በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ህዳር 16, 20151 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 2,654
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 15,102
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 5,982
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከህዳር 10-16, 20152 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 21
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 110
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 37
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በኢፒኦ የዳታ ፋይል እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኢትዮጵያ ካሉ ክልሎች ትልቁ ክልል የሆነው የኦሮሚያ ክልል እጅግ ያልተረጋጋ ክልል ሆኖ ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አለማረጋጋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ናቸው። ባለፈው ሳምንት በእነዚህ አራት ዞኖች ውስጥ በተለያዩ አካላት መካከል የተደረጉ 13 የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና የቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በጉጂ ዞን በአጋ ዋዩ ወረዳ፣ ቦሬ ወረዳ እና ኤጀርሳ እንዲሁም በምዕራብ ጉጂ ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ እና ደዳ ኦዳ ቀበሌ ላይ ተዋግቷል። በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በምዕራብ ወለጋ ዞን በነጆ፣ መንዲ፣ ቂልጡ ካራ፣ ጊምቢ እና ቶሌ አካባቢዎች ላይ መዋጋታቸው ተዘግቧል። እነዚህን አካባቢዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደገና መቆጣጠሩ ተነግሯል። የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጊ ወረዳ ሎፒ እና ሃሩ ወረዳ ሃሩ ከተማ ላይ በኦነግ-ሸኔ ላይ ያነጣጠረ ሶስት የሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ጥቃት ፈፅሟል። በምስራቅ ወለጋ ዞን ሰለተከሰቱት ኩነቶች በሚቀጥለው ክፍል በዝርዝር ቀርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው። ባለፈው ሳምንት አምስት እንደዚህ ያሉ ኩነቶች በክልሉ ውስጥ ተመዝግበዋል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባላት እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሁለት ጥቃቶችን ፈጽመዋል። ህዳር 10 ቀን በምዕራብ ሸዋ ዞን ዲኪ እና ቱሌ ቀበሌዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ሶስት ወጣቶችን በጥይት ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። ከቀናት በኋላም በምዕራብ ሸዋ ዞን በሜታ ወልቂጤ ወረዳ በላፍቶ ቤሎ አቅራቢያ በሚገኘው ቃሬ ሄቶ ቀበሌ የመንግስት ታጣቂዎች 21 ሰዎችን በጥይት መግደላቸው ተዘግቧል። ተጎጂዎቹ በሜታ ወልቂጤ ወረዳ የሚገኙ እስረኞች ነበሩ። በቃሬ ሄቶ ቀበሌ ለተፈፀመው ግድያ ምክንያቱ አልታወቀም።
የተቀሩት ሶስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች የተፈፀሙት በኦነግ-ሸኔ ነው። ህዳር 12 ቀን ኦነግ-ሸኔ በምስራቅ ሸዋ ዞን አሪቦን አካባቢ ሹፌር እና ረዳቱን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወንዶችን ከአዳማ ወደ መተሃራ በ‘ዶልፊን’ ሚኒባስ ሲጓዙ አስቁመው አፍነው ወስደዋቸዋል። በተመሳሳይ እለት የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በአርሲ ዞን በጀጁ ወረዳ ተሂላ በተባለው አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አንድ አባትና ልጅን ጨምሮ አምስት ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸው ተነግሯል። ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ ጨሃ ኬሳ በተባለ አካባቢ ኦነግ-ሸኔ ሦስት ሰዎችን መግደሉ፣ ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ማቁሰሉን እና 18 ሰዎችን አፍኖ መውሰዱም ተነግሯል።
በትግራይ ክልል የትግራይ መከላከያ ሰራዊት (ቲዲኤፍ) በመባል የሚታወቀው የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይል ሀላፊ ጄነራል ታደሰ ወረደ ባለፈው ሳምንት እንደገለፁት በኬንያ ናይሮቢ በተፈረመው መግለጫ መሰረት የቲዲኤፍ አዛዦች ለቲዲኤፍ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ ማብራሪያ ማድረጋቸውን እና የቲዲኤፍ ኃይሎች ወደ ተመረጡ ቦታዎች መግባት መጀመራቸውን እና “ትጥቅ የመፍታት እንቅስቃሴ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ እንደሚቀጥል” ጠቁመዋል (ትግራይ ቲቪ፣ ህዳር 13, 2015)። ሆኖም እስከ አሁን ድረስ ቲዲኤፍ ትጥቅ መፍታት መጀመሩ ወይም አለመጀመሩ እስካሁን ግልጽ አይደለም። በትህነግ/ህወሓት ውስጥ የሰላም ስምምነቱን የማይቀበሉ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይሎች እንዳሉ እና ይህ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሰዋል። የትህነግ/ህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ሃርድቶክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎች ካልተፈቱ ቲዲኤፍን ትጥቅ መስፈታት ላይቻል እንደሚችል ጠቁመዋል (ቢቢሲ፣ ህዳር 15, 2015)። ከዚህም በተጨማሪ ትህነግ/ህወሓት ኤርትራ በክልሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት አድርጋለች በማለት መክሰሱን ቀጥሏል። ሆኖም ይህ ክስ በሌሎች ገለልተኛ ምንጮች አልተረጋገጠም። ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ድርድር ቡድን መሪ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ድርድር ቡድን አባል የነበሩት የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ-ንጉካ የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለመገምገም ከትህነግ/ህወሓት ባለስልጣናት ጋር በትግራይ ክልል መቀሌ ተገናኝተዋል (ቦርከና፣ ህዳር 15, 2015፣ ትግራይ ቲቪ፣ ህዳር 15, 2015)።
በመጨረሻም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ “የጉራጌ ዞን እንደ ክልል ዕውቅና እንዲሰጠው በቀረበው ጥያቄ ምክንያት የዞኑን የፀጥታ ጉዳዮች በመደበኛ ሂደት ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ በመሆኑ” ከህዳር 15 ጀምሮ የጉራጌ ዞን በፌዴራል ፖሊስና በክልሉ ልዩ ኃይል በሚመሩት በኮማንድ ፖስት ስር እንደሚተዳደር ገልፀዋል (ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኤጀንሲ፣ ህዳር 15, 2015)። ከዚሁ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው እስካሁን በጉራጌ ዞን ሊካሄድ የታቀደውን የክላስተር አደረጃጀት በመቃወም እና ዞኑ በክልልነት እንዲታወቅ ተደራጅተው የጠየቁ እና ተሳትፈዋል የተባሉ ከ70 በላይ ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሲያሳይ ሌሎች ምንጮች ደግሞ ከ200 በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን ጠቁመዋል (ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኤጀንሲ፣ ህዳር 15, 2015፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 14, 2015)። ይህ ውሳኔ እና እስር መንግስት በቅርቡ ያቀደውን ‘ክላስተር ላይ የተመሰረተ የአስተዳደር መዋቅር’ በመቃወም በህዳር 9 ቀን ወጣቶች በጉራጌ ወልቂጤ ከተማ ላይ ጎማ በማቃጠል ዋናውን መንገድ ከዘጉ በኋላ የተፈፀመ ነው። ሰልፈኞቹ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ የወረወሩ ሲሆን ሰልፈኞቹን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች ጥይት ወደ ላይ ተኩሰዋል።
የኪረሙ ሁከት እና በሁከቱ ተሳታፊ አካላትን የመለየት ችግሮች
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን በኪረሙ ወረዳ ከህዳር 9 እስከ 12 ድረስ ለአራት ቀናት የዘለቀ ሁከትና ብጥብጥ በብዙ ምንጮች ከተረጋግጠ ቁጥራቸው ከፍተኛ ከሆነ የሟቾች ቁጥር ጋር ተዘግቧል ። እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ ህዳር 9 ቀን በወረዳው ተንካራ አካባቢ የአማራ ብሔር ታጣቂዎች (ፋኖ ተብለው የሚጠሩት) የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ላይ የደፈጣ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ውጊያ መጀመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ። ጥቃቱ የደረሰው የክልሉ ልዩ ኃይል በከብት ዘረፋ እና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ የአማራ እስረኞችን ወደ ነቀምት ከተማ ሲያጓጉዝ ነበር። ዶይቸ ቬለ (ዲደብሊው) አማርኛ ያነጋገራቸው አንድ የአማራ የአይን እማኝ እንደገለፁት የፀጥታ ኃይሉ በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ የኦሮሞ እስረኞችን ፈትተው የአማራ እስረኞችን ብቻ ወደ ነቀምት ለማጓጓዝ በመንቀሳቀሳቸው በዚህ አካባቢ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በፀጥታ ኃይሉ ላይ እምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል። ውጊያው እስከ ህዳር 12 ድረስ ቀጥሏል። በዚህ ውጊያ ምክንያት የመንግስት የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች አካባቢውን ለቀው ወደ አጎራባች አማራ ክልል የሸሹ ሲሆን የመንግስት ኃይሎችን ብሄርን መሰረት ባደረገ ጥቃቶች በመፈፀም ከሰዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 15, 2015)።
በምስራቅ ወለጋ ዞን በኪረሙ ሰሞኑን ለተከሰተው ሁከት በርካታ የተለያዩ መረጃዎች ተለቀዋል። የአማራ ማህበር በአሜሪካ (ኤኤኤ) እንደገለጸው ህዳር 9 ቀን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል የአማራ ተወላጅ እስረኞች በወረዳ ደረጃ እንዲከሰሱ እንጂ ወደ ነቀምት እንዳይዛወሩ የጠየቁ 13 ትጥቅ ያልታጥቁ ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን ተናግረዋል። ብጥብጡ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን ህዳር 10 ቀን ጠዋት ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በትንሹ ስምንት የአማራ ተወላጆችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል (ኤኤኤ፣ ህዳር 11, 2015)። የአማራ ማህበር በአሜሪካ ስለ ውጊያም ሆነ ስለ ፋኖ ታጣቂዎች ምንም ያለው ነገር የለም።
በኪረሙ ውስጥ እንደተከሰተው ሁለት ፅንፍ ያያዙ ሃሳቦች ባሉበት አካባቢ የኩነቶችን ትክክለኛ ምክንያት ፈልጎ ማግኘት እጅግ በጣም ከባድ ነው። እያንዳንዱ ኩነት ሁኔታው እንዴት እንደተከሰተ ከሚገልፁ መላምቶች ጋር ብዙ ውንጀላዎችን እና መቃወሚያዎችን ያስነሳሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ የአይን እማኞች ቢገኙም ፅንፍ ያያዙ ብሄረሰብ ባሉበት አካባቢ ግን ተዋጊ ያልሆኑት የህብረተሰቡ አካላትን በግጭቱ አንድ ወገን ላይ ስለሚያስቀምጣቸው የአይን እማኞቹ ራሳቸው እንኳን አድሏዊ ይሆናሉ ማለት ነው። በኢትዮጵያ በጣም አስቸጋሪ የሆነው የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ደግሞ ይህንን ያጠናክረዋል (ለበለጠ ዝርዝር ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ይመልከቱ)።
ከላይ እንደ ምሳሌ በቀረበው የኪረሙ ጥቃት የፋኖ ታጣቂዎች በመንግስት ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈፃሚ እንደሆኑ በአንዳንድ ምንጮች ተለይቷል (ኦኤምኤን፣ ህዳር 12, 2015)። የኪረሙ ክስተት ከመፈጠሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ከኪረሙ ወረዳ በስተምስራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ጃርዴጋ ወረዳ አሊቦ ከተማ የፋኖ ታጣቂዎች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያደረሱት ጥቃት በሰፊው ተዘግቧል (ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ ህዳር 10, 2015)። ሌሎች ምንጮች የታጠቁት የአማራ ታጣቂዎች “የአማራ ፅንፈኞች” መሆናቸውን ገልጸዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 15, 2015)። ነገር ግን የፋኖ ታጣቂዎች ኢ-መደበኛ ባህሪ እና የታጠቁ የአማራ ብሄር ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል መኖራቸው እራሳቸውን ፋኖ ብለው ቢጠሩም ባይጠሩም ማንነታቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። የፋኖ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ውጪ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የተገለጸባቸው ሌሎች ቦታዎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች እና በትግራይ ክልል ምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ዞኖች ናቸው (ስለ “ፋኖ ወጣት ታጣቂ” አመጣጥ እና እንቅስቃሴ የበለጠ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ አክተር ፕሮፋይልን ይመልከቱ)።