በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጷጉሜ 4, 20141እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,331
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 19,181
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,403
ቁጥር: ኢትዮጵያ, ነሐሴ 7-ጷጉሜ 4, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 117
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 453
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 261
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ነሐሴ 18 ቀን በመንግስት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች መካከል ውጊያዎች በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች እንደገና ተቀሰቅሷል። ውጊያው የተከሰተው መጋቢት 15 ቀን የሰብአዊ ተኩስ አቁም መታወጁን ተከትሎ ከአምስት ወራት አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ ነው። ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች አዲሱን ውጊያ በማናሳሳት አንዱ ሌላውን ወንጅሏል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ነሐሴ 18, 2014፣ ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ ነሐሴ 18, 2014)።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን እና በትግራይ ክልል ደቡባዊ ትግራይ ዞን በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ተከስተዋል። በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ በጨውበር፣ ዞብል ተራሮች፣ ጀሮታ እና ተኩለሽ እና በጊዳን ወረዳ ወትወት ውጊያዎች መከሰታቸው ተዘግቧል። በደቡብ ትግራይ ክልል በጨርጨር ወረዳ ቢሶበር እና በራያ አላማጣ ወረዳ ጎባ ጋላ ውጊያዎች ተከስቷል። በሌላ በኩል በአፋር ክልል የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በፋንቲ ራሱ-ዞን 4 በያሎ ወረዳ በሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮሳቸው ሶስት ሰላማዊ ሰዋች ሲሞቱ በትንሹ 10 ሰላማዊ ሰዋች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል (ዲደብሊው አማረኛ፣ ነሐሴ 19, 2014)። በያሎ ወረዳም የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች እና የአፋር ታጣቂዎች ተዋግተዋል።
ውጊያው በፍጥነት በአፋር ክልል ፋንቲ ረሱ-ዞን 4፣ በትግራይ ክልል በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ማዕከላዊ ትግራይ፣ ምስራቃዊ ትግራይ እና ምዕራብ ትግራይ ዞኖች; በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ተስፋፍቷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በኢትዮጵያና በሱዳን አዋሳኝ አካባቢ በምዕራብ ትግራይ በቤከር፣ በረከት፣ ሎግዲ እና ሸረሪና አካባቢዎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ትህነግ/ህወሓት ኃይሎች እና ሳምሪ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መደረጉ ተዘግቧል።
በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ በተካሄደው ውጊያ ውስጥ የተሳተፉት በርካታ የትህነግ/ህወሓት ወታደሮች በደቡብ ሱዳን በአቢዬ በነበረው የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ካገለገሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ እና በሱዳን ጥገኝነት የጠየቁ የቀድሞ የትግራይ ተወላጆች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መሆናቸው ተነግሯል (ብሉምበርግ፣ ነሐሴ 27, 2014)። ከበርካታ ወራት በፊት ሱዳን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ሀገራት እና በባንግላዲሽ ጦር እንዲተኩ ከጠየቀች በኋላ፣ በአቢዬ የነበሩ 528 የትግራይ ተወላጆች የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የደህንነት ሰጋት አለብን በማለት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም (ሱዳን ትሪቡን፣ ሚያዚያ 16, 2014)። እነዚህ ዘገባዎች ቢኖሩም፣ የሱዳን ጦር ኃይሎች የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች/የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በሱዳን ይገኛሉ የሚለውን አስተባብሏል (ብሉምበርግ፣ ነሐሴ 27, 2014)። የትግራይ ተወላጆች የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የሱዳን ቆይታቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) በቅርቡ ይፋ ካደረገው በጥቅምት 2012 በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰወን ግጭት ተከተሎ የትግራይ ተወላጆች ተጠልለው በሚገኙበት በሰሜን በምስራቅ ሱዳን በሚገኙ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ እንደነበረ ከመግለፁ ጋር ተገጣጥሟል (ሱዳን ትሪቡን፣ ጷጉሜ 2, 2014)።
በሌላ በኩል የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እና የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በምዕራብ ትግራይ ዞን አዲ ጎሹ እና ፀፀር፣ በማእከላዊ ትግራይ ዞን ራማ እና ምስራቅ ትግራይ ዞን ፀሮና እና ዘለአምበሳ እንዲሁም በአፋር ክልል ኪልባቲ ረሱ-ዞን 2 ዳሎል ላይ ተዋግተዋል።3ይህ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት መረጃ በትህነግ/ህወሓት የተሰጠ ነው። በአፋር ውስጥ ሊኖር የሚችል ኩነት የተመዘገበው በአከባቢው ስም ምክንያት ነው (ይህ የቦታ ስም በአፋር ክልል እንጂ በትግራይ ክልል ውስጥ ሊገኝ አልተቻለም)። ጷጉሜ 2 ቀን የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በአዲግራት ከተማ ዙሪያ ትህነግ/ህወሓት በሚቆጣጠራቸው ቦታዎች ላይ መድፍ መተኮሱ ተነግሯል።
ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ ላይ የህፃናት መጫወቻ ሜዳ እና ሆስፒታልን ጨምሮ የተለያዩ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የታገዙ የአየር ድብደባዎች ጥቃት መፈፀሙ ተነግሯል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ነሐሴ 25, 2014፤ ሮይተርስ፣ ነሐሴ 20, 2014)። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ትግራይ ዞን ውስጥ ባልታወቀ ቦታ ለትህነግ/ህወሓት መሳሪያ ጭኖ ነበር የተባለ አንቶኖቭ አይሮፕላን መምታቱን ተናግሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አውሮፕላኑ የኢትዮጵያ አየር ክልል የገባው ከሱዳን በኩል መሆኑን ገልጿል (ፋና ቴሌቪዥን፣ ነሐሴ 20, 2014)። ትህነግ/ህወሓት ይህንን ክስ አስተባብሏል (ቲዊተር@ትግራይ ኢኤኦ፣ ነሐሴ 18, 2014)። ነሐሴ 20 ቀን የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ሰዎች ከትህነግ/ህወሓት ወታደራዊ ማሰልጠኛ እና ካምፖች አካባቢዎች እንዲርቁ ጠይቋል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ነሐሴ 20, 2014)።
በነሐሴ በተቀሰቀሰው ውጊያ የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማን፣ የመንደፈራ ቀበሌን እና የዞብል ተራራን እንደገና በቁጥጥር ስር አውለዋል። የፌዴራል መንግስት በቆቦ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ከፈተኛ ጉዳት ለማስቀረት ሠራዊቱ ለቆ መውጣቱን አስታውቋል። የመንግስት ኃይሎች በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞን አበርገሌን እና በሰሜን ጎንደር ዞን አዲ አረቃይን ቆላ ተምቤን፣ በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ቆላ ተንበይን እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ማይ ጸምሬን፣ ደደቢትን፣ ፀልሞዬን፣ ማሂ አንፂን፣ አደይ መደዳይን እና ማይ ታሳይን በድጋሚ መቆጣጠራቸው ተነግሯል። ። የትህነግ/ህወሀት ኃይሎች ሃላፊ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ጥምር ኃይል ሸራሮን፣ አደመጢ፣ ሃልነብሪ እና አዲ አረቃይን እንደገና መቆጣጠራቸውን አረጋግጠዋል (ትግራይ ቲቪ፣ መስከረም 3, 2015)።
በቅርቡ የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የሌሊት የሰዓት እላፊ እና በከተሞቻቸው ያሉ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ጣቢያቸው እንዳይወጡ የሚከለክል ገደብን ጨምሮ የተለያሉ ገደቦችን አውጀዋል። በአማራ ክልል በቆቦ፣ ኮምቦልቻ እና ደባርቅ ከተሞች ከትህነግ/ህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ውጊያው የተቀሰቀሰው በርካቶች የሰላም ድርድሩ መሻሻል ያሳያል ብለው በሚጠብቁበት ወቅት ነው። የአሜሪካ መንግሥት እና የአውሮጳ ኅብረት ተወካዮች እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ቀስቅሷል ያሉትን አዲስ ውጊያ ሲያወግዙ፣ ሌሎች ደግሞ ትህነግ/ህወሓትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎችን በአዲስ አበባ፣ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ አድርገዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጷጉሜ 4, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ጷጉሜ 3, 2014፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ነሐሴ 24, 2014)። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሁሉም አካላት መሳሪያቸውን እንዲያስቀምጡ እና በውይይት መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል (ቲክቫህ-ኢትዮጵያ, ጷጉሜ 4, 2014)።
የኢትዮጵያ አዲስ አመት መስከረም 1 ቀን ላይ ትህነግ/ህወሓት በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ከፌዴራል መንግስት የሚደረገውን የሰላም ድርድር መቀበሉን አስታውቆ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ከተመረጡት ተወካዮች ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል (ቲዊተር@ትግራይ ኢኤኦ፣ መስከረም 1, 2014)። ከነሐሴው ውጊያ በኋላ ትህነግ/ህወሓት በድርድሩ ላይ ባለው አቋም በርካታ ግልፅ የሆኑ ለውጦች ታይተዋል፤ ከዚህ ቀደም የትህነግ/ህወሓት መሪዎች በፌዴራል መንግስት ሊሟሉ ይገባቸዋል ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ድርድሩም በቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲመራ ፈልገው ነበር ( ዘ አፍሪካ ሪፖርት ነሐሴ 16, 2014፤ ትግራይ ቲቪ፣ ነሐሴ 12, 2014፤ በትህነግ/ህወሓት የቀረበው የቅድመ ሁኔታ ዝርዝር ላይ የበለጠ ዝርዝር ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013 ይመልከቱ)። በተጨማሪም ትህነግ/ህወሓት የሽግግር መንግስት መመስረትን ሊያስከተል በሚያስችል እይታ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ የፖለቲካ ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጿል። መንግስት ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ያቀረቡትን ተመሳሳይ ጥሪዎችን ችላ ብሏል። የፌዴራል መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች አሁን ያለው መንግስት በህገ መንግስቱ መሠረት የተመረጠ መሆኑን እና የሽግግር መንግስት እንደማይኖር አረጋግጧል።
ይህ የሰሞኑ የትህነግ/ህወሓት መግለጫ ምንም ይሁን ምን በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰው አልባ አውሮፕላን የታገዙ የአየር ድብደባዎች እንደቀጠሉ ነው (ቪኦኤ አማርኛ፣ መሰከረም 3, 2015፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ መሰከረም 4, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል ምንም እንኳን መጠኑ የቀነሰ ቢሆንም ጦርነቶች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በክልሉ ቀጥለዋል – ከነሐሴ 7 እስከ ጷጉሜ 4, 2014 ባለው ጊዜ 10 የጦርነት እና 22 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል።በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያዎች በጉጂ፣ ኢሉ አባ ቦራ፣ ቄሌም ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ተከስቷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስራቅ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ፣ በቄሌም ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተዘግቧል። ለእነዚህ ጥቃቶች ተጠያቂ የሆኑት የፋኖ ታጣቂዎች፣ ኦነግ-ሸኔ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን ናቸው። በሆሮ ጉዱሩ ዞን አምሩ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ከፍተኛው ሞት ተመዝግቧል። በነሐሴ 24 እና 25 ከአምሩ ወረዳ አዲስ አለም ቀበሌ እና ከአማራ ክልል ቡሬ ወረዳ የመጡ የአማራ ታጣቂዎች በአምሩ ወረዳ ከ60 ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆችን ሲገድሉ ከ70 ያላነሱ ደግሞ አቁስለዋል። ጥቃቶቹ የተመዘገቡት በአጋምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙ፣ ጀቦ ዶባን፣ ጦምቤ ዳነጋበ፣ ጃዋጅ፣ ኛሬ፣ ለገ ሚቻ፣ ሉቁማ ዋሌ ቀበሌዎች ነው (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጷጉሜ 1, 2014)። ይህ ጥቃት የተፈፀመው ኦነግ-ሸኔ የአምሩ ወረዳ አስተዳደር ማዕከል የሆነችውን አቦራ ከተማን ለመያዝ ሲሞክር በአጋምሳ ቀበሌ ሦስት የአማራ ተወላጆችን ከገደለ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ቡድኑ በቀበሌው የሚገኙ 59 ሰዎችንም ትጥቅ አስፈትቷል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ነሐሴ 22 ቀን ከአካባቢው ለቆ ወጥቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 25, 2014)። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከነሐሴ 23 እስከ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ ኦነግ-ሸኔ በአጋምሳ ከተማ 11 ሰዎችን ገድሎ ሌሎች 11 ሰዎችን አቁስሏል። ቡድኑ በአሙሩ ወረዳ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ቅርንጫፎችንም ዘርፏል (አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 28, 2014)። እነዚህን ጥቃቶች ተከትሎ ከ20,000 በላይ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች ለመሰደድ ተገደዋል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጷጉሜ 1, 2014)።
በአማራ ክልል በመንግስትና በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች መካከል ከነበረው ውጊያ በተጨማሪ ነሐሴ 26 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የሸዋ ሮቢት ከንቲባን ተኩሰው ገድለዋል። ከዚህ ጥቃት በስተጀርባ ያለው ምክንያት አይታወቅም።
በአፋር ክልል በሶማሌ እና በአፋር ድንበር ላይ አወዛጋቢ በሆነው በገዳማይቱ አካባቢ ግጭት ተቀስቅሷል (ስለነዚህ አወዛጋቢ አካባቢዎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦን የአፋር–ሶማሌ ድንበር ግጭትን ይመልከቱ)። ነሐሴ 11 አካባቢ በጋቢ ዞን 3 በገዳማይቱ የአፋር እና የሶማሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች ተዋግተዋል። የሶማሌ ክልል መንግስት ወደ 60,000 የሚጠጉ የሶማሌ ተወላጆች አካባቢውን ለቀው መሰደዳቸውን አስታውቋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ነሐሴ 13, 2014; አዲስ ስታንደርድ ነሐሴ 12, 2014) ነሐሴ 18 ቀን ኦነግ-ሸኔ በሃሪ-ዞን 5 በዳዌ ወረዳ በቡርቃ ከተማ ገብተው የቤት ለቤት ፍተሻ ካደረጉ በኋላ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ገድሏል።
ነሐሴ 12 ቀን በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን በቤኪ ከተማ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንታዊ ልዑካን ቡድን በከተማው የሚገኙ ከገዳማይቱ የተፈናቃሉ ሰዎች በሚጎበኙበት ወቅት ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። ተቃዋሚዎቹ የክልሉ መንግስት በገዳማይቱ በአፋር እና በሶማሌ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደውን ውጊያ የያዘበት ሁኔታ የተቃወሙ ሲሆን “በውጊያው ወቅት የመንግስትን ዝምታ” አውግዘዋል (ሂይራን ኦንላይን፣ ነሐሴ 12, 2014፣ ቲክቫህ-ኢትዮጵያ፣ 12, 2014)። የክልሉ ልዩ ኃይል እንደሆኑ የተጠረጠሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሰማይ በመተኮስ ተቃዋሚዎቹን በትነዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነሐሴ 23 እና 24 በቆራሄ ዞን ሽላቦ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በሊንታ ቁራኦ ሽሬ መንደር በመሬት ውዝግብ የተነሳ የማረሃን ጎሳ ታጣቂዎች በማቃቡል ጎሳ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተዋግተዋል። በትንሹ 10 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ‘ክላስተር ክልሎች’ ለመመስረት መንግስት ያቀረበውን ሀሳብ ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሶ በቀጠለበት ወቅት፣ የክልሉ ኮማንድ ፖስት የሰዓት እላፊ አዋጅ ያወጀ ሲሆን፣ የሞተር ብስክሌቶችን እንቅስቃሴ በመገደብ እና በወልቂጤ ከተማ እና በመላው የጉራጌ ዞን “ምንም አይነት ተቃውሞ እና ህዝባዊ ስብሰባ” እንዳይካሄድ አግዷል (አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 12, 2014፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስለታቀዱት የክላስተር ክልሎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሃዊ፡ ሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ይመልከቱ)። በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ የክልሉ ፖሊስ በወልቂጤ ከተማ የዞኑን ፀጥታ ሴክተር ሃላፊን ጨምሮ የተለያዩ ወጣቶችን እና የዞኑን ባለስልጣናትን አዲስ የቀረበውን ክላስተር ክልል በመቃወም፣ የራስ አስተዳደር እንዲከበር በመጠየቅ እና ከቤት ያላመውጣት እና ንግድ ቤቶች እንዲዘጉ በማደራጀት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውሏል። በኋላም የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች የጉራጌ ዞን ውሳኔን መንግስት ባለማክበሩ እና ለጥያቄያቸው ምላሽ ባለመስጠቱ መንግስትን ከቤታቸው ባለመውጣት እና የስራ እና የንግድ ማዕከላትን ባለመክፈት ተቃውመዋል (አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 21, 2014)።
በመጨረሻም የጋራ የሰላምና ፀጥታ ግብረ ሃይል በአዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ 31 ግለሰቦችን ከተለያዩ መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሏል። ግብረ ኃይሉ ግለሰቦቹን በኃይማኖታዊ ተቋማት ሽፋን ወታደራዊ ስልጠና በመሰጠት እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በማቀድ ተጠርጥረው መታሰራቸውን ገልጿል።