በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ህዳር 9, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,631
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,506
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 9,128
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከህዳር 3-9, 20152 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 24
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 99
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 70
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በኢፒኦ የዳታ ፋይል እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከስድስት ቀናት ውይይት በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና – የትግራይ መከላከያ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) በመባል የሚታወቁት – የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች ሀላፊዎች ህዳር 3 ቀን የከፍተኛ አዛዦች ለዘለቄታዊ ሰላም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ የማድረግ መግለጫ በኬንያ ናይሮቢ ተፈራርመዋል። በዚህ መግለጫ ውስጥ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ጨምሮ ሁለቱ ወገኖች በጥቅምት ወር ላይ በደቡብ አፍሪካ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ የፍኖተ ካርታ እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተስማምተዋል። ትጥቅ ከማስፈታት እና ተዋጊዎችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ ሂደት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት የክትትልና ማረጋገጫ ቡድን እንዲያቋቋም ስምምነት ተደርሷል። በዚህ መግለጫ መሠረት ከህዳር 6 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ለሁለቱ ወገኖች ኃይሎች ማብራሪያ ይሰጣል። ይህ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ባሉት አራት ቀናት ውስጥ ቲዲኤፍ በተመረጡ አራት ቦታዎች ላይ ትጥቁን ይፈታል። በስምምነቱ ላይ ኤርትራ በስም ያልተጠቀሰች ቢሆንም አንቀጽ 2(መ) እደሚያብራራው የከባድ የጦር መሣሪያዎችን ትጥቅ ማስፈታት የሚከናወነው “የውጭና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል በሚወጡበት” በተመሳሳይ ጊዜ ነው (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ህዳር 3, 2015)።
በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ላይ አንዳንድ ስጋቶች አሉ። የትህነግ/ህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ እና የትግራይ ክልል መንግስት በስምምነቱ ላይ እርምት እንዲደረጉ በርካታ መግለጫዎችን አውጥተዋል (ትግራይ ቲቪ፣ ህዳር 3, 2015፣ ትግራይ ቲቪ፣ ህዳር 4, 2015)። ሁሉም የተጠየቁት እርማቶች የድርድር ቡድኑ የትህነግ/ህወሓት ተወካዮች ሳይሆን “የትግራይ መንግስት” ተወካዮች ናቸው የሚለውን አቋም እንዲያብራሩ ጠይቀዋል። ይህ ጥያቄ አከራካሪ ነው ምክንያቱም በፌዴራል መንግስቱ ህገ-ወጥ ነው በተባለው ምርጫ ትህነግ/ህወሓት የትግራይ ክልል መንግስት ሆኖ ተመረጦ ነበር (ሮይተርስ፣ መስከረም 1, 2013)።
በተጠየቀው እርምት ላይ ባለሥልጣናቱ በመጀመሪያ ትህነግ/ህወሓት ምንም አይነት ተወካይ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳልላከ ይልቁንም የተላኩት ተወካዮች “በትግራይ መንግስት” እንደተላኩ ተናግረዋል። ሁለተኛ መግለጫዎቹ ትህነግ/ህወሓት የታጠቀ ኃይል እንደሌለው ግልጽ ለማድረግ ያለሙ ነበሩ። በእነዚህ መግለጫዎች መሰረት አሁን ያለው የትግራይ ኃይል የተቋቋመው የትግራይ ክልልን ለመከላከል ነው። ሦስተኛ “የትግራይ መንግስት የሚፈርሰው በመረጠው የትግራይ ተወላጆች ብቻ እንጂ በሰላም ስምምነት እንደማይፈርስ” ጠቁመዋል። የትህነግ/ህወሓት ቃል አቀባይ እና የትህነግ/ህወሓት ልኡካን ቡድን መሪ ጌታቸው ረዳም “የትግራይ መንግስት” ተወካዮች ሆነው ለመደራደር አቅደው እንደነበር ጠቁመው የአፍሪካ ህብረትም ሆነ “ሌሎች” ጥያቄያቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ጠቁመዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 6, 2015)።
መተላለፊያ መንገዶች በሚገኙበት አካባቢዎች ግጭቶች በመቀነሳቸው ምክንያት ከሰኔ 2013 በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዳር 7 ቀን የዓለም ምግብ ፕሮግራም 15 የጭነት መኪናዎች በአዲ አርቃይ በኩል አቋርጠው በጎንደር-ማይ ፀብሪ መንገድ ወደ ትግራይ ክልል መድረስ ችለዋል (ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ህዳር 8, 2015)። ስድስት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይሲአርሲ) የጭነት መኪናዎችም ህዳር 11 ቀን መቀሌ ገብተዋል (አይሲአርሲ ኢትዮጵያ፣ ህዳር 12, 2015)። የኢትዮጵያ መንግስት የተበላሹ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን በፍጥነት እየሰራ ሲሆን የጋሸና-አላማጣ ኤሌክትሪክ መስመር ሙሉ ጥገና ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁን አስታውቋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 12 , 2015)።
የኦሮሚያ ክልል በአገሪቱ ካሉ ክልሎች በጣም ያልተረጋጋ ክልል ሆኖ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በክልሉ 11 የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ 11 ኩነቶች ውስጥ 10ሩ የጦርነት ኩነቶች የተካሄዱት በመንግስት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል ነው። እነዚህ ክስተቶች በሰሜን ሸዋ ዞን ጉንዶ መስቀል ከተማ እና ዳዪ ቀበሌ፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን ዱግዳ ዳዋ እና ሱሮ በርጉዳ ወረዳዎች፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋማ ሀጋሎ ወረዳ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ወዴሳ እና በምዕራብ ወለጋ ዞን በጊ ወረዳ ተከስተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ የአማራ እና የፋኖ ሚሊሻዎች ከመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጋር የተዋጉ ሲሆን የመንግስት የፀጥታ አባላትን ጨምሮ ከ20 ያላነሱ ሰዎችን መግደላቸው ተነግሯል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ከተማ በኦነግ-ሸኔ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ ሁለት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችን አድርጓል። በእነዚህ ጥቃቶች ከ40 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ኦነግ-ሸኔ በጉጂ ዞን ጉሚ ኤልዳሎ፣ ሊበን፣ ጎራ ዶዶላ፣ ዋዴራ፣ ሰባ ቦሬ እና አዶላ ራዴ ወረዳዎችን፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን መልካ ሶዳ ወረዳን፣ በቦረና ዞን አሬሮ ወረዳን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠሩም ተነግሯል።
በተጨማሪም በክልሉ በተለያዩ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ስምንት የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ስምንት ጥቃቶች መካከል ሦስቱ በመንግስት ኃይሎች – በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት – በምስራቅ ወለጋ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች የተፈጸሙ ናቸው። ኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሁለት ጥቃቶችን በሰሜን እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ፈጽሟል። የአማራ እና የፋኖ ሚሊሻዎች ከህዳር 6 እስከ 8 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሊቦ ከተማ ከ12 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል።
በአማራ ክልል ህዳር 3 ቀን በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ የቅማንት ታጣቂ ቡድን የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ በማስቆም 15 ሰላማዊ ሰዎችን አፍኖ ወሰዷል። አውቶቢሱ ከሽንፋ ወደ ገንደ ወሃ እየተጓዘ ነበር።
በመጨረሻም ህዳር 9 ቀን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ላይ በቅርቡ በመንግስት የቀረበውን ‘ክላስተርን መሰረት ያደረገ አስተዳደራዊ መዋቅር’ በመቃወም ወጣቶች ጎማ አቃጥለው ዋናውን መንገድ ዘግተዋል። ሰልፈኞቹ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ የወረወሩ ሲሆን ሰልፈኞቹን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች ጥይት ወደ ላይ ተኩሰዋል።