በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 22, 20141 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,167
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 18,062
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,059
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ሐምሌ 16-22, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 13
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 112
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 21
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት አክሌድ በክልሉ ውስጥ 10 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን መዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የተዘገቡት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በሙሉ የተፈፀሙት በመንግስት ሃይሎች ማለትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌ እና ከአማራ ክልሎች በመጡ ልዩ ሃይሎች ነው። እነዚህ ኩነቶች የተመዘገቡት በአርሲ፣ በባሌ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በምዕራብ ሀረርጌ እና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 20 የሚጠጉ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት አልፏል።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በ2010 ተሃድሶ ካደረገ በኃላ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እምብዛም ሲሳተፍ አይታይም። ሐምሌ 21 ቀን በባሌ ዞን በጉራዳሞሌ ወረዳ በሃብሮና ቀበሌ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ባልታወቀ ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸው እና ነዋሪዎችም ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል። ከሳምንት በፊት ሐምሌ 11 ቀን ከሶማሌ ክልል የመጡ የሶማሌ ብሔር ታጣቂዎች በጉራዳሞሌ ወረዳ በኦሮሞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው ሽሽተው ነበር።
በመጨረሻም ሐምሌ 18 ቀን የታክሲ እና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና ደጋፊዎቻቸው በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ እየጨመረ የመጣውን የጸጥታ ችግር እና የጸጥታ ችግርን ለመቅረፍ የመንግስት ምላሽ አለመኖሩን አውግዘዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የአልሸባብ ጥቃት ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሏል
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንዲሁም በሶማሊያ ድንበር በሚገኙ አካባቢዎች በኢትዮጵያ ኃይሎች እና በአልሸባብ መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ቀጥለዋል (አልሸባብ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሰለተሳተፈባቸው ኩነቶች የበለጠ ዝርዝር ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 9-15, 2014 ይመልከቱ)። ሐምሌ 18 ቀን የአልሸባብ ታጣቂዎች ከአጎራባች ሶማሌ ሂራን ክልል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክሩ በሶማሌ ክልል በሸበሌ ዞን ፈርፈር ወረዳ አል ቁዱን በተባለው አካባቢ ቡድኑ ከሶማሊያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ተዋግቷል። ሰማንያ አምስት የአልሸባብ አባላት መገደላቸውን እና በርካታ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውም ተነግሯል። በተጨማሪም ሐምሌ 22 ቀን በሶማሊያ በባኮል ክልል በአቶ ከተማ አልሸባብ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ላይ በበርካታ ሞርታር፣ አርፒጅኤስ (RPGs) እና ሶስት የመኪና ቦምቦችን በመጠቀም ጥቃት ሰንዝሯል። ቡድኑ በዚሁ አካባቢ ከክልሉ ልዩ ሃይል እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተዋግቷል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአቶ ከተማ አካባቢ በሚገኙ የአልሸባብ ካምፖች ላይ ያነጣጠረ የአየር ድብደባ አድርጓል። የኢትዮጵያ መንግስት በእነዚህ ውጊያዎች እና የአየር ጥቃቶች ምክንያት የቡድኑ መሪዎችን ጨምሮ ወደ 150 የሚጠጉ የአልሸባብ አባላት መገደላቸውን ተናግሯል (ኢኤምኤስ፣ ሐምሌ 22, 2014፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 22, 2014)። ይህ በእንዲህ እንዳለ አልሸባብ 103 የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላትን መግደሉን ተናግሯል (አናዶሉ ኤጀንሲ፣ ሐምሌ 22, 2014)። ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ውጊያው እና የአየር ድብደባው በሳምንቱ መጨረሻም ቀጥሏል (አናዳሉ ኤጀንሲ፣ ሐምሌ 23, 2014፤ ኢኤምኤስ፣ ሐምሌ 24, 2014)።
ጦርነቱ የድንበር ከተሞችን አቶ፣ ይድ፣ ኤል ባርዴ፣ ዋቃሾ እና ፈርፈርን ጨምሮ በአምስት ዋና ዋና ቦታዎች ላይ ያተኮረ ነው (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሐምሌ 19, 2014)። በሶማሌ ክልል ቀላፎ ድንበር አካባቢ የአልሸባብ አባላት መታየታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶችም ነበሩ (ኢኤምኤስ፣ ሐምሌ 22, 2014)። እስካሁን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በአልሸባብ ታጣቂዎች የተደረገውን የወረራ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማክሸፍ የቻለ ይመስላል። የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ – ብዙ ጊዜ በአማርኛ ስሙ “ልዩ ሃይል” እየተባለ የሚጠራው –ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋር በነበረ ግጭት ወቅት ፀረ-ሽምቅ ሃይል ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን የልዩ ኃይሉ አባላትም እነዚህን አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለመቋቋም የሰለጠኑ ናችው። ኦብነግ በ2010 ትጥቅ ፈትቶ እንደ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተቋቁሟል። ቡድኑ በአልሸባብ የተደረገውን የወረራ ሙከራ በማውገዝ በትዊተር መግለጫ አውጥቷል (ኦብነግ፣ ሐምሌ 14, 2014)።
ቢያንስ አንድ የመረጃ ምንጭ የአሜሪካን ግምገማ ጠቅሶ እንደዘገበው ታጣቂው ቡድን ከመቆሙ በፊት እስከ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ግብቶ ነበር። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጦር የአልሸባብን ጥቃት አስቀድሞ ለማስቆም እንዲቻለው በሶማሊያ ውስጥ ነፃ ቀጠና እንደሚያዋቅር አስታውቀዋል። የሶማሊያ ባለስልጣናት ሃሳቡን በደስታ ሲቀበሉት ተንታኞች ግን በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ወደፊት ስለሚኖረው ግንኙነት አንድምታ እና ይህ ሃሳብ የተነሳበትን ወቅት ጥያቄ አቅርበዋል (ቪኦኤ፣ ሐምሌ 22, 2014)።
አልሸባብ እና ኢስላሚክ ስቴት (አይ ኤስ) ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ ላይ እየጨመረ የመጣውን ፍላጎታቸውን ያሳዩ ሲሆን የምልመላ ቪዲዮዎችን በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ለቀዋል (ሚሊታንት ዋየር፣ ሐምሌ 23, 2014)። በቅርቡ ጥቃቱን የከፈተው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን “የኢትዮጵያ ሙጃሂዲን” በመባል የሚታወቅ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 19, 2014)። ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ በአካባቢው የተወሰነ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን የአይኤስ አጋር አካላትን የሚያሳትፍ እንቅስቃሴ አንዳንድ ጊዜ ይነገራል ሆኖም ቡድኑ ከአይኤስ ጋር ያለው ግንኙነት ግልፅ አይደለም። የመጨረሻው የአይኤስ አጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ የፖለቲካ ጥቃት እንቅስቃሴ በጥር 2013 በባሌ ዞን የተፈፀመውን ቀለል ያሉ ውጊያዎችን ያካትታል (ሺንዋ፣ ጥር 17, 2013)።
የማስተካከያ ማስታወሻ፡- ቀደም ሲል ታትሞ የወጣው የዚህ ዘገባ ቅጂ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በኦሮሚያ ክልል ብዙም ተሳትፎ እንደሌለው ገልጿል። ይህ ዓረፍተ ነገር የተስተካከለ ሲሆን የአሁኑ ቅጂ ልዩ ኃይሉ በ2010 ካደረገው ተሐድሶ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እምብዛም ተሳትፎ እንደሌለው ይገልጻል።