በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 –ህዳር 30, 20151እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,702
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 20,970
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 9,409
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከህዳር 24-30, 20152በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 13
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 80
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 15
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በኢፒኦ የዳታ ፋይል እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በምዕራብ ኦሮሚያ ከቀጠለው እና እየተስፋፋ በመጣውን ግጭት እና በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ከመስቀል ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰ ረብሻ ምክንያት ባለፈው ሳምንት በሃገሪቱ ያለው ውጥረት ጨምሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል ተደራሽነት በመሻሻሉ እና በክልሉ የሚከሰቱ ጥቃቶች በመቀነሳቸው የክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ነው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)።
በትግራይ ክልል ዋና ከተማዋን መቀሌ እና ውቁሮ፣ አዲግራት፣ ሽሬ እና ሁመራን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የመብራት አገልግሎት ጀምሯል። እነዚህ አካባቢዎች ከሰኔ 2013 ጀምሮ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ወይ ሙሉ ለሙሉ አላገኙም ወይም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ውስን ነበር (ዲደብሊው አማርኛ፣ ታህሳስ 1, 2015)። በተጨማሪም የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአክሱም እና በአድዋ ከተሞች “በጥቂት ቀናት ውስጥ” ወደ ነበረበት ሊመለስ እንደሚችል የሚያሳዩ መረጃዎች ሲኖሩ በሽሬ ከተማ ቴሌኮሙኒኬሽን ባለፈው ሳምንት አገልግሉት መስጠት ጅምሯል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 28, 2015)። በተጨማሪም በጎንደር -ሁመራ -ማይ ጸምሪ፣ ኮምቦልቻ-አላማጣ-መቀሌ እና ሰመራ-መቀሌ መንገዶችን ጨምሮ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ ነው። ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታ በረራዎችም እንደገና የጀመሩ ሲሆን ከአዲስ አበባ ሽሬ የሚደረጉ የሰብአዊ በረራዎች ባለፈው ሳምንት ጀምረዋል (ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ህዳር 27, 2015)። ቀደም ሲል የሰብአዊ በረራዎች የሚደረጉት ወደ መቀሌ ብቻ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ግጭት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በክልሉ ውስጥ ስድስት የጦርነት ኩነቶች እና አምስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሁሉም የጦርነት ኩነቶች የተከሰቱት በምዕራብ ኦሮሚያ ማለትም በምስራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ነው። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ሶስት ጥቃቶች ውጊያ ከተከሰተባቸው ምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ጋር የተገናኙ ናቸው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)።
በምስራቅ ወለጋ ዞን በጉቲን ከተማ ውጊያ የተዘገበ ሲሆን ህዳር 24 እና 25 የአማራ ብሄር ታጣቂዎች ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ተዋግተዋል። በግጭቱ ቢያንስ 34 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። የሟቾች ቁጥር ከዚህ በጣም ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። የአካባቢው የአማራ ነዋሪዎች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከመንግስት በተሰጠው ስልጣን የአካባቢውን የአማራ ማህበረሰብ ለመጠበቅ በተቋቋሙት የአማራ ብሄር ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋል። የጉቲን ከተማ የኦሮሞ ነዋሪዋች እና የአካባቢው ባለስልጣናት ፋኖ ብለው የሚጠሯቸው የአማራ ብሄር ታጣቂዎችን በጉቲን ለተቀሰቀሰው አዲስ ዙር ጥቃት በማነሳሳት ከሰዋቸዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 28, 2015፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 26, 2015፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 27, 2015)። የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን ለማረጋጋት ህዳር 26 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ወደ ከተማዋ አሰማርቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 27, 2015)። ነገር ግን ህዳር 29 ቀን በኦሮሞ ክልል ልዩ ኃይል እና በአማራ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መቀስቀሱ ተነግሯል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን ከጉቲን በስተሰሜን 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በኪረሙ ወረዳም ግጭቱ እንደቀጠለ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በሃሮ አዲስ አለም እንዶ ከተማ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈፀሙ ተነግሯል። የኦነግ-ሸኔ ቃል አቀባይ ኦዳ ቶርቢ የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው የሚለውን ክስ አስተባብለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ህዳር 28, 2015)። ቡድኑ በዚሁ ወረዳ ኦኬ (ቦኬዬ) በተባለ ስፍራ የአማራ ተወላጆች ላይ ሌላ ጥቃት ማድረሱን ተነግሯል (በኪረሙ ወረዳ ስላለው ግጭት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከህዳር 17-23, 2015ን ይመልከቱ)።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት የፋኖ ታጣቂዎች እና ኦነግ-ሸኔ በሌሎች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በወለንጪቲ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ መንደሮች የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው የተባሉ የአማራ ታጣቂዎች ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ቡድኑ በርካታ ቤቶችን አቃጥሏል የሰላማዊ ሰዎችን ንብረቶችንም ዘርፏል። ከሁለት ቀናት በኋላ በሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ አካባቢ አራት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በኦነግ-ሸኔ ታፍነው ተወስደዋል። ቡድኑ ሦስቱን የጭነት መኪኖች ያቃጠለ ሲሆን አሽከርካሪዎቹን ለማስለቀቅ እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር (56,200 ዶላር አካባቢ) ጠይቋል።
በክልሉ በተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጅ ሰላማዊ ሰዎች ከቄያቸው ተፈናቅለዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት መሰረት “በስፈራው መሄድ ስላልተቻለ አዲስ የተፈናቃዮች አሃዝ እስካሁን የተረጋገጡ አይደሉም፣ ነገር ግን በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚያመጣ ይጠበቃል” (ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ህዳር 27, 2015)። እንደ አካባቢው ባለስልጣናት በኪረሙ ወረዳ በሚገኙ 19 ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች “ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል” በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለዋል (ዲደብሎው አማርኛ፣ ህዳር 26, 2015፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 26, 2015)። በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጠረው ግጭት የተነሳ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሸሽተው ወደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ገብተዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 27, 2015)።
በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች ሰልፎች ተካሂደዋል። ባለፈው ሳምንት በመላው የኦሮሚያ ክልል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች “በአማራ ብሄር ታጣቂዎች እና በመንግስት ኃይሎች በኦሮሞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ” በማውገዝ ተቃውሞ ተካሂዷል (ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ ህዳር 28, 2015)። በአዳማ ከተማ ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን ባደረገው ጥረት መጠነኛ ጉዳት መድረሱ ቢገለጽም ሁሉም ተቃውሞዎች ሰላማዊ ነበሩ። በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በድሬዳዋ እና በጋምቤላ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም በተመሳሳይ የኦሮሞ ተወላች ተማሪዎች ተቃውሞ ተካሂደዋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ ከተማ “በኦነግ-ሸኔ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት እና የመንግስትን ዝምታ” በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል (አዲስ ማለዳ፣ ህዳር 30, 2015)። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዲላ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችም በኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን በተመሳሳይም የኦሮሞ ተወላጆች በክልሉ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ግድያ ተቃውመዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ታህሳስ 1, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭትም በመዲናይቱ አዲስ አበባ ውጥረት እንዲነግስ ያደረገ ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ መስቀል እና የክልሉን መዝሙር መዘመር ጋር በተያያዘ በርከት ያሉ ሰልፎች እና ግጭቶች ተፈጥረዋል። በጉለሌ ክፍሌ ከተማ ወረዳ 1 በሚገኘው የአምሃ ደስታ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወላጆች በትምህርት ቤቱ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ መሰቀሉን በመቃወም ህዳር 25 ቀን ሰልፍ አድርገዋል። በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ተማሪዎች ለተከታታይ ቀናት ወደ ትምህርት ገበታቸው አልተመለሱም (ኢሳት፣ ህዳር 28, 2022)። ከሁለት ቀናት በኋላ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘው የከፍትኛ 12 ትምህርት ቤት ተማሪዎች የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ያወረዱ ሲሆን ይህንን ሊያስቆሙት የሞከሩ ሌሎች ተማሪዎች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። ብጥብጡ ትምህርት ቤቱ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ተዛምቷል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በግጭቱ አንድ ተማሪ ሲገደል አንድ መምህርን ጨምሮ ከ10 በላይ ተማሪዎች ቆስለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ግን በተፈጠረው አለመረጋጋት የአንድ ተማሪ ህይወት አልፏል የሚለውን ዘገባ ውድቅ አደርጓል (የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ህዳር 30, 2015)። በሚቀጥለው ቀን በአዲስ ከተማ ክፍሌ ከተማ በአዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ብጥብጡ ቀጥሎ መምህራን፣ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች በትምህርት ቤቱ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ይሰቀላል አይሰቀልም በሚል ተጋጭተዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ በከተማዋ ለተቀሰቀሰቅ ሁከት “የዋና ከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ በሚፈልጉ… ጽንፈኞችን” ተጠያቂ ያረገ ሲሆን በመዲናዋ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሁከትና ብጥብጥ በመቀስቀስ እና አመጽ ሰልፎችን በማዘጋጀት የተጠረጠሩ 97 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል (የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ህዳር 29, 2015)።
በመጨረሻም የቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ አባላት በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ፈትተው የተሃድሶ ስልጠና ለመውሰድ ሱዳን በሚያዋስነው በሸርቆሌ ወረዳ በኩል ወደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መግባታቸው ተዘግቧል። ይህ የሆነው በሱዳን ካርቱም ቡድኑ እና የክልሉ መንግስት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኃላ ነው (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ታህሳስ 2, 2015)። የክልሉ መንግስት ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ሌላ የሰላም ስምምነት ከጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር በአሶሳ ከተማ ተፈራርሞ ነበር (ለበለጠ መረጃ የ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 5-11, 2015ን ይመልከቱ)። መንግስት እነዚህ ሁለት ቡድኖችን እና ኦነግ-ሸኔን ላለፉት ጥቂት አመታት በክልሉ ውስጥ ግጭት በማነሳሳት ሲከሳቸው ነበር።