በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 – መስከረም 20, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,417
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 19,701
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,591
በቁጥር: ኢትዮጵያ, መስከረም 14-20, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 31
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 112
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 65
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል እና በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ውጊያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚፈፀሙ ጥቃቶች ብዙ ሰዎች እየተጎዱ በመሆናቸው አለመረጋጋት ቀጥሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያዎች እና የሰው አልባ አውሮፕላን (የድሮን) ጥቃቶች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ፣ ጊዳን እና ጎቢዬ አካባቢዎች በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ቢያንስ 16 ውጊያዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የመንግስት ኃይሎች በራያ ቆቦ ወረዳ ተኩለሽ፣ ሸዊ ማርያም፣ አረፋ ጎርጊስ፣ ጤፍ ወሃ እና በቃሊሞ አጎላ አካባቢዎችን መልሰው መቆጣጠራቸውን ተነግሯል። በትግራይ ክልል በብዛት የተዘገበው የጦርነት ኩነት የተከሰተው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ነው። በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ማይ ፀምሪ በተባለው አካባቢ ሁለቱ ወገኖች ተዋግተዋል። በዚሁ ዞን ሶስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶች በባሃራ፣ አዲ ዳዕሮ እና ሽሬ ላይ መድረሱም ታውቋል። መስከረም 15 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በባሃራ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አድርሷል። በዚህ ጥቃት ከሽሬ ወደ ዛና አካባቢ ይጓዝ በነበረ የዓለም ምግብ ድርጅት ተሽከርካሪ ላይ እና በአሽከርካሪው ላይ ጉዳት ደርሷል። መንግስት የሰው አልባ አውሮፕላኑ የፈጸመው ጥቃት በትህነግ/ህወሓት የጦር ካምፖች እና የጦር መሳሪያ መጋዘኖች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የገለፀ ሲሆን የእርዳታ ሰራተኞችም በእነዚህ አካባቢዎች ስራቸውን እንዲያቆሙ ጠይቋል። መንግስት ትህነግ/ህወሓት ሰራዊቱን ለማጓጓዝ የሰብአዊ ዕርዳታ ተሽከርካሪዎችን ይጠቀማል ሲል በድጋሚ ከሷል (በኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ መስከረም 16 ቀን 2022)።
ከሁለት ቀናት በኋላ፣ በመስከረም 17 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሌላ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በአዲ ዳዕሮ አድርጓል። በዚህ ጥቃት ምክንያት ቢያንስ አምስት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 16 ሰዎች ቆስለዋል። ትህነግ/ህወሓት የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በሚግ-29 ተዋጊ አይሮፕላን ነው ሲል ተናግሯል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ 19 መስከረም, 2015)። የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ሃይሉ “የትህነግ/ህወሓት የጦር መሳሪያዎች ባሉበት ቦታ ላይ ያነጣጠረ የሰው አልባ አውሮፕላን” ጥቃት መፈፀሙን ገልጾ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሰላማዊ ሰዎች በወታደራዊ ኢላማዎች አለመኖራቸውን ካረጋገጠ በኃላ እርምጃ ይወስዳል” ሲል ተናግሯል። መንግስት “የኢትዮጵያ አየር ክልል በጥብቅ ክትትል ውስጥ ነው” ሲል የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በአዲ ዳዕሮ የአየር ጥቃት አድርጓል ከሚለው ክስ እራሱን ማግለል እንደሚፈልግ ጠቁሟል (ኢትዮጵያ ከረንት ኢሹ ፋክት ቼክ፣ መስከረም 20, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል ሁለት የውጊያ ኩነቶች በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ተዘግበዋል። በቦሰት ወረዳ በላዬኛው አዋሽ ተፋሰስ እርሻ ልማት (ኑራ ሄራ እርሻ ልማት – ኑራ ሄራ ግብርና ማዕከል) በተባለው አካባቢ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረስ መጀመሩን ተከትሎ ከመንግስት ኃይሎች ጋር መዋጋቱ ተነግሯል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን ኦነግ-ሸኔ በግብርና ማዕከሉ የሚገኙ 11 ጣቢያዎችን መቆጣጠሩ ተነግሯል።
በክልሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በመንግስት ኃይሎች የተፈፀሙ ሁለት ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑ ግድያዎች በቡኖ በደሌ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተዘግበዋል። በምዕራብ ጉጂ ዞን ሰባት ወረዳዎች የመንግስት ኃይሎች ከ1,000 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ታሳሪዎቹ ኦነግ-ሸኔን “በሎጂስቲክስ” በመደገፍ “ልጆቻቸው የኦነግ-ሸኔ አባል እንዲሆኑ ወደ ኦነግ-ሸኔ በመላክ” እና ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የታሰሩ ናቸው (ኢሳት፣ መስከረም 18, 2015)። የአዳማ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና የክልሉ ፖሊስ 33 የኦነግ-ሸኔ እና የአባ ቶርቤ – ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገመት ቡድን – እና 49 የትህነግ/ህወሓት አባላትን በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማ “ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ እና የመስቀል እና የኢሬቻ በዓልን ለማወክ በማቀድ” ሲል በመጠርጠር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል (አዲስ ማለዳ፣ መስከረም 19 ቀን 2015)።
ኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ በመቋረጡ ምክንያት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሁንም ያለው ሁኔታው አልታወቀም፤ አንዳንድ ዘገባዎች ኦነግ-ሸኔ መስከረም 15 ቀን የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳን እንደተቆጣጠረ ያመላክታሉ (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 19, 2015)። በኦነግ-ሸኔ እና በቀበሌ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የጀመረው መስከረም 12 ነበር (ስለእነዚህ ኩነቶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: መስከረም 7-13, 2015ን ይመልከቱ)። መስከረም 15 ቀን በኦነግ-ሸኔ በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ወደ አሙሩ ወረዳ ተዛምቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 18, 2015)። ኦነግ-ሸኔ በዚህ ወረዳ እና አካባቢው በሚገኘው አሙሩ ወረዳ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየፈፀመ መሆኑን ወደሌሎች አካባቢዎች የተሰደዱትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ገልጸዋል። በእነዚህ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ይገመታል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 19, 2015፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 19, 2015፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 18 , 2015)። ኦነግ-ሸኔ በእነዚህ ጥቃቶች ላይ ምንም ተሳትፎ እንደሌለው አስተባብሏል (ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ መስከረም 23, 2015)።
በተጨማሪም በሆሮ ጉዱሩ ዞን የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተለይም በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 19, 2015)። መስከረም 15 ቀን በአሙሩ ወረዳ በጎቡ ሲባ፣ ኦቦራ፣ ሃሮጉዲና፣ ወልቂጤ እና ሪጌቴ ቀበሌዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተዘግቧል። ከእነዚህ ጥቃቶች ጀርባ ማን እንዳለ ግን ግልፅ አይደለም (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 18, 2015)። አንዳንድ እማኞች ግን በጎቡ ሲባ ቀበሌ ለደረሰው ጥቃት የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ሲያደርጉ በጥቃቱ ከ35 በላይ ሰላማዊ ሰዎች በአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸውን ተናግረዋል(ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 16, 2015፤ ኦኤንኤም፣ መስከረም 15, 2015)። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላ እማኝ ደግሞ ኦነግ-ሸኔ ወደ ቀበሌው በመግባት በትንሹ አምስት የአማራ ተወላጆችን መግደሉን ተናግረዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 16, 2015)።
ላለፉት ሶስት አመታት ሰላማዊ ሰዎች በሁሉም ወለጋ አካባቢዎች ማለትም በምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች በኦነግ-ሸኔ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል (በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሰለሚደርሰው ጥቃት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ይመልከቱ)። በተለይ የአማራ ተወላጅ ሰላማዊ ሰዎች በዚህ ጥዋት ኢላማ ሆነዋል። እነዚህ ሶስት ዞኖች በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ወቅት ከአማራ ክልል ወሎ አካባቢ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉት ብዙ የአማራ ተወላጆች ይገኙባቸዋል (ካሳ በላይ፣ እ.ኤ.አ. 2004፤ ደስአለኝ ራህማቶ፣ እ.ኤ.አ.2003)። የአክሌድ መረጃ እነዚህ ጥቃቶች እ.ኤ.አ. በ2021 እና 2022 (ከታህሳስ 2013 ጀምሮ) እየበዙ መምጣታቸውን ያሳያል። መንግስት በእነዚህ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት መከላከል ባለመቻሉ በመንግስት እና በአማራ ማህበረሰብ መካከል ውጥረት ነግሷል። በመሆኑም እነዚህ ጥቃቶች አማራዎች እራሳቸውን በእነዚህ አካባቢዎች እና በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎችን በሚያዋስኑ አካባቢዎች እንዲከላከሉ እያስገደዷቸው ነው። በኦሮሚያ ክልል የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በዋናነት በፖለቲካ አለመረጋጋት ኩነቶች ከታህሳስ 2013 ጀምሮ ተሳታፊ መሆናቸውን እና የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ ከታህሳስ 2014 ጀምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር መጀመራቸውን የአክሌድ መረጃ ያመላክታል። በአዲስ አበባ መስከረም 21 ቀን የኢሬቻ በዓል – በኦሮሞዎች የተከበረው የምስጋና ቀን – በሚከበርበት ወቅት የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎችን እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን እና በወለጋ ያለውን ግድያዎችን የሚቃወም ተቃውሞ ተደርጏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 21, 2015)። ይህ በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰቦች፣ ተወካዮች እና መንግስታት መካከል ሌላ ውጥረት ይፈጥራል።