በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ህዳር 23, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,676
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,763
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 9,287
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከህዳር 17-23, 20152 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 23
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 147
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 120
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በኢፒኦ የዳታ ፋይል እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከሁለት አመታት ግጭት በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ከፈረሙ አንድ ወር ሆኖታል። በስምምነቱ መሰረት የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ከጦርነት ቀጠና መልቀቅ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የመሳሰሉ አንዳንድ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። ባለፈው ሳምንት የትህነግ/ህወሓት ባለስልጣናት የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ከማይ ቅነጣል፣ ዛላምበሳ፣ ነበለት፣ ጨርጨር፣ ኩኩፍቶ፣ ሕጉምብርዳ ፣ በሪተኽላይ እና አበርገሌ ግንባሮች መልቀቃቸውን ሪፖርት አድርገዋል (ትህነግ/ህወሓት፣ ህዳር 22, 2015)። የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ዋና አዛዥ ታደሰ ወረደ እንደተናገሩት 65% የሚሆነው የትህነግ/ህወሓት ሠራዊት የውጊያ ቀጠናዎችን ለቀው ወደ ካምፕ ተዘዋውረዋል (ሮይተርስ፣ ህዳር 25, 2015)። የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች የውጊያ ቦታዎችን መልቀቃቸው በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም። ከዚህ በተጨማሪም በህዳር መጀመሪያ ላይ የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች በናይሮቢ ካደረጉት ስብሰባ በኋላ የተቋቋመው የሁለቱ ወገኖች እና የአፍሪካ ህብረት ጥምር ኮሚቴ ቀላል ትጥቅ ማስፈታት ላይ በዝርዝር አብረው ለመስራት ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ተገናኝተዋል (ኤዩ፣ ህዳር 22, 2015)።
ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ጋር የሚተባበረው የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት የሰላም ስምምነቱን በመጣስ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎችን መግደላቸው እንዲሁም በቁጥጥራቸው ስር “ባሉ በሰሜን እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ቢያንስ ደርዘን ከተሞች ውስጥ ከተኩስ አቁሙ በኃላ” ሱቆችን እና ተሽከርካሪዎችን መዝረፋቸው ተነግሯል (ሮይተርስ፣ ህዳር 23, 2015)። እንደ ሰብአዊ ባለስልጣናት ገለጻ “በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች እና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ባሉ ሌሎች አካባቢዎች” እየተካሄደ ባለው ግጭቶች ምክንያት እነዚህ አካባቢዎችን አሁንም ማዳረስ አልተቻለም (ዲደብሊው፣ ህዳር 23, 2015)።
እንደ መንግሥት ከሆነ የሽሬ ከተማን ኃይልና ኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች የሚያገናኙት የኤሌክትሪክ መስመሮች “በጥቂት ቀናት ውስጥ” ወደ ነበሩበት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ህዳር 22, 2015፤ ኢቢሲ፣ ህዳር 19 2015)። መንግስት የባንክ፣ የኤሌትሪክ እና የመገናኛ አገልግሎቶች ማደስ የሰላም ስምምነት አካል ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ፖለቲካዊ ብጥብጥ እንደቀጠለ ነው። ባለፈው ሳምንት በተለያዩ አካላት መካከል የተደረጉ 11 ውጊያዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ኃይሎች በሆሮ ጉዱሩ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ተዋግተዋል። ቡድኑ በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሐራ ከተማ ዙሪያ የሪፐብሊካን ጋርድ ወታደራዊ ተሽከርካሪን አድፍጦ ካጠቃ ባኃላ ከሪፐብሊካን ጋርድ ኃይሎች ጋር ተዋግቷል። በተለይ በመተሐራ አካባቢ የሪፐብሊካን ጋርዶች የሚሳተፉባቸው ክስተቶች ብዙም ያልተለመዱ በመሆኑ ይህን ኩነት ለየት ያደርገዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በግንደ በርበሬ፣ ሀሙማ ጊንዶ፣ ባቡ ድሬ፣ በቾ እና ሀርቡ ቀበሌዎች ኦነግ-ሸኔ ከቀበሌ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል። ቡድኑ ከግንደ በርበሬ በስተቀር እነዚህን ሁሉ ቦታዎች መቆጣጠሩ ተነግሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በኦነግ-ሸኔ ላይ ያነጣጠሩ የሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ጥቃት ማድረጉን ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ ዞን ጉዱሩ ወረዳ በኮምቦልቻ እና በሰሜን ሸዋ ዞን በዋረ ጃርሶ ወረዳ ፋጂ ኤጀርሳ ቀበሌ በርካታ የሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ጥቃቶች ተደርገዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ያለው ብጥብጥ ቀጥሏል። ህዳር 20 ቀን የአማራ ብሔር ታጣቂዎች እንደሆኑ የሚገመቱ የአማራ ኃይሎች ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በኪረሙ የተዋጉ ሲሆን 10 የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እና የኪረሙ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሆኑ የተገለፀ የአካባቢው አስተዳደር ባለስልጣንን ጨምሮ 11 ሰዎችን ገድለዋል። አንድ ቀን ቀደም ብሎ በኪረሙ ወረዳ በተፈጠረ አለመረጋጋት ምክንያት በአንድ ትምህርት ቤት ተጠልለው የነበሩ ከ100 በላይ ሰዎችን ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቂ ቡድን ተኩሶ መግደሉ ተዘግቧል። ከዚህ ጥቃት በስተጀርባ ያለው ምክንያት ግልጽ አይደለም። በአሁኑ ወቅት በኪረሙ ወረዳ እና አካባቢው የገጠር መንደሮች እና ከተሞች ሁከትና ብጥብጥ እየቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በአማራ ብሄር ተወላጆች እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ተጨማሪ ክስተቶች በሚቀጥለው ሳምንት ዘገባ ይዳሰሳሉ። በወረዳው ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ሁከት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል (በኪረሙ በቅርቡ ስለተቀስቀሰው የግጭት ማዕበል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከህዳር 10-16, 2015ን ይመልከቱ)። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች በኪረሙ ስለተፈጠረው ሁከት ምላሽ የሰጡ ሲሆን የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቅ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት “እየተካሄደ ያለውን እልቂት፣ መፈናቀል፣ ማሰር እና የንፁሃን ሰዎች መዘረፍን ለማስቆም ፍላጎትና አቅም የለውም” ሲሉ ከሰዋል” (አብን፣ ህዳር 24, 2015)። በዚህ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ፋኖን ጨምሮ የአማራ ታጣቂዎች በሁከቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማውገዝ ተቃውሞ ተካሂዷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 27, 2015)።
በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በክልሉ በአጠቃላይ ስምንት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ህዳር 17 አካባቢ በሰሜን ሸዋ ዞን በሴረር ኩላ ቀበሌ የአማራ ብሔር ታጣቂዎች እንደሆኑ የተገመቱ የአማራ ኃይሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። በተጨማሪም የመንግስት ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ አንድ ሰው መግደላቸው እና በፊንፊኔ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ በካሶ ሰርቤ ቀበሌ ጋዜጠኞችን መደብደባቸው ተነግሯል።
የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሱ አራት ጥቃቶች ተሳትፈዋል። ህዳር 18 ቀን ኦነግ-ሸኔ በምስራቅ ሸዋ ዞን በዶኒ ጠበል (ዶኒ) እና በፎቂ ከተሞች በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል። በዚህ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ 11 ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል። ቡድኑ በአካባቢው ሳምንታዊ ገበያ ሲገበያዩ ቆይተው ከዶኒ ከተማ ወደ ፎቂ ከተማ ይጓዙ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችንም አፍኖ ወስዷል። በተጨማሪም ህዳር 21 ቀን ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳአ በርጋ ወረዳ ሙገር ከተማ አቅራቢያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሠራተኞች ማመላላሻ (ሰርቪስ) አውቶብስን አስቁመው 30 የሚጠጉ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞችን ጎትተው አውጥተው መውሰዳቸው ተዘግቧል። ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች ወደ ማዕድን ማውጫ ቦታ እየሄዱ ነበር። ቡድኑ የፅዳት እና ጥበቃ ሠራተኞች ለቆ ቀሪዎቹን 17 ሠራተኞች ወደ አልታወቀ ቦታ ወስዷል። ታፍነው የተወሰዱት ሠራተኞች እስከ 500,000 ብር (9,400 ዶላር አካባቢ) ከፍለው በሳምንቱ መጨረሻ ተለቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ በወለንጪቲ ውስጥ ባልታወቀ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ ከመተሐራ ዙሪያ ካሉ አከባቢዎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎችን አፍኖ የወሰደ ሲሆን በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ መተሐራ በዱቢቻ ደምበል አካባቢ አግቷቸው እንደሚገኝ ተዘግቧል (ኢሳት፣ ህዳር 20, 2015)።
በመጨረሻም ህዳር 22 ቀን በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ሹሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው አምሃ ደስታ (እንጦጦ አምባ) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ይስቀላል ወይም አይሰቀልም በሚል በተነሳ ውዝግብ የተነሳ ብጥብጥ ተቀስቅሷል። በዚህ ብጥብጥ ሁለት ህጻናት ቆስለው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተማሪዎች ታስረዋል።