበኛ የሆኑ ታጣቂዎችን ያካትታል። በጣም አስፈላጊው ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱት ውጊያዎች ድንበርን ለማስፋፋት በሚፈልጉ በአማራ ብሔርተኞች እና በፌዴራል መንግስት መካከል ከፍተኛ አለመግባባት በተፈጠረበት ወቅት ነው። በግንቦት ወር ላይ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሰር እንደ ፋኖ ባሉ የአማራ ብሄርተኛ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል (ሮይተርስ፣ ግንቦት 15, 2014)። በጥቅምት 2013 ዓ,ም ከትህነግ/ህወሓት ጋር በነበረው ግጭት እነዚህ የብሄርተኛ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር የተሰለፉ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው የአሰላለፍ ለውጥ ምክንያት ግን እንደ ሱዳን ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ላይ መጠነኛ ለውጥ ሊኖረው ይችላል። መንግስት እነዚህን ወገኖች በቀጣይ ውይይት ካላሳተፈ ወይም ጥያቄዎቻቸውን ከሱዳን ጋር በሚደረግ የሁለትዮሽ ውይይት ላይ ካላነሳ ግን በርግጠኝነት ግጭቱ የበለጠ ሊባባስ ይችላል። ሰኔ 28 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ከጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር “በወቅታዊ ክልላዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች” ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት-ኢትዮጵያ ፣ ሰኔ 28, 2014)
በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን የተከሰቱት ክስተቶች ሁኔታውን ይበልጥ የተወሳሰበ ያደርገውታል። በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች መንግስት ሱዳንን በመሸሸግ የሚወነጅላት በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ ተፈጽሟል። በቅርቡ የተፈፀመው ግድያ ከሱዳን ድንበር 150 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ ነው (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2014)። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ቡድኖች እና ከትህነግ/ህወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በሱዳን ድንበር በኩል ወረራ እንደሚፈፅሙ መንግስት በየጊዜው ሪፖርት ያደርጋል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በአብዛኛው በያዝነው አመት የካቲት ወር ላይ ኤሌክትሪክ ማምረት የጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው (አልጀዚራ፣ የካቲት 13, 2013)። በያዝነው የዝናብ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን ለሶስተኛ ዙር ለመሙላት ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ሁለቱም ሱዳን እና ግብፅ የኢትዮጵያ መንግስትን ብቻውን እየሰራ ነው ሲሉ ተቃውመውታል። ዲፕሎማሲው በሂደት ላይ ቢሆንም መንግስታዊ ያልሆኑ ሃይሎች እና ሌሎች ውጫዊ ጉዳዮች መኖራቸው ንግግሮችን የሚያወሳስቡ ሲሆን ውጥረቱንም የበለጠ እንዳይጨምር ያሰጋል።