በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ነሐሴ 6, 20141እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,211
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 18,702
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,119
ቁጥር: ኢትዮጵያ, ሐምሌ 30-ነሐሴ 6, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 14
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 131
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 26
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች – ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች – መካከል ስድስት የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። እነዚህ ውጊያዎች በቄለም ወለጋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮ ጉዱሩ እና በኢሉ አባ ቦራ ዞኖች ተከስተዋል።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አምስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ ሶስቱ በመንግስት ታጣቂዎች በምዕራብ ጉጂ፣ በቄለም ወለጋ እና በምዕራብ አርሲ ዞኖች የተፈጸሙ ናቸው። አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም ይደግፋሉ በሚል ተከሰዋል። በተጨማሪም የመንግስት ኃይሎች በአርሲ ዞን ሶሌ ኡታ እና ሶሌ ጨፌ ቀበሌዎች ከ26 በላይ የአርሶ አደር ቤቶች እና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በዳሴ ጃቦ እና አባዶ ጃዌ ቀበሌዎች ከ20 በላይ የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶች ኦነግ-ሸኔን ይደግፋሉ በሚል አቃጥለዋል።
በተጨማሪም ሐምሌ 30 ቀን በሆሮ ጉዱሩ ዞን አሙሩ ወረዳ በአጋምሳ ቀበሌ የፋኖ እና የአማራ ብሔረሰብ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥይት ተኩሰው አንድ ሰው ሲገድሉ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎችን አቁስለዋል። በተመሳሳይ ቀን ኦነግ-ሸኔ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ኑሬ ሄራ በተባለ ቦታ 20 የየላየኛው አግሮ ኢንዱስትሪ (ንብረትነቱ የሜድሮክ ኩባንያ የሆነ) ሠራተኞችን ገድሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሠራተኞችን አቁስሏል። ነሐሴ 6 ቀን የዳኖ ወረዳ ነዋሪዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ስዮ ከተማ ኦነግ-ሸኔን በመቃወም ሰልፍ አድርገዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ የፌዴራል ፖሊስ እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል ከቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ታጣቂዎች ጋር ውጊያ ያደረጉ ሲሆን በዚህ ውጊያ 23 የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሲገደሉ አምስት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ 246 ታጣቂዎች ለመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጥተዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ነሐሴ 3, 2014)።
የጋምቤላ ክልል መንግስት በነሐሴ 2 ቀን ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በአግኛዋክ ዞን ዲማ ወረዳ በዲማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የኡኩጉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በጥቃቱ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌላ አንድ ሰው መቁሰሉ ተነግሯል። ታጣቂዎቹ ሁለት ልጆችንም አፍነው ወስደዋል።
በመጨረሻም ነሐሴ 5 ቀን በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን በሚኤሶ ወረዳ በኡንዱፎ፣ ዳንላህላይ እና ሌሎች ውዝግብ ያላባቸው አካባቢዎች በአፋር እና በሶማሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተቀስቅሷል። ሁለቱ ቡድኖች በአካባቢው ባለው አወዛጋቢ ቦታዎች ምክንያት በተደጋጋሚ ይጋጫሉ (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦን የአፋር–ሶማሌ ድንበር ግጭት ገፅ ይመልከቱ)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ያላትን ቁርጠኝነት በወታደራዊ ሰምሪት ማጠናከሯ
በሐምሌ ወር መጨረሻ በአልሸባብ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች መካከል በኢትዮጵያ-ሶማሊያ ድንበር ላይ የተካሄደው ውጊያ ያልተለመደ ክስተት በመሆኑ የኢትዮጵያንም ሆነ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን አስገርሟል። በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የሚመራው በኋላም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ኃይል በተሳካ ሁኔታ የአልሸባብ ታጣቂዎችን መከላከል ችሏል (ስለነዚህ ኩነቶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 9-15, 2014 ይመልከቱ)። የኢትዮጵያም ሆነ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስታት ለሶማሊያ የገቡትን ወታደራዊ ቃል ኪዳን በማጠናከር ላለፉት ጥቂት አመታት የተገበሩትን ፖሊሲዎች በመቀልበስ ለጥቃቱ ምላሽ ሰጥተዋል።
ባለፈው ሳምንት፣ ነሐሴ 2 ቀን የሶማሊያ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ከሳምንት በፊት ጥቃቱ እና ውጊያው በተከሰተበት በደቡብ ምዕራብ በምትገኘው በዶሎ ከተማ አቅራቢያ የጦር ሰፈር በመመስረት ማሰማራቷን ገልፀዋል (ቪኦኤ፣ ነሐሴ 3, 2014)። እንደ አክሌድ መረጃ ከሆነ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጄቶች ከሀምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአልሸባብ ታጣቂዎች ላይ ቢያንስ ስምንት የአየር ጥቃቶችን አድርገዋል።
በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችን በሃገሪቱ እንደገና የማሰማራት እቅድ በማፅደቃቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የሚገኙትን 700 የሚጠጉ የምድር ጦር ኃይሎች ለቀው ያስወጡበትን ውሳኔ በመሻር ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሊያ የጀመረችውን ተሳትፎ አጠናክራለች (ኒውዮርክ ታይምስ፣ ግንቦት 8, 2014)። በእርግጥ ከመጋቢት 2014 በኃላ ዩናይትድ ስቴትስ ነሐሴ 8 ቀን በቡድኑ ላይ እጅግ አስከፊ የሆነ የአየር ድብደባ በሶማሊያ ማእከላዊ ክልል ሂራን ያደረገች ሲሆን ቢያንስ 14 የአልሸባብ አባላት ተገድለዋል (ቪኦኤ፣ ነሐሴ 9, 2014)።
ይህ የቅርብ ጊዜው የወታደራዊ ሰምሪት እና የአየር ድብደባ የኢትዮጵያ እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግስታት ፖሊሲ መቀልበስን ያሳያል። ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በጥቅምት 2013 ከትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ጋር የተቀሰቀሰውን የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ከሶማሊያ ማስወጣት ጀመራለች (ብሎምበርግ፣ ህዳር 4, 2013)። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አልሸባብ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ወታደሮች ተይዘው የነበሩ ከተሞችን በመቆጣጠር ተስፋፍቷል።
የሶማሊያ አለመረጋጋት በማዕከላዊው መንግስት እና በፌዴራል አባል ክልሎች መካከል ያለው አለመግባባት እና ውዝግብ የሞላበት የፖለቲካ ስርአት ነው። የአልሸባብ የ15-አመታት ሽምቅ ውጊያ ፍጻሜ በሌለው መልኩ የቀጠለ ሲሆን በተጨማሪም በቡድኑ ላይ ለተደረጉ የተለያዩ የፀረ-ሽምቅ ዘመቻዎችን ቡድኑ ያለማቋረጥ ተቋቁሟል (ክራይስስ ግሩፕ፣ ሰኔ 14, 2014)። የዩናይትድ ስቴትስ እና የኢትዮጵያ የታደሱ ግንኙነቶች አልሸባብ በሶማሊያ ያለውን ጥንካሬ ለመቀየር አዳጋች ቢሆንባቸውም እንኳን የቡድኑን የወደፊት መስፋፋቱን ሊገቱ ይችሉ ይሆናል።
ይሁን እንጂ በተለይ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ወታደሮች ዋጋው በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ግጭቶች በመላ ሀገሪቱ እየሰፉ በመምጣቱ የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ ናቸው። ከቅርብ ወራት ወዲህ የሰሜኑ ጦርነት ጋብ ቢልም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች የተቀሰቀሱ ሽምቅ ውጊያዎች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት በአሁኑ ወቅት ያለውን የጸጥታ ኃይል አቅም በላይ እንዳይሆን ስጋት ፈጥሯል።