በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ጥቅምት 25, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,569
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,329
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8,987
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከጥቅምት 19-25, 20152 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 25
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 62
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 7
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በኢፒኦ የዳታ ፋይል እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከ10 ቀናት ድርድር በኋላ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 23 ቀን የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ለዘለቄታዊ ሰላም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ 15 አንቀጾችን ያቀፈ ነው። ሁለቱ አካላት ሌሎች ጉዳዮች ጨምሮ በቋሚነት ተኩስ ለማቆም፣ የትህነግ/ህወሓት ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ በክልሉ የፌዴራል መንግስት ስልጣንን ለማስመለስ፣ ክልላዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ “ሁሉን አካታች” የሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ለመመስረት፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት ለመመለስ እና በክልሉ ሰብአዊ እርዳታን ለማቀላጠፍ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 25 ቀን 2015)። በስምምነቱ አንቀፅ 6(መ) መሰረትም የስምምነቱን ትግበራ ለማስጀመር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ መከላከያ ኃይሎች ተበለው የሚታወቁት የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጥቅምት 25 ቀን በስልክ ከተነጋገሩ በኃላ ጥቅምት 28 ቀን በኬንያ ናይሮቢ በአካል ተገናኝተዋል (ቪኦኤ፣ ጥቅምት 28 ቀን 2015፤ ኢኤምኤስ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2015)።
ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ ምንም አይነት የፖለቲካ ግጭት አልተመዘገበም። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰላም ስምምነቱን የተቀበሉ ሲሆን አንዳንድ ዲያስፖራ የትግራይ ተወላጆች የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ትጥቅ መፍታት እንዳሳሰባቸው እና ኤርትራ በስምምነቱ ውስጥ ለምን በስም አልተጠቀሰችም በማለት ጥያቄ አቅርበዋል (ለምሳሌ እነዚህን ይመልከቱ ዩኤን ኒውስ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015፤ ፋይናሻል ታይምስ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015፤ የሩስያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015፤ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 25 ቀን 2015፣ የቱርክዬ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015)። በተመሳሳይ ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል ሲተዳደሩ የነበሩትን እንደ ወልቃይት ፀገዴ እና ራያ ያሉ አካባቢዎችን አስተዳደር በተመለከተ ስምምነቱ ወደ ትግራይ ክልል አሳልፎ እንደሚስጥ በመግለጽ የአማራ ብሔርተኞች ስምምነቱን ተቃውመዋል። ሆኖም ጥቅምት 24 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ ወልቃይት ፀገዴ አካባቢ ያሉ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እና የክልል አስተዳደር ጥያቄዎችን “በንግግር እና በሀገሪቱ ህግ” ለመፍታት ሁለቱ አካላት መስማማታቸውን አመላክተዋል (ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015)።
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች ማለትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መካከል የሚደረገው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል። ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ፣ ቂልጡ ካራ እና ዶንጎሮ አካባቢዎችን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ከተዋጋ በኃላ እነዚህን አካባቢዎች መቆጣጠሩ ተነግሯል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተፈፀሙ የሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ድብደባዎች በክልሉ የቀጠሉ ሲሆን በመና ሲቡ ወረዳ በዋማ ቶቤራ ቀበሌ በመንዲ ከተማ እና በቦጂ ድርመጂ በቢላ ከተማ በተፈፀሙ ሦስት የአየር ድብደባዎች ከ55 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በክልሉ ባለፈው ሳምንት የተመዘገቡት ሁሉም ጦርነቶች እና የሰው አልባ አውሮፕላን ድብደባዎች በምዕራብ ወለጋ ዞን ተከስተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ክልል በሌላ ስፍራዎች ባለፈው ሳምንት አራት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረ ጉራቻ ከተማ ምድረ ገነት ቅድስት ልደታ ማርያም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከገባ በኋላ አንድ ዲያቆን ገድሎ 11 አገልጋዮችን አግቷል። ከሁለት ቀናት በኋላ በአርሲ ዞን በጀጁ ወረዳ በሁሩታ ዶሬ ቀበሌ ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቂ ቡድን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ አራት ሰዎችን መግደሉ ተነግሯል። የእነዚህ ጥቃቶች መንስኤዎች አልታወቁም። የተቀሩት ሁለት ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል የተፈፀሙ ሲሆን በሰሜን ሸዋ ዞን ዋረ ጃርሶ ወረዳ ቱሉ ሚልኪ በተባለ ቦታ አንድ ሰው ሲገድሉ ሌላ ሰው አቁስለዋል፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ስሪቲ ቀበሌ ላይ አንድ ሰው መግደላቸውን የተገለጸ ሲሆን ተጎጂዎቹ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው ነበር።
በመጨረሻም በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የባምቢስ ወረዳ አስተዳደር በኦነግ-ሸኔ እና በፌዴራል ፖሊስና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መካከል በአጎራባች ኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤንጉዋ አካባቢ መዋጋታቸውን ተከትሎ በባምባሲ ወረዳ የምሽት የሰዓት እላፊ መውጣቱን አስታውቋል። አስተዳደሩ ኦነግ-ሸኔ በወረዳው ተመሳሳይ ጥቃት ለመሰንዘር ማቀዱን አስተማማኝ መረጃ እንዳለው ገልጿል (የኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015)።