በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 – መስከረም 13, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,380
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 19,518
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,475
ቁጥር: ኢትዮጵያ, መስከረም 7-13, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 29
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 259
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 39
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በመንግስት ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ቀጥለዋል። በትግራይ ክልል አምስት የውጊያ ኩነቶች በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ዘለ አምበሳ፣ በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ራማ አቅራቢያ እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን በዚባን ጌደና ከተማ፣ ማይ ኩሂሊ እና በአዲ አዋላ ዙሪያ ተዘግበዋል። በእነዚህ ሁሉ ቦታዎች በነበሩት ውጊያዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እና የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ተሳትፈዋል። ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ውጊያ ለመሳተፍ የታጠቁ ኃይሎቿን እና “ተጠባባቂ” ከ60 ዓመት በታች የሆኑ ኃይሎቿን ወደ ጦሯ እንዲቀላቀሉ ጠርታለች (ሮይተርስ፣ መስከረም 7, 2015)።
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚደርሰው የሰው አልባ አውሮፕላኖች (የድሮን) አየር ጥቃት ቀጥሏል። መስከረም 7 ቀን በትግራይ ክልል በመቀሌ፣ ሽሬ እና ውቅሮ የሚገኙ ወታደራዊ ማዕከሎች የሰው አልባ አውሮፕላኖች ደብድበዋል። ትህነግ/ህወሓት እንደገለፀው በእነዚህ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች 12 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል (ኢኤምኤስ፣ መስከረም 7, 2015)። ከጥቂት ቀናት በኋላ መስከረም 13 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመቀሌ ደስታ ሆቴል አካባቢ ሌላ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በመፈፀሙ አንድ ሰው ሞቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ስላለው ግጭት የሚዲያ ዘገባዎችን መገደቡን ቀጥሏል። ይህ አዲሱ ዙር ውጊያ ከመቀስቀሱ አንድ ቀን በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘጋቢዎች የሠራዊቱን እንቅስቃሴ እንዳይዘግቡ አስጠንቅቋል (የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት፣ ነሐሴ 17, 2014)። ስለዚህ በሰሜን ሰላለው ውጊያ የሚወጡ ዘገባዎችን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ይባስ ብሎም የማይቻል ነው። ከነሐሴ 18 እስከ 25 መንግስት ጦርነት የተካሄደባቸው ቦታዎች ላይ አንዳንድ ዝርዝሮችን ቢያወጣም ከዚያ በኃላ ግን በቅርቡ የሰጠው መረጃ የለም። ትህነግ/ህወሓት ግን ውጊያው ሰለ ሚደረግባቸው ቦታዎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰለሚፈፅማቸው የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶች መረጃ ማውጣቱን ቀጥሏል ነገር ግን እንደተጠቀሰው እነዚህን ዘገባዎች በገለልተኛ ወገን ለማጣራት እና ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው። መንግስትም ሆነ ትህነግ/ህወሓት የውጊያ ተግባራቸውን በተመለከተ መረጃ ከመግለፅ ይቆጠባሉ።
ከአጭር ጊዜ መረጋጋት በኋላ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ጦርነት አገርሽቷል። ኦነግ-ሸኔ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት ኃይሎች በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ጉጂ፣ አርሲ፣ ምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ተዋግተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ኦነግ-ሸኔ በጉጂ ዞን መልካ ጉባ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጦር ካምፕ ማጥቃቱን፤ በአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ አኖሌ ሀውልት አቅራቢያ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን በቢላ ስዮ ወረዳ ጫሊ ጂማ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት ኃይሎችን ሲያጏጉዙ በነበሩ ኮንቮይዎች (መኪኖች) ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈፀሙ ተነግሯል (ኦኤምኤን፣ መስከረም 12, 2015)።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የቀጠለ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ስድስት ኩነቶች ተመዝግበዋል፤ ከስድስቱ ጥቃቶች ሦስቱ የተፈጸሙት በኦነግ-ሸኔ ነው። መስከረም 10 ቀን ኦነግ-ሸኔ እንደሆነ የተጠረጠረ ማንነቱ ያልተገለፀ ታጣቂ ቡድን በምስራቅ ሸዋ ዞን በፈንታሌ ወረዳ የአልጌ ቀበሌ ሊቀመንበርን በጥይት ተኩሶ ገድሏል። ከመስከረም 12 እስከ 13 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ከተማ በቀበሌ 01 ኦነግ-ሸኔ ሰላማዊ ሰዎችን ማጥቃት ሲጀምር ከቀበሌ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል። መንግስት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የመንግስት ታጣቂዎች መስከረም 13 ቀን ከአማፂ ቡድኑ አዛዦች አንዱን ከገደሉ በኋላ ኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች እና በቀበሌ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አመልክቷል (በኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ መስከረም 14, 2015)። ጋዜጣዊ መግለጫው ግን ተጨማሪ ዝርዝሮችን ከመስጠት ተቆጥቧል። በተለምዶ መንግስት እንደዚህ ያሉ መግለጫዎችን ሲሰጥ የሰላማዊ ሰዎች ሞት ቁጥር ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ ነው። በዚህ አካባቢ ሁሉም የመገናኛ አውታሮች በመጥፋታቸው እስካሁን ድረስ እነዚህ ጥቃቶች በሚመለከት ሌላ ዝርዝር ዘገባ አልወጣም (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 13, 2015)። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በአሙሩ፣ ሆሮ ቡልቅ እና ጃርደጋ ጃርቴ “ኦነግ-ሸኔ፣ አማራ ታጣቂዎች እና ግለሰቦች” ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ንፁሀን ሰዎች መገደላቸውን አመላክቷል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶ ኮሚሽን፣ መስከረም 16, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል ከህግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ ግድያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች በመንግስት ኃይሎች ግድያዎች መፈፀማቸው ተዘግቧል።
የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች በአማራ እና ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በተከሰቱ ኩነቶችም ተሳትፈዋል። ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ደዋ ሀረዋ ወረዳ ቡርቃ፣ ዋርሳመት እና ካራ ዳካ አካባቢዎች ላይ ኦነግ-ሸኔ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ከአማራ ክልል ፖሊስ እና ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል። በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መስከረም 8 ቀን በቡርጂ ልዩ ወረዳ አውራንጄ ቀበሌ የኦነግ-ሸኔ አባላት ከብቶቻቸውን በሚጠብቁ አርሶ አደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው ሁለት አርሶ አደሮችን ገድለው አንድ ሌላ አርሶ አደር አቁስለዋል። ቡድኑ ወደ 30 የሚጠጉ የቀንድ ከብቶችንም ገድሏል።
በተጨማሪም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መስከረም 11 ቀን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የመጣ ኦነግ-ሸኔ ነው ተብሎ የሚጠረጠር ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቀ ቡድን ዘጠኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ሲጠባበቁ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል። እነዚህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአማሮ ልዩ ወረዳ በዶርባሌ ቀበሌ መልካ ኦዳ መንደር በቆሬ ብሄረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲያጣሩ የተመደቡ ናቸው (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 12, 2015)። በዚህ ጥቃት አምስት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ አራት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ተገደዋል።
በመጨረሻም በተመሳሳይ ቀን ከደቡብ ሱዳን ድንበር ማሉዋል ጋኦት በተባለው አካባቢ ከደቡብ ሱዳን የመጣ ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ባሮ ወንዝ ላይ ከጃካዎ ድልድይ ወደ መተሃር ከተማ ሲጓዝ በነበረ ሞተር ጀልባ ላይ ተኩስ ከፍቷል። የታጠቀው ቡድን ከታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት ተኩስ መክፈቱ ተነግሯል። በዚህ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት ሰባት ሰዎች ቆስለዋል። ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ የደረሱበት እንዳልታወቀ ተዘግቧል።