በቁጥር: ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2፣ 2014 – መጋቢት 8፣2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,169
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 6,347
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,671
በቁጥር: ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2 – 8፣ 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 12
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 29
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 21
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሣሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኢትዮጵያ ከትግራይ የሰላም ሂደት ጋር ተያይዞ የግጭት ሁኔታ መሻሻል ማሳየት የቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልልም ግጭት በሰላም እንዲፈታ ጥሪዎች ቀርበዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቱሉ ጉሌድ ከተማ አቅራቢያ በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳኝ ድንበር ላይ በሶማሌ እና በኦሮሞ ብሔር ታጣቂዎች መካከል በተከሰተ ግጭት የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተዘግቧል (ተከታዩን ካርታ ይመልከቱ)። ቀደም ባሉት ጊዜያ በዚህ አካባቢ በግጦሽ መሬቶች እና በውኃ ቦታዎች ዙሪያ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሳቢያ ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሲሆን ላለፉት ጥቂት ዓመታት አንጻራዊ ሰላማዊ ሁኔታ ነበር። ዘንድሮ ወርሃ ጥር ጀምሮ ግጭቶች አገርሽተዋል። በኦሮሚያ ክልል በተከሰተ ሌላ ጥቃት በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሐራ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ-ሼኔ አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም ተብሏል) – ባደረሱት ጥቃት ስምንት ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት መግደላቸው እና 4 ሰዎችን ማቁሰላቸው ተዘግቧል። ከተጎጂዎቹ መካከል ስድስቱ ጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ነበሩ። የኦነግ-ሼኔ (የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመባልም ይታወቃል) እንቅስቃሴዎች የምዕራብ ኦሮሚያ ያህል ጠንካራ እና መጠነ ሰፊ ባይሆንም በምሥራቅ ኦሮሚያ አካባቢዎችም በስፋት ይስተዋላሉ። ከመጋቢት 2014 ጀምሮ ከአማራ ክልል በሚመጡ ሚሊሻዎች እና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቀበሌ ሚሊሻዎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሊበን ከተማ መጋቢት 2፣ 2015 ሦስተኛ ቀኑን በያዘ ተቃውሞ ወጣቶች ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋታቸው ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ሆኗል። የተቃውሞው ምክንያትም ከስድስት ወራት በላይ የቆየ የመጠጥ ውኃ እና መብራት አቅርቦት መቋረጥ ነው ተብሏል። የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን ለመበተን በተኮሱት ጥይት አንድ ሰው ለሞት ተዳርጓል።
በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ባጃጅ በመባል የሚታወቁት ባለሦስት ጎማ ታክሲዎች ዋና ዋና መንግዶች ላይ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተጣለው እገዳ ከሳምንት በፊት በተደረጉ ሁከት ባስከተሉ ተቃውሞዎች ተነሥቷል። የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እንዳስታወቀው ታክሲዎቹ ቢሮው ባስቀመጣቸው አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሠሩ ቢፈቀድላቸውም የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አይሆኑም። በሌላ የአዲስ አበባ ሁነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እየደረሱ ናቸው ያላቸው ሕገወጥ እስር፣ ማስፈራራት እና ማዋከብ “ተቀባይነት የለውም” ሲል አውግዟል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት እናት ፓርቲ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያካሄዱ በይፋ ባልተጠቀሱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ታግደዋል። የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ አባላትም በይፋ ባልተገለጠ ክስ በፌደራል ፖሊስ ታስረዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን ጎብኝተው በትግራይ ክልል የተጀመረውን የሰላም ሂደት አፈፃፀም አድንቀዋል። ብሊንከን ጨምረውም “በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው” እና ችግሩ “በውይይት መፈታት” እንዳለበት ተናግሯል።
በመጨረሻም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 46 የሚሆኑ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ቤሕዴን) አባላት ከእስር ተፈተው ወደ 3,000 የሚሆኑ አስቀድሞ የተፈቱ የቀድሞ የቡድኑን አባላት ተቀላቅለዋል። ይህም የሆነው ከስድስት ወራት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በተደረጉ የሰላም ሂደቶች ከተጀመሩ ወዲህ ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአጠቃላይ እና በክልሉ መተከል ዞን ደግሞ በተለየ ሁኔታ በ2012 እና 2013 በኢትዮጵያ ውስጥ አደገኛ ግጭቶች ከተከሰቱባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን እንደ ቤሕዴን ያሉ አማፂያን እና ከአማራ ክልል በሚመጡ ታጣቂ ኃይሎች መካከል በተነሱ በርካታ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በቅርቡ የተደረሰው ስምምነት ግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ ከናረ ወዲህ የተደረገ እና ውጤት እያስገኘ ያለ የሰላም ሂደት መሆኑ ለአከባቢው የመረጋጋት ተስፋ ሰጥቷል።