በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 15, 20141እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,154
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 17,950
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 8,038
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ሐምሌ 9-15, 2014 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 22
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 74
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 24
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። አክሌድ በሰሜን ሸዋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ፊንፊኔ ልዩ ዞኖች በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ዘጠኝ የውጊያ ኩነቶችን መዝግቧል። ከሐምሌ 12 እስከ 14 በጉጂ ዞን በጎራ ዶላ ወረዳ አዳዲ እና ቄሬሮ ቀበሌዎች ሁለቱ ወገኞች ተዋግተዋል።
ባለፈው ሳምንት በክልሉ አስር በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከሐምሌ 10 እስከ 12 ኦነግ-ሸኔ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ገድሏል እንዲሁም አፍኖ ወስዷል። በተጨማሪም ስድስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ላይ የመንግስት ኃይሎች እጃቸው እንዳለበት ተመላክቷል። በምዕራብ አርሲ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች ከ12 በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል የተወሰኑት ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም ቡድኑን ይደግፋሉ ተብለው የተከሰሱ ሲሆን ሌሎቹ የተገደሉበት ምክንያት ግን ምን እንደሆነ አልታወቅም። በተጨማሪም ሐምሌ 11 ቀን ከሶማሌ ክልል የመጡ የሶማሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች በባሌ ዞን በጉራዳሞሌ ወረዳ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው የወረዳው ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ሽሮ እና ጄሎ ቀበሌዎች ላይ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ቢያንስ ሁለት ሰላማዊ ሰዎች ሲሞቱ አምስት ደግሞ ቆስለዋል። ቡድኑ የአካባቢው ገበሬዎችን ከብቶች እየናዳ ወስዷል።
በመጨረሻም የፌዴራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተለያዩ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሰጥቷል። ግብረ ሃይሉ 174 የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) አባላት፣ 98 የኦነግ-ሸኔ አባላት፣ 51 የፋኖ አባላት እና 100 ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውስጥ ያልተገለጸ ቦታ ላይ ጥቃት ለመፈጸም አቅደዋል በማለት 454 ሰዎችን የፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቋል። በተጨማሪም መንግስት በአዲስ አበባ እና አካባቢው ጥቃት ለመፈጸም አቅደዋል ያላቸውን 31 የአልሸባብ እና የእስላማዊ መንግስት (አይኤስ) አባላት በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ተናግሯል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሐምሌ 16, 2014)። በተጨማሪም የጋራ ግብረ ሃይሉ ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 7 በኦሮሚያ ክልል ጊምቢ ወረዳ በኦነግ-ሸኔ ላይ የፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል የተቀናጀ ወታደራዊ ጥቃት መፈፀማቸውን እና ከ153 በላይ የአማፂው ቡድኑን አባላት መግደላቸውን እንዲሁም ከ900 በላይ አባላት መማረካቸውን ገልጿል (የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሐምሌ 16, 2014)። ሰኔ 11 ቀን ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በጉቱ፣ ጨርቆሳ፣ ስልሳው፣ በገነ፣ ጫካው ሰፈር እና ሀያው አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከ338 ያላነሱ በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች የሆኑ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 11 እስከ 17, 2014 ይመልከቱ)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የአልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ መግባት
ባለፈው ሳምንት አልሸባብ እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በሶማሌ እና በኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ ከሚገኙት ዮድ እና አቶ አካባቢዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሃርጌሌ ወረዳ ለቀናት የዘለቀ ውጊያ አድርገዋል። ሐምሌ 15 ቀን በሃርጌሌ ወረዳ ሁሉሁል ውስጥ በሆልሂር በተባለው አካባቢ የክልሉ ልዩ ሃይል የአልሸባብ ታጣቂዎችን በመክበብ ቡድኑን “እንዳወደመ” ተነግሯል (የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ ሐምሌ 16, 2014)። በእነዚህ ውጊያዎች ሶስት ሰላማዊ ሰዎችን እና የኢትዮጵያ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 17 ሰዎች እንዲሁም ከ100 በላይ የአልሸባብ አባላት መሞታቸው ተዘግቧል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሐምሌ 20, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 19, 2014፤ ሮይተርስ፣ ሐምሌ 15, 2014)። እነዚህ ክስተቶች ከሳምንት በፊት ሐምሌ 7 ቀን በአፍዴር ዞን በኤልከሬ-ሴረር ወረዳ ቡላ ተራራ አካባቢ በክልሉ ልዩ ሃይል እና ወደ 60 በሚጠጉ የአልሸባብ አባላት መካከል የነበረውን ውጊያ ተከትሎ የአልሸባብ አዛዥ መገደሉን ተከትሎ ነው። ከቀናት በኋላ የፌዴራል መንግስት በርካታ የአልሸባብ ታጣቂዎች በአዲስ አበባ ጥቃት ለመፈጸም አቅደዋል በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ አልሸባብ ከሚንቀሳቀስባት ከሶማሊያ ጋር ረጅም ድንበር ቢኖራትም በኢትዮጵያ በአልሸባብ የሚሰነዘር ጥቃት ያልተለመደ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በአብዛኛው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በመኖሩ ነው (ስለዚህ ኃይል የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘው የኢፒኦን የኢትዮጵያ ፖሊስ ሃይል (2010) የልዩ ፖሊስ እና የፖሊስ ሃይል ኢትዮጵያ (2010) የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ማብራሪያ ገፆችን ይመልከቱ)። እንዲሁም ይህ ልዩ ኃይል በሶማሊያ ውስጥ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (ኤቲኤምአይኤስ) አካል ሆነው ተሰማርተዋል (ሎንግ ዋር ጆርናል፣ ሐምሌ 18, 2014)። ምንም እንኳን በዚህ ስምሪት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች ውጤታማ ቢሆኑም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ከባድ የሰብአዊ መብት ረገጣ አድርገዋል ተብለው ይወነጀላሉ (ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ነሃሴ 14, 2010)። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮችም በሶማሊያ የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ የተከሰተውን ውጊያ ተከትሎ ተጨማሪ የሠራዊቱ አባላት ወደ ድንበር አካባቢ ተሰማርተዋል።
የኢትዮጵያ ኃይሎች በሶማሊያ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሲሆን እ.ኤ.አ በ2006 በአሜሪካ የተደገፈውን ዩኒየን ኦፍ ኢስላሚክ ኮርት የተባለውን ቡድን ለመጣል የሚደገረውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የኢትዮጵያ ኃይሎች ወደ ሶማሊያ ከገቡ በኃላ በሶማሊያ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በሶማሊያ ያሉት የኢትዮጵያ ኃይሎች አቅም ከሶማሊያ ብሔራዊ ጦር (ኤስኤንኤ) ወይም የፖሊስ ኃይሎች ይበልጣሉ ተብሎ ይታሰባል (ብሩኪንግስ፣ ህዳር 10, 2012)። በ2012 ከትህነግ/ህወሓት ጋር የተፈጠረውን ውጊያ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸው አልሸባብ እንዲስፋፋ የሚያደርገውን “የደህንነት ክፍተት” እንዳይፈጥር ስጋት አስነስቷል (ብሎምበርግ፣ ህዳር 3, 2012)። ይህም የኢትዮጵያ ኃይሎች በሶማሊያ አልሸባብን ለመዋጋት ያላቸውን ትልቅ ሚና አጉልቶ ያሳያል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የአልሸባብ ታጣቂዎች የተሳተፉበት ኩነቶች እጅግ በጣም ጥቂት በመሆኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ ውስጥ በአልሸባብ የደረሰው የፖለቲካ ጥቃት አዲስ ደረጃ መድረሱን የሚያመለክት ነው። ምናልባትም ቀደም ሲል ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንደ የሀገሪቱን ምስራቃዊ ድንበር ያሉ አንዳንድ ጉዳዮች ወደ ኃላ ተትው እና የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል እንዲሰፍሩ በመደረጉ ሀገሪቱን ለአልሸባብ ጥቃቶች አጋልጧል። ቡድኑ በኢትዮጵያ ያደረገው ወረራ ግን የተለያየ ውጤት አስመዝግቧል። የሰሞኑ የአልሸባብ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሁኔታ እና የኢትዮጵያ ኃይሎች በሌሎች የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በመጠመዳቸው እንደዚህ ያሉ ድንበር ዘለል ጥቃቶች በአገሪቱ ወደፊት ሊጨምሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
ሆኖም የአልሸባብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ለመንግስት የውስጥ እና የውጪ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታት ባለመቻሉ የውስጥ ጫና እየገጠመው በመሆኑ የህዝብን ድጋፍ ወደ እራሱ የሚመልስበት መንገድ ያስፈልገዋል። የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የአልሸባብን ወረራ ማሸነፍ የሌላ ክልል ልዩ ኃይሎች ከዚህ በፊት በተገቢው ሁኔታ ሊያደርጉት ያልቻሉትን ታጣቂ ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ ያለውን ውጤታማነት ያሳያል። በሶማሌ ክልል መንግስት ባለፈው ሳምንት የተለቀቀው መግለጫ ውጊያውን ከአልሸባብ እና ከሌሎች የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታዎች ጋር ለማገናኘት ሙከራ ማድረጉ የህዝብ ድጋፍን ለማግኘት ይመስላል። በዚህ መግለጫ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት የአልሸባብ ታጣቂዎች “ክልሉን የሚያዋስነው ኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን ኦነግ-ሸኔን ለመቀላቀል” ነበር ሲሉ መናገራቸው ሁለቱ ቡድኖች ሙሉ በሙሉ የተለያየ ዓላማ ያላቸው እና በጋራ የመንቀሳቀስ ታሪክ የሌላቸው በመሆኑ አስገራሚ አድርጎታል (የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ ሐምሌ 16, 2014)።
በአለም አቀፍ ደረጃ፣ እንደ አዲስ ያገረሸው የአልሸባብ ስጋት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በሶማሊያ የሚገኙ አክራሪ እስላማዊ ቡድኖችን ለመዋጋት አለም አቀፍ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ኃይሎች መደገፉን አጉልቶ ያሳያል። የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ እና በኦሮሚያ በወታደሮቹ የሚፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ረገጣ ዘገባዎች እንዲፈታ ግፊት እያደረሰበት ባለበት በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብን ለመዋጋት እያደረገ ያለውን ታሪካዊ አስተዋፅኦ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳሰብ ሳያስፈልገው አይቀርም። ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የአልሸባብን ጥቃት ለመከላከል ያለውን ሚና ለማሳየት እድል ሰጥቶታል።
ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በአልሸባብ እያንሰራራ ያለው የፖለቲካ ጥቃት አሳሳቢ ነው። ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ተቀባይነት ወደ ሚያገኝበት ክልል የተስፋፋ ያለበትን አዝማሚያ ያሳያል። ይህ ስጋት እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ አልሸባብ መሸነፉን የሚገልጹ ሪፖርቶች የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ያላቸውን አቅም እና በምስራቃዊ ድንበር ላይ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ያላቸውን ብቃት ያሳያል ይህም በመላ ሀገሪቱ ለመንግስት የሚፈለገውን ድጋፍ ከፍ ሊያደርግ ይችላል።