በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ጥቅምት 11, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,517
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,108
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,913
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከጥቅምት 5-11, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 22
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 79
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 48
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን በሽሬ፣ በደቡብ ትግራይ ዞን በአላማጣ፣ ኮረም፣ ቢሶበር፣ መኾኒ እና ራያ ባላ በሚገኘው ጉባ ተራራ ላይ በመንግስት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች መካከል ውጊያዎች ተዘግበዋል። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የመንግስት ኃይሎች ሽሬን የተቆጣጠሩ ሲሆን በመቀጠልም አላማጣ፣ ኮረም፣ ቢሶበር እና መኾኒን ተቆጣጥረዋል። የሽሬ ከተማን መንግስት መልሶ መቆጣጠሩ ለወታደሮቹ እንደ አክሱም እና አድዋ ያሉ ከተሞችን ከክልሉ ርዕሰ መዲና መቀሌ ጋር የሚያገናኘው ቢ30 አውራ ጎዳናን ስለሚያገኝ ለኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ስልታዊ ጠቀሜታ አለው።
በዚህ ሳምንት ጥቅምት 15, 2015 በጀመረው እና እስከ ጥቅምት 20, 2015 እንደሚቆይ በሚጠበቀው በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትህነግ/ህወሓት ተወካዮች ደቡብ አፍሪካ ገብተዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው የሰላም ድርድር በመጀመሪያ በመስከረም 28, 2015 ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም “በሎጂስቲክስ ምክንያቶች” ግን እንዲዘገይ ተደርጓል (ሮይተርስ፣ መስከረም 27, 2015)። እየተካሄደ ስላለው የሰላም ድርድር ብዙ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እየተነጋገሩ እንደሆነ መገመት ግን ይቻላል። በተጨማሪም እነዚህ ወገኖች ግጭቱ እንዲራዘም ምክንያት በሆኑ ሌሎች አምስት ዋና ጉዳዮች ማለትም ስለ ምዕራብ ትግራይ ዞን፣ የባንክና የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በትግራይ ስለማስጀመር፣ የትግራይ የመገንጠል መብት፣ የትግራይ ያልሆኑ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እና የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች እና የትህነግ/ህወሓት ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይገመታል (ስለ እነዚህ ጉዳዮች የበለጠ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ይመልከቱ)። የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ መሳተፉን የሚያሳይ ማስረጃ ቢኖርም ኤርትራ ግን የሰላም ድርድሩ ተሳታፊ አይደለችም። በዚህ ዙር የሰላም ድርድር የተመድ፣ የዩኤስ እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ተወካዮች በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው (ኤዩ፣ ጥቅምት 15, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎችና የአየር ድብደባዎች ተዘግበዋል። ባለፈው ሳምንት በመንግስት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል አራት የውጊያ ኩነቶች በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ጊዳራ ቀበሌ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ በጎጆ ከተማ እና በሜታ ዋልቂጤ ወረዳ ካሬ ሄቶ እና ጎሮ ማኮ ቀበሌዎች ተዘግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ባልተለመደ መልኩ በርካታ የአየር ድብደባዎች በኦሮሚያ ተዘግቧል። ጥቅምት 9 ቀን የኢትዮጵያ አየር ሃይል በምዕራብ ሸዋ ዞን በሜታ ዋልቂጤ እና ጮቢ ወረዳዎች እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ኑኑ ቁምባ ወረዳ በኦነግ-ሸኔ ላይ የሰው አልባ አውሮፕላን አየር ጥቃቶች ማድረጉ ተዘግቧል። ቢቢሲ አማርኛ ያነጋገራቸው እማኞች እንደገለፁት አንደኛው ጥቃት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ የኦነግ-ሸኔ ወታደሮች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያነጣጠረ ነው። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የኦነግ-ሸኔ አባላትን እና ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 70 ሰዎች መሞታቸው እና 120 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 15, 2015)። ተጨማሪ የአየር ድብደባዎች እሁድ ጥቅምት 13 ቀን 2015 የተፈፀሙ ሲሆን፣ ይህም በሚቀጥለው ሳምንት ሳምንታዊ ዘገባ የሚሸፈን ይሆናል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ስምንት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ኩነቶች ውስጥ ሦስቱ በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ እና በሰሜን ሸዋ ዞን በውጫሌ ወረዳ በመንግስት ኃይሎች የተፈፀሙ ሲሆን በአጠቃላይ አምስት ሰዎች በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል። በመንዲ ከተማ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች የኦነግ-ሸኔ አባላት ናቸው ተብለው የተከሰሱ ሲሆን የተቀሩት ሁለቱ ጥቃቶች ምክንያቱ ግን አልታወቀም። የተቀሩት አምስት ጥቃቶች በአማራ ብሔር ታጣቂዎች የተፈፀመ ሲሆን በአጠቃላይ ከ43 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል። ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈፀሙ ሲሆን አንድ ጥቃት የተፈፀመው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነው።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አለመረጋጋት ቀጥሏል። ጥቅምት 5 ቀን በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ኤጄንታ፣ ወለምሻ ማያ እና ኢፍታውን ቀበሌዎች ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የጉሙዝ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከ”ጉሙዝ አማፂ ቡድን” ጋር ተዋግተዋል (ኢኤምኤስ፣ ጥቅምት 8, 2015)። ይህ ውጊያ ጥቅምት 1 ቀን ላይ የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪ እና ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የተከሰተ ነው (ስለዚህ ኩነት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: መስከረም 28-ጥቅምት 4, 2015 ይመልከቱ)።
በመጨረሻም ጥቅምት 9 ቀን የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መንግስት እና የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) በአሶሳ ከተማ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። የጉህዴን ፓርቲ ሊቀመንበር እና ዘጠኝ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 300 የፓርቲው አባላት ከግልገል በለስ ማረሚያ ቤት የተፈቱት በመጋቢት 2014 ላይ ነበር። እነዚህ የፓርቲው አባላት የተፈቱት የካማሺ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ለውይይት ከተቀመጡ በኋላ ነው። እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት በዞኑ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ የታሰሩ አባላቶቻቸው እንዲፈቱ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበው ነበር። የጉህዴን አባላትም እጃቸውን ሰጥተው ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ተስማምተው ነበር። በመሆኑም በመጋቢት 10 ቀን 2014 የክልሉ መንግስት እና የጉህዴን የፖለቲካ እና የትጥቅ ክንፍ አመራሮች የሰላም እና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት በዞኑ አድርገው ነበር (ስለካማሺ ባህላዊ የሰላም እና ዕርቅ ሥነ ሥርዓት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 3, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014 ይመልከቱ)። ይሁን እንጂ ባህላዊውን የሰላምና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት ተከትሎ አንዳንድ የጉህዴን አባላት ትጥቅ አንፈታም በማለታቸው በመንግስት እና በቡድኑ መካከል ከሰኔ 2014 ጀምሮ ውጥረት ሰፍኖ ነበር (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 20 እስከ 26, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 ይመልከቱ)።