በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 1, 20141እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,076
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 17,494
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 7,966
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 25 እስከ ሐምሌ 1, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 6
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 165
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 162
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ነገር ግን በክልሉ ምንም አይነት ውጊያዎች አልተዘገቡም። ሰኔ 27 ቀን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ-ሸኔ) በቄለም ወለጋ ዞን በሃዋ ገላን ወረዳ ለምለም ቀበሌ መንደር 20 ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ቢያንስ 150 አብዛኞቹ የአማራ ተወላጆች የሆኑ ሰዎችን ገድሎ ከ45 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ አቁስሏል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ቡድኑ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን አግቶ በመውሰድ የነዋሪዎችን ንብረት ዘርፏል። አማፂ ቡድኑ ይህን ክስ ውድቅ ያደረገ ሲሆን የአካባቢው የመንግስት ሚሊሻዎች ጥቃቱን ፈጽመዋል ሲል ከሷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2014)። በማግስቱ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ዳኖ ቱልቶ ቀበሌ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ሦስት አርሶ አደሮችን ገድለው ሁለት አርሶ አደሮችን ደግሞ ማቁስላቸው ተነግሯል። የታጠቀው ቡድን ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ የቀንድ ከብቶችንም ዘርፏል። አማፂ ቡድኑ ጥቃቱን ያደረሰው ኦነግ-ሸኔ ነው የሚለውን ውንጀላ አስተባብሏል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 29, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተሳተፉበት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት ሃይሎች በቄለም ወለጋ ዞን ሰዲ ጨንቃ ወረዳ በጫንቃ ቀበሌ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላትን ተኩሰው ገድለዋል። ጉዳት የደረሰባቸው አካላት “በኦነግ-ሸኔ ላይ በሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ከመንግስት ሃይሎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆን” ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው (ኦኤምኤን፣ ሰኔ 30, 2014)። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሆኑ የሚገመት የጸጥታ ሃይሎች በምዕራብ ወለጋ ዞን በዩብዶ ወረዳ ዩብዶ ከተማ እና አይራ ወረዳ አይራ ከተማ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት የመንግስት ሰራተኞችን እና የቀበሌ ታጣቂዎችን ተኩሰው ገድለዋል። በተጨማሪም በምዕራብ ወለጋ ዞን ኖሌ ካባ ወረዳ ሰሜሮ በተባለ ቦታ እንደገና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት ሃይሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎችን ባልታወቀ ምክንያት ተኩሰው ገድለዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት – ሁለተኛ ግድያ የፖለቲካዊ ምላሽ ማስከተል
በኦሮሚያ ክልል በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ያደረሰውን ከፍተኛ ሞት ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰኔ 29 ቀን ብዙ ባልተለመደ መልኩ ዝግ ስብሰባ ማድረጋቸው ተዘግቧል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሰኔ 29, 2014)። በተመሳሳይ ቀን በጥቃቱ የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት እጃቸው አለበት የሚባለውን በመጥቀስ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮች ምዕራብ ኦሮሚያ በፌዴራል መንግስት አስተዳደር ስር እንዲሆን ጠይቀዋል (ቢቢሲ አማርኛ፤ ሰኔ 29, 2014)። ባለፈው ሳምንት በቄለም ወለጋ ዞን ለምለም ቀበሌ ከ150 በላይ የሚሆኑ በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች በሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት የደረሰው በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11 ቀን በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት በትንሹ 338 በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። ሁለቱም ጥቃቶች ኦነግ-ሸኔ እንደፈፀማቸው ቢነገሩም ቡድኑ ይህን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው ልዩ ስብሰባው ስድስት ነጥቦችን የያዘ የውሳኔ ሐሳብ ያስተላለፈ ሲሆን አብዛኞች ባንዲራ ዝቅ ብሎ የሃዘን ቀን እዲታወጅ የጠየቁትን በመተው “በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች” ለአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲደረግ ወስኗል።የተላለፉት ስድስት ነጥቦቹ የተከሰቱትን ጥቃቶች አጣርቶ ለፓርላማ መረጃ ለማቅረብ ኃላፊነት የተሰጠው ልዩ ኮሚቴ እንዲቋቋም እና ሌሎች ነጥቦችን ያካተቱ ናቸው (የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ሰኔ 29, 2014)።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ በአማራ ክልል ከተቀሰቀሰው ሰልፎች በተቃራኒ ባለፈው ሳምንት ምንም አይነት ህዝባዊ ተቃውሞ አልተደረገም። የቶሌውን እልቂት ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች ሰልፎች እንዳይካሄዱ ለማፈን የተለያዩ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ ጥረት ግጭቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። በሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋ ሮቢት ከተማ የተደረገውን የቶሌ ጭፍጨፋን የሚያወግዝ ሰልፍ አስተባብረዋል በሚል የታሰሩት ሰዎች እንዲፈቱ በጠየቁ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እና በፀጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሰኔ 18 ቀን ያደረጉትን ተቃውሞ ተከትሎ በአዲስ አበባም የተቃውሞ ሰልፈኞች በሀይል እንዲበተኑ መደረጉም ተዘግቧል (ቦርከና፣ ሰኔ 19, 2014)።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዳይሬክተር በቄለም ወለጋ ለተፈፀመው ጭፍጨፋ ምላሽ ለመስጠት ሰኔ 27 ቀን በሰጡት መግለጫ “በአካባቢው እየቀጠለ ያለው የፀጥታ ችግር እና በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ብሔር ተኮር ግድያ በአስቸኳይ መቆም አለበት” ብለዋል (ኢሰመኮ፣ ሰኔ 27, 2014)።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ሶስት ሳምንታት በኦሮሚያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለተፈፀመው ለሁለቱም ግድያዎች ተጠያቂ የሆነውን ኦነግ-ሸኔ ለማሸነፍ ቃል ገብተዋል (ቪኦኤ፣ ሰኔ 30, 2014)። አብይ በፓርላማ “ሽብርተኝነት” እና የሰሜን አሜሪካ ውስጥ ያለውን የጦር መሳሪያ ጥቃትን አሁን ካለው ኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማነፃፀሩ አሁን ላለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች ግድ የለሽነቱን አሳይቷል በሚል ይህ ንግግሩ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ቁጣን አምጥቷል (ቦርከና፣ ሰኔ 30, 2014)። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በኦነግ-ሸኔ የተፈፀመውን ጥቃት በ“አሸባሪነት” የፈርውጁ ሲሆን በመላው አለም “ሽብርተኝነትን” ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ያለውን ተግዳሮቶች ለማሳየት በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ያለውን የጠመንጃ ጥቃት፣ በሶማሊያ የሚገኘው አልሸባብን፣ በናይጄሪያ ያለውን ቦኮ ሃራምን እና በየመን ያሉ የሃውቲ አማፂያን እንደ ምሳሌ አንስተዋል (ኢቢሲ፣ ሰኔ 30, 2014)።
ከሰሞኑ በሕዝብ ዘንድ ከታዩት ወሳኝ የህዝብ ድምፆች አንዱ የአማራ ማህበር በአሜሪካ ሲሆን ከቶሌ ጭፍጨፋ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቋል (ኤኤኤ፣ ሰኔ 13, 2014)። ማህበሩ በቄለም ወለጋ ዞን በተከሰተው ግድያ ላይ ዝርዝር መረጃ ከሰጡ አካላት መካከል አንዱ ሲሆን በዜና አውታሮች እና በማህበራዊ ሚዲያዎች መንግስትን በመተቸት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል (ኤኤኤ፣ ሐምሌ 3, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በገዢው ብልፅግና ፓርቲ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ጫና ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት መንግስት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ቢችልም፣ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ከቀጠለ ግን እንደገና ተቃውሞና የሁከት እንቅስቃሴ የመፈጠር እድሉ ከፍተኛ ነው።