በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 29, 20141እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,195
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 18,479
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,103
ቁጥር: ኢትዮጵያ, ሐምሌ 23-29, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 21
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 68
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 44
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትና ውጊያ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መካከል ስምንት የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል። እነዚህ ውጊያዎች በምዕራብ ሸዋ፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና አርሲ ዞኖች የተከሰቱ ሲሆን አብዛኞቹ ውጊያዎች የተከሰቱት በምዕራብ ሸዋ ዞን ነው።
ባለፈው ሳምንት አክሌድ በኦሮሚያ 11 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶችን መዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በመንግስት ኃይሎች ማለትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ነው። እነዚህ ኩነቶች የተከሰቱት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ፊንፊኔ ልዩ፣ ምስራቅ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ሲሆን በአጠቃላይ ከሃያ ሁለት በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ታውቋል። አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም ይደግፋሉ በሚል ተከሰዋል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ጫቂ መንደር የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎች ገብተው ሦስት ሰዎችን ገድለዋል። ሁለቱ ቡድኖች የግል ንብረቶችንም ዘርፈዋል።
በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ኃይሎች በደራሼ ልዩ ወረዳ አጣዬ ቀበሌ ስምንት ሰዎችን መግደላቸው ታውቋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ግን የጸጥታ ኃይሎች ማንነታቸው ካልታወቀ ታጣቂ ቡድን ጋር የተኩስ ልውውጥ በማድረግ አራት ታጣቂዎችን ገድለው ወደ 20 የሚጠጉ ሌሎች ሰዎችን አመፅ በማነሳሳት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሰር መደረጋቸውን ተናግረዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 26, 2014)። የደራሼ ልዩ ወረዳ ከአጎራባች የኮንሶ ዞን አስተዳደር ጋር ተያይዞ በተነሳ ግጭት ከሚያዝያ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተደጋጋሚ የፖለቲካ አለመረጋጋት የታየበት ሲሆን የአካባቢ ምክር ቤት አባላትም በቅርቡ በአዲስ ክልላዊ መንግስት መዋቀር ለመካተት ድምጽ ሰጥተዋል (አዲስ ስታንዳርድ ሐምሌ 26, 2014)።
በመጨረሻም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በሚገኘው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ኦሮሞ ያልሆኑ ተማሪዎች የኦሮሞ ተወላጆችን መደብደባቸው ተነግሯል።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ተወላጅ መሪዎች መካከል ያለውን ድርድር አለመግባባት ማዘግየቱ
በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር እንደገና የሚጏተትበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ድርድር የሚጀምርበት ወሳኝ ወቅት ዘግይቷል። ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ደኅንነት (ፒኤፒኤስ) በተፋላሚ ወገኖች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ኃላፊነት ያለው የአፍሪካ ኅብረት ቡድን አካል እንዲሆኑ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ለማካተት ስምምነት ላይ ደርሷል (ሪፖርተር፣ ሐምሌ 30, 2014)። አዲስ ስታንዳርድ ባሳተመው ጽሁፍ መሰረት ይህ ስምምነት ትህነግ/ህወሓት በኬንያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በአለም አቀፍ አጋሮች ድርድሩ በኬንያ እንዲካሄድ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሐምሌ 27, 2014)። የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ልዩ ልዑካን በመንግስት እና በትህነግ/ህወሓት መካከል “ውይይት እንዲጀመር ለማበረታታት” ባለፈው ሳምንት በመቀሌ የጋራ ጉብኝት አድርገዋል (የአሜሪካ ኢምባሲ አዲስ፣ ሐምሌ 26, 2014)።
ውይይቱ በአፍሪካ ህብረት ብቻ እንዲመቻች የሚፈልጉ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት አዲሱን የአደራዳሪዎች አወቃቀር ተቃውመው የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናትን “ለሰላም ድርድር የማያሻማ ቁርጠኝነት እንዲኖር ግፊት ማድረግ አልቻሉም” ሲሉ ከሰዋል (ትዊተር @ ሬድዋንሁሴን፣ ሐምሌ 28, 2014)። በተመሳሳይ መልኩ መንግስት ባልተገደበ ሁኔታ ዕርዳታ እየገባ መሆኑን በመግለፅ አለም አቀፉን ማህበረሰብ መንግስት ዕርዳታውን ከልክሏል በማለት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ መንግስትን ጥፋተኛ አድርገዋል ሲል ከሰዋል። የትህነግ/ህወሓት ባለስልጣናት የትግራይ “መላው ህዝብ በከበባ ስር ነው” ይላሉ (ትዊተር @ረዳ_ጌታቸው, ሐምሌ 30, 2014)።
ትህነግ/ህወሓት በትግራይ ታጣቂ ሃይሎች ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆኑ እና ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት የባንክ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት መመለስን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን በድጋሚ አንስቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 1, 2014)። የትህነግ/ህወሓት ቀደም ሲል የተዘረዘሩ ቅድመ ሁኔታዎች በኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013 ሪፖርት ላይ ተተንትነዋል። ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ልኡካን ከትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የተላከ አገልግሎት መልሶ ለማቋቋም ለሚሰሩ ሰራተኞች ደህንነት ዋስትና የሚሰጥ ደብዳቤ ይዘው ክመቀሌ ተመልሰዋል (የአሜሪካ ኤምባሲ አዲስ፣ ሐምሌ 26, 2014)።
ድርድሩ የተቋረጠ ቢሆንም፣ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ በመሆናቸው ጦርነቱ በቅርቡ እንደገና ይቀጥላል ተብሎ አይታሰብም። ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በዘለቀው ውጊያ ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ወጪ በማውጣታቸው ምክንያት ይበልጥ ሰላማዊ መንገዶችን ለመፈለግ አበረታቷቸዋል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ባለስልጣናት እየተታዳደረ ያለው የምዕራብ ትግራይ ዞንን ጨምሮ ዋና ዋና እንቅፋቶች አሉ። ሁለቱንም ወገኖች የሚያረካ መፍትሄ እስካልተገኘ ድረስ ውጊያ ተመልሶ ሊቀሰቀስ ይችላል።