በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከጥር 13, 2014 –ጥር 19, 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,273
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 6,552
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,653
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከጥር 13-19, 20151በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 37
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 132
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 18
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ለሳምንት ያህል የዘለቀ ግጭት መከሰቱ የተገለጸ ሲሆን ለአራት ወራት ያህል ከዘለቀ ከፍተኛ የፖለቲካ ግጭት በኋላ በኦሮሚያ ክልል አንድ ኩነት ብቻ ተመዝግቧል።
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አዋሳኝ ድንበሮች ለቀናት የቆየ ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን በትንሹ 98 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። እንደ አንድ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢ አስተዳዳሪ ጥር 12 ቀን በኦሮሚያ ልዩ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ሰንበቴ አቅራቢያ በሚገኘው ሙጢ ፋታ መንደር (በአንዳንድ ምንጮች ጃዋ እየተባለ በሚጠራው) መንደር በተፈጠረ አለመግባባትና ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ በማለት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሰባት የኦሮሞ ተወላጆችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል።2 ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ ጥር 16, 2015 በማግስቱ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የኦሮሞ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፈራታና ግድም ወረዳ በጀዋሃ ነጌሶ ቀበሌ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በቡድኑ እና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እና በተባባሪ ኃይሎች ለሁለት ቀናት መዋጋታቸውን እና ከ28 ያላነሱ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት እና ስድስት የፌዴራል ፖሊስ አባላት መገደላቸው ተዘግቧል።3ሪፖርተር፣ ጥር 17, 2015 በጥር 15 ቀን ግጭቱ ወደ አጎራባች አካባቢዎች ተስፋፍቷል። በታጠቁ ኃይሎች መካከል ውጊያዎች በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሰንበቴ፣ ማጀቴ፣ ጭሬ፣ ጨፋ ሮቢት እና በከሚሴ ከተማ ዙሪያ ሲመዘገቡ በሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ በአጣዬ እና በሸዋ ሮቢት ከተሞች እንዲሁም በአካባቢያቸው ባሉ ቦታዎች እንዲሁም ባልጪት፣ መስኖ ሀገረ ማርያም ቀበሌ፣ ጨጨቅ ቀበሌ፣ ጀዋሃ ነጌሶ ቀበሌ እና ቀወት ውጊያዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ጦርነቱ እስከ ጥር 17 ድረስ ቀጥሏል። የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ እንደገለፁት በኦሮሚያ ልዩ ዞን ብቻ 98 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 155 ሰዎች ቆስለዋል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በአካባቢው በተፈጠረ ግጭት ወደ 1,930 የሚጠጉ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።4ዲደብሊው፣ ጥር 20, 2015
ግጭቱን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስት በፀጥታ ኃይሎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደረሱትን “ፀረ-ሰላም ኃይሎች” ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።5አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 17, 2015 የኦነግ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የመንግስት ታጣቂዎች በአርሶ አደሮች ላይ ተኩስ ከፍተዋል ሲል ግጭቱ በመቀስቀስ ከሷቸዋል። እንደ ፓርቲው ገለጻ በዚህ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት “የፖለቲካ ሸፍጥ” በመሆኑ የኦነግ ፓርቲ ተወካይ ለግጭቱ “ፖለቲካዊ መፍትሄ” እንዲሰጥ ጠይቀዋል።6ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 18, 2015 በተጨማሪም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመባል የሚታወቀው የኦነግ-ሸኔ ቃል አቀባይ ኦነግ-ሸኔ በአካባቢው ምንም አይነት ኃይል እንደሌለው በመግለጽ የቡድኑ ኃይሎች በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገዋል። ቃል አቀባዩ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭቱ እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ሲሉም ከሰዋል።7ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 20, 2015 በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ “በመንግስት ተቋማት የሚደገፉ ኃይሎች” በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ያለ ሲሆን የአማራ ክልል መንግስት የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ ባለመቻሉ እና በአካባቢው “የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ባለማግኘቱ” አውግዟል።8የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ጥር 17, 2015 ነገር ግን የእናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በቅርቡ በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ኦነግ-ሸኔ አነሳስቷል ሲሉ ከሰዋል።9ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 20, 2015
የአማራ ክልል ኦሮሞ ልዩ ዞን ተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትበት ቦታ ነው። ልዩ ዞኑ በአማራ ክልል ውስጥ ቢገኝም ኦሮሞ ተወላጆች የሚኖሩበት እና የሚያስተዳድሩት ሲሆን ይህም በአቅራቢያው ካሉ ከተሞች እና መንደሮች መካከል የውዝግብ መንስኤ ነው። ኢፒኦ በዚህ አካባቢ ከ2013 ጀምሮ በርካታ ግጭቶችን ተከታትሎ ሪፖርት አድርጓል (ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 8, 2014 እስከ ሚያዚያ 14, 2014፤ ኢፒኦ ሳምንታዊ : ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 29, 2013 ይመልከቱ)። በ2014 አካባቢውን የኦነግ-ሸኔ እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር ኃይሎች ባደረጉት ያልተለመደ የጋራ ዘመቻ ለአጭር ጊዜ ተቆጣጥረውት ነበር።10ሮይተርስ፣ ጥቅምት 21, 2014
በዘገባዎች መዘግየት ምክንያት በቅርብ ስለተከሰተው ግጭት እና ስላስከተልው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ማወቅ አልተቻለም። ነገር ግን ሁከቱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ለመሰደድ መገደዳቸው ተዘግቧል።11ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 22, 2015 አዲስ አበባን ከደሴ የሚያገናኘው ዋና መንገድ ለቀናት ተዘግቶ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግጭቱ ጋብ ማለቱንና አካባቢው የተረጋጋ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።12ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 22, 2015
በኦሮሚያ ክልል ጥር 16 ቀን በምስራቅ ሸዋ ዞን አዋሽ መልካሳ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ባቶ ደጋጋ ቅዱስ ጎርጊስ ቤተክርስቲያንን አቃጥለዋል። አክሌድ ባለፈው ሳምንት በክልሉ ውስጥ ሌላ ምንም አይነት ኩነቶች አልመዘገበም።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጥር 17 ቀን ኦነግ-ሸኔ በጌዴኦ ዞን በገደብ ከተማ በመግባት ጥቃት በማድረስ ከሁለት እስር ቤቶች እስረኞችን አስፈትቶ የጦር መሳሪያ ዘርፎ እና ስድስት ባንኮችን ሰብሮ ጉዳት አድርሷል። ጥቃቱ እስከ ማግሥቱ ማለዳ ድረስ ቀጥሏል። በዚህ ጥቃት አንድ ፖሊስ እና አራት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገድለዋል። የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች በገደብ ጥቃት ማድረጋቸውን ነገር ግን ጥቃት ያደረሱት በከተማው በሚገኘው የፌዴራል እና የክልል ኃይሎች ካምፕ ላይ መሆኑን የኦነግ-ሸኔ (የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት) ቃል አቀባይ አረጋግጠዋል።13ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 18, 2015
በመጨረሻም ጥር 19 ቀን በቡርጂ እና በቦረና ማህበረሰቦች መካከል ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል። ግንቦት 27 ቀን 2014 በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በቡርጂ ልዩ ወረዳ በሶያማ ከተማ ገበያ ላይ የቡርጂ ብሔር ተወላጆች ከጉጂ ዞን የመጡ አስር የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ደብድበው የገደሉ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎችን ደግሞ አቁስለው ነበር። ከዚህ ግጭት በኃላ ማህበረሰቡን የሚያገናኘው መንገድ የተዘጋ ሲሆን በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነትም ተቋርጦ ነበር። በባህላዊ የግጭት አፈታት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የባህል መሪዎቹ መንገዱን ለመክፈት እና ሁለቱ ማህበረሰቦች በጋራ መገበያየታቸውን እንዲቀጥሉ ተስማምተዋል።14ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 20, 2015