በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 – መስከረም 27, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,448
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 19,889
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,771
በቁጥር: ኢትዮጵያ, መስከረም 21-27, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 21
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 104
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 102
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ጦርነት ቀጥሏል፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ በሮቢት ተራራ እና በላንጎ ዙሪያ እንዲሁም በትግራይ ክልል በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ሽሬ እና አዲ ሃገራይ በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ውጊያዎች ተዘግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ውጊያውን ተከትሎ የመንግስት ኃይሎች ሽሬን እና አዲ ሃገራይን መቆጣጠራቸውን ተነግሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችን በትግራይ ክልል አዲ ዳዕሮ፣ ዛና፣ ዳንግላት እና አግቤ አካባቢዎች አድርሷል። በአዲ ዳዕሮ ከተማ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን በማስጠለል ላይ የሚገኝ ትምህርት ቤትን በመምታቱ ከ50 በላይ ሰዎች ሲሞቱ 70 ሰዎች ቆስለዋል (ሮይተርስ፣ መስከረም 25, 2015)። በዳንግላት በተፈፀመው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በትንሹ አምስት ሰዎች ሲሞቱ 37 ሰዎች ቆስለዋል (ሮይተርስ፣ መስከረም 28, 2015)። የኤርትራ መከላከያ ሰራዊትም በዚህ ሳምንት “በትግራይ ሰሜናዊ ምስራቅ ራማ፣ ዛላምበሳ እና ጸሮና ከተሞች” ላይ “ሰፋ ያለ ጥቃት” ከፍቷል (ኤፒ ኒውስ፣ መስከረም 30, 2015; ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 30, 2015)።
መስከረም 22 ቀን ትህነግ/ህወሓት “ታክቲካል ጂኦግራፊያዊ ማስተካከያ ለማድረግ” ኃይሉን ከሰሜን ወሎ ዞን ማስወጣቱን ያሳወቀ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ኃይሉን እንደገና ወደ ዞኑ ሊያስገባ እደሚችል አሳውቋል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 23, 2015)። ቡድኑ ወደ ዞኑ የገባው ነሐሴ 18, 2014 በትህነግ/ህወሓት እና በፌዴራል መንግስት ኃይሎች መካከል ዳግም በተቀሰቀሰበት ወቅት ነበር። ነገር ግን ሌሎች ዘገባዎች እና አንዳንድ የአካባቢው እማኞች የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ከዚህ አካባቢ በመንግስት ኃይሎች ተገፍተው መውጣታቸውን ይናገራሉ (ኢኤምኤስ.፣ መስከረም 23, 2015፤ ኢኤምኤስ፣ መስከረም 24, 2015)። ይህን ተከትሎ የመንግስት ኃይል የቆቦ ከተማን በኋላም የራያ ቆቦን እና የጎቢዬ አከባቢዎችን ተቆጣጥረዋል።
በነሐሴ 18 በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት ሸሽተው የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች የመንግስት ኃይል እነዚህን አካባቢዎች እንደገና ሲቆጣጠሩ ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል። በዚህም ምክንያት ባለፈው ሳምንት ትህነግ/ህወሓት አካባቢውን ተቆጣጥሮ በቆየበት ወቅት የትህነግ/ህወሓት ኃይል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን፣ ዘረፋዎችን እና የንብረት ውድመትን የሚያሳዩ ዘገባዎች መውጣት ጅምረዋል (አል አይን፣ መስከረም 26, 2015፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 25, 2015፤ ኢኤምኤስ፣ መስከረም 25, 2015)። የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በቆቦ ከተማ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን እና ንብረታቸውን መዝረፋቸው ተዘግቧል (ዘ ጋርዲያን፣ መስከረም 30, 2015)። ጳጉሜ 4 2013 የትህነግ/ህወሓት ኃይል በዚሁ ከተማ በትንሹ 23 ሰላማዊ ሰዎች ገድለዋል (አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የካቲት 9, 2014)። በተጨማሪም የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በቆቦ ከተማ፣ አበርት፣ ዞበል ተራራ እና ሌሎች አካባቢው በሚገኙ ቀበሌዎች ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን መሳሪያ ይዘዋል በሚል እና ለመንግስት ይሰልላሉ በሚል አፈነው መውሰዳቸው ተነግሯል (አል አይን፣ መስከረም 26, 2015)።
በመስከረም ወር የመጨረሻው ሳምንት ላይ የአፍሪካ ኅብረት ትህነግ/ህወሓት እና የፌዴራል መንግሥትን በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በሆኑት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የጠቢባን ፓናል አባል ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ንጉካ መሪነት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የሰላም ድርድር ላይ እንዲሳተፉ ጋብዟል (ኤዩ፣ መስከረም 26, 2015)። መስከረም 25 ቀን ሁለቱም ወገኖች ግብዣውን ተቀብለዋል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ መስከረም 25, 2015፣ ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 25, 2015)። ትህነግ/ህወሓት “ተጨማሪ የሚጋበዙ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች ወይም ዋስትና ሰጪዎች ይኖሩ እንደሆነ”፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚና እና የጉዞ ሎጂስቲክስ በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ጠይቋል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 25, 2015)። ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ ለመስከረም 28, 2015 የታቀደው የመጀመሪያው ዙር ድርድር “በሎጂስቲክስ ምክንያት” ዘግይቷል (ሮይተርስ፣ መስከረም 27, 2015)። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት መስከረም 27 ቀን ኡሁሩ ኬንያታ ሌላ ቀደም ተብሎ በተያዘ መርሐግብር ምክንያት በታቀደው የሰላም ድርድር ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ ለአፍሪካ ህብረት አሳውቀዋል። በተጨማሪም “የተጋበዙት ሁሉም አካላት የተግባቦት ደንብን ጨምሮ የውይይት መድረኩ አካሄድ” ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን የድርድሩ የመጀመሪያ አጀንዳ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል (ቢቢሲ፣ መስከረም 27, 2015)
በዚህ ወቅት ድርድሩ መቼ እንደሚካሄድ ግልፅ አይደለም። በሰኔ ወር የፌዴራል መንግስት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የሰላም ኮሚቴ ሾሟል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 20, 2015)። መስከረም 1 ቀን ትህነግ/ህወሓት ጌታቸው ረዳ እና ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ትህነግ/ህወሓትን ወክለው የድርድር ቡድን አካል እንደሚሆኑ አመልክቷል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 1, 2015)።
ሁለቱ ወገኖች ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር ላይ በአምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም ስለ ምዕራብ ትግራይ ዞን፣ የባንክና የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች፣ የትግራይ መገንጠል፣ የትግራይ ያልሆኑ ኃይሎች መውጣት እና የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች እና የትህነግ/ህወሓት ሊኖራቸው ሰለሚችለው ሚና ላይ ሊወያዩ ይችላሉ። (በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015ን ይመልከቱ)። የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እስኪደረስ ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ የመቀጠል እድሉ ከፍተኛ ነው።
በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለያዩ የፖለቲካ አለመረጋጋት ኩነቶች ተስተውለዋል። የኦሮሚያ ክልል በአገሪቱ እጅግ ያልተረጋጋ ሁለተኛ ክልል ሆኖ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ወለጋ ዞን በባቦ ጋምቤላ ወረዳ እና በጉጂ ዞን ውስጥ ባልታወቁ ስፍራዎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች ተዋግተዋል። በክልሉ ኦነግ-ሸኔ፣ የመንግስት ኃይል፣ ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን እና የሶማሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ አምስት ጥቃቶች ተፈጽመዋል። መስከረም 23 ቀን በባሌ ዞን ጉራ ዳሞሌ ወረዳ በሃብሮና ቀበሌ የሶማሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍተው ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎችን ገድለዋል። በጥቃቱ ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ለመሰደድ ተገደዋል። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ባለፈው ሳምንት ቀጥሏል። መስከረም 26 ቀን በአሙሩ ወረዳ ዋሊ ሉኩማ ቀበሌ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ አምስት ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል። የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ለመሰደድ ተገደዋል። ቡድኑ የሰላማዊ ሰዎች ቤቶችን በማውደም ወደ 80 የሚጠጉ የቀንድ ከብቶችን ዘርፏል (በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሰላለው ውጊያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለደረሰው ጥቃት የበለጠ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: መስከረም 14-20, 2015ን ይመልከቱ)።
በተጨማሪም መስከረም 22 ቀን በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሀራ ከተማ መተሀራ አባደር ሁለተኛ ካምፕ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል። በመስከረም 20 ቀን በተመሳሳይ ቦታ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሟል። በእነዚህ ሁለት ጥቃቶች 12 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን ምስክሮች ለዚህ ጥቃት ኦነግ-ሸኔን ጥፈተኛ አድርገዋል (ኢሳት፣ መስከረም 22, 2015)። ከአንድ ቀን በኋላ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳ በርጋ ወረዳ መቆዳ የሚገኘው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኞችን አሳፍሮ በነበረ አውቶቡስ ላይ ኦነግ-ሸኔ ባደረሰው ጥቃት በትንሹ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ 16 ሰዎች ቆስለዋል። ከአምስት ቀናት በፊት መስከረም 18 ቀን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የሲሚንቶ ፋብሪካውን ስራ አስኪያጅ እና ሹፌራቸውን ወደ ፋብሪካው ሲጓዙ እዚያው ወረዳ ገጢራ አካባቢ አፍነው ወስደዋል።ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ሸዋ ዞን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እስደሆነ የተገመተ የመንግስት ኃይል አንድ ሰላማዊ ሰው ተኩሰው መግደላቸውም ተነግሯል።
በጋምቤላ ክልል መስከረም 25 ቀን በዋና ከተማዋ በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ፅህፈት ቤትን እና ሰራተኞቹን በማጥቃት በክልሉ የሚገኘውን ጽህፈት ቤት እንዘጋዋለን በማለት አስፈራርተዋል። ይህ ክስተት በሰኔ ወር በመንግስት ኃይል እና በኦነግ-ሸኔ እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል በተካሄደው ውጊያ ወቅት እና ከውጊያው በኃላ የክልሉ ኃይል፣ ኦነግ-ሸኔ እና ጋነግ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈፀሙትን ግድያ አስመልክቶ የመስከረም 18 የኢሰመኮ ሪፖርት ከወጣ በኋላ ነው ነበር (በጋምቤላ ክልል ስለነበረው ውጊያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 4 እስከ 10, 2014 ይመልከቱ)። ከዚህ በተጨማሪም በመስከረም 26 ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በኑዌር ዞን ማኩዬ ወረዳ በሎንግጆክ ቀበሌ ተኩስ ከፍተው ሦስት ሰዎችን ገድለዋል። ቡድኑ የ11 አመት ልጅንም አፍኖ ውስዷል።
በመጨረሻም የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እንደዘገበው መስከረም 25 ቀን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከአልሸባብ ታጣቂዎች ጋር በሶማሊያ በባኮ ክልል ዬድ ወረዳ በቁዳዓሌ መንደር በነበረ ውጊያ 11 የአልሸባብ ከፍተኛ አመራሮችን እና 70 የቡድኑ አባላትን ጨምሮ 81 የአልሸባብ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታውቋል። እንደ ዘገባው ከሆነ የክልሉ ልዩ ኃይል ይህን ዘመቻ ያደረጋው የአልሸባብ ታጣቂዎች ኢትዮጵያን እንደገና ለማጥቃት በዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው (የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ መስከረም 26, 2015)። በሐምሌ 2014 አልሸባብ እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በሶማሌ እና በኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ ከሚገኙት ዮድ እና አቶ አካባቢዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ለቀናት የዘለቀ ውጊያ አድርገዋል (ስለነዚህ ኩነቶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 9-15, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 16-22, 2014 ይመልከቱ)።