በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ጥቅምት 4, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,477
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,015
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,857
በቁጥር: ኢትዮጵያ, መስከረም 28-ጥቅምት 4, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 30
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 90
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 50
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት ጦርነት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልልም መጠነኛ አለመረጋጋት ቀጥሏል። መስከረም 10 ቀን የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይል እና ከትህነግ/ህወሓት ጋር ግኑኝነት ያላቸው የሳምሪ ወጣት ታጣቂዎች፣ የቅማንት እና የጉሙዝ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ከአማራ ታጣቂዎች ጋር በአማራ ክልል መተማ ወረዳ ጀበረስ ካራ አካባቢ እና በረ እና ሻሮ ተራሮች ተዋግተዋል። የመንግስት ኃይሎች በእነዚህ አካባቢዎች በትህነግ/ህወሓት እና የትህነግ/ህወሓት አጋር ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ አንዳንድ ምሽጎችን እንደገና መቆጣጠሩን ተነግሯል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ ቃሊም እና ወርቄ ላይ በትህነግ/ህወሓት እንደተቀበሩ የሚገመት ሁለት ፈንጂዎች ፈንድተዋል። በቃሊም አንድ ሰው ሲገደል አራት ሰዎች ደግሞ የቆሰሉ ሲሆን በወርቄ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰላማዊ ሰዎች ቆስለዋል።
በትግራይ ክልል ውጊያዎች ሪፖርት መደረጋቸው ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ደደቢት እና አዲያቦ አካባቢ የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ከኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተዋግተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በተጨማሪም ትህነግ/ህወሓት በመስከረም 29 ቀን የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምስራቅ ትግራይ “ራማ፣ ዛላምበሳ እና ጸሮና ግንባሮች” ላይ “ሰፋ ያለ ጥቃት” እንደከፈተ ገልጿል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 30, 2015)። በደቡብ ትግራይ ዞን በራያ አላማጣ በመረዋ፣ ዋጃ፣ ሰሚዛ፣ ጀመዶ፣ መሀርማር እና ማህጎ አካባቢዎች የመንግስት ኃይሎች ከትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ጋር ከተዋጉ በኃላ እነዚህን አካባቢዎች መቆጣጠራቸውንም ተነግሯል።
ባለፈው ሳምንት መስከረም 29 ቀን ትህነግ/ህወሓት በትግራይ የሚኖሩ በሙሉ በጦርነቱ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል (ቢቢሲ አማርኛ፣ መስከረም 30, 2015)። በዚህ ሳምንት ጥቅምት 7 ቀን መንግስት “ትህነግ/ህወሓትን በሚደግፉ ጠላት የውጭ አካላት የኢትዮጵያን የአየር ክልል በተደጋጋሚ እና በከባዱ በመጣሳቸው” ምክንያት “የመከላከል እርምጃ” እየወሰደ መሆኑን እና “የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም አየር ማረፊያዎች እና ሌሎች የፌዴራል ተቋማትን ወዲያውኑ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው” ብሏል (ትዊተር @ኤፍዲአርኢስርቪአ፣ ጥቅምት 7, 2015)። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ቢያቀርቡም እነዚህ መግለጫዎች ግን ለጊዜው በአካባቢው ውጊያ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠቁማሉ። በተጨማሪም የመንግስት መግለጫ በቅርቡ የፌዴራል መንግስት የትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌን ለመቆጣጠር ያለውን ፍላጎት ያሳያል። መንግስት ከህዳር እስከ ታህሳስ 2014 በትህነግ/ህወሓት ላይ ባደረገው የመከላከል ዘመቻ መንግስት መቀሌን ለመያዝ ፍላጎት እንደሌለው ነገር ግን የትህነግ/ህወሓት ኃይሎችን ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች ለማስወጣት ብቻ ፍላጎት እንዳለው ገልጿ ነበር (ሮይተርስ፣ ታህሳስ 15, 2014)።
በኢትዮጵያ እየቀጠለ ያለው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጫና አሳድሯል። በመስከረም 30 በወጣው የዩኤን የውስጥ መግለጫ መሰረት ነሐሴ 18 ቀን በጀመረው አዲስ ዙር ውጊያ ምክንያት ወደ 470,000 የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 6, 2015)። በተጨማሪም ጥቅምት 4 ቀን በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ሽሬ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በደረሰ የአየር ጥቃት አንድ የአለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ (ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ/ አይአርሲ) ሠራተኛ እና ሌሎች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሌላ አይአርሲ ሠራተኛ እና ሌሎች ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል (አይአርሲ፣ ጥቅምት 5, 2015)። በደቡብ ትግራይ ዞን ኮረምና አላማጣ ከተሞች የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን መግደላቸውን እና ማፈናቸውን ተነግሯል።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተስነዘሩ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል። በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና ወረዳ በጉቲን ቀበሌ እና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ አቅራቢያ ጎዪ መንደር ውስጥ የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሁለት ጥቃቶች መፈፀማቸው ተነግሯል። በጉቲን አምስት ሰዎች መገደላቸውን እና ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም በጎዪ ሁለት ወጣቶች መገደላቸው ተነግሯል። በተጨማሪም በጊዳ አያና ወረዳ ሀሮ አያና ቀበሌ የአማራ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ተዋግተዋል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሦስት ወረዳዎችን – ሊበን ጩቃላ፣ ዱግዳ እና ቦራ ወረዳዎችን – በቁጥጥር ስር ማዋሉን ባለፈው ሳምንት ተዘግቧል።
ጥቅምት 2 ቀን በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ በሚገኘው ሳንሱሲ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ የኦነግ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተመትተው መገደላቸው ተነግሯል።
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ ግድያዎች እና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ ነው። ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ጉጂ ዞን በቡሌ ሆራ ወረዳ የኦነግ-ሸኔ አባላት ናቸው በሚል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ስምንት ሰዎችን በጥይት መግደላቸው ተዘግቧል። በተጨማሪም መስከረም 28 ቀን በምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ ቦኩ ኒሶ ቀበሌ ውስጥ አምስት ቤቶችን ባለቤቶቹን ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሆኑ የተጠረጠሩ የመንግስት ኃይሎች አቃጥለዋል።
በቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ጥቅምት 1 ቀን በመተከል ዞን በማንዱራ ወረዳ አጀንታ እና ቱኒ ዳቢሻ ቀበሌዎች መከከል በሚገኝ ስፍራ የጉሙዝ ብሄረሰብ ታጣቂዎች የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪን እና አስተዳዳሪውን ሹፌርና ከአስተዳዳሪው ጋር ለሌላ የፀጥታ ስምሪት ሲጓዙ የነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ ሰባት ሰዎችን ገድለዋል። በተጨማሪም ጥቅምት 3 ቀን ይኸው የታጠቀ ቡድን በማንዱራ ወረዳ ቱኒ ዳቢሻ ቀበሌ በጉሙዝ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ባልታወቀ ምክንያት ጥቃት አድርሰዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት ክልሉ በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ነበር።
በመጨረሻም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል። የፈተና ወረቀት ስርቆት እና ኩረጃን ለመከላከል ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ ፈተና በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄደ ሲሆን ፈታኞች ወደ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ተወስደዋል። በአማራ ክልል ወደ 12,000 የሚጠጉ ተማሪዎች ከመፈተኛ ክፍሎች ወጥተው ፈተናውን አንወስድም ማለታቸው ተነግሯል። በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን በደብረታቦር ከተማ ጥቅምት 1 ቀን በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ለፈተና ከተቀመጡት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 7,150ዎቹ ፈተናውን አንወስድም ብለው ከመፈተኛ ክፍሎቹ ወጥተው ፈታኞች እና የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። ባለሥልጣናቱ ግርግሩ የተፈጠረው “በሌሎች አካባቢዎች ፈተናው ተስርቋል” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው የተሰራጨ “የውሸት ዜና” ነው (ትክቫህ ኢትዮጵያ፣ ጥቅምት 1, 2015)። ይህንን ሁከት ለማስቆም የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ከገቡ በኃላ የአንድ ተማሪ ህይወት ሲያልፍ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የፀጥታ አባላት ቆስለዋል።