በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ
- ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 በጨረፍታ
- አበይት ክንውኖች
- ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ የተከሰቱ ቁልፍ ኩነቶች
- ወርሀዊ ትኩረት፡ በሰላም ዕድሎች መካከል የፖለቲካ ግጭት አዝማሚያዎች መቀነስ
ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22, 2015 በጨረፍታ
አበይት ክንውኖች
- ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ አክሌድ 37 የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች እና 86 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች መዝግቧል። ይህ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከጀመረ ከጥቅምት 2013 ወዲህ የተመዘገበ ዝቅተኛው የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ነው።
- ባለፈው ወር የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች እና በፖለቲካ ግጭት ምክንያት ሪፖርት የተደረገ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበ ሲሆን 32 ኩነቶች እና 82 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግቧል። በሃገሪቱ ከተመዘገቡት ጠቅላላ ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ከ95 በመቶ በላይ የተመዘገቡት በኦሮሚያ ክልል ነው።
- ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም ተደጋግመው የተከሰቱት የኩነት ዓይነቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ጦርነቶች ሲሆኑ 25 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃት ኩነቶች እና 11 የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ክስተቶች መካከል አብዛኞቹ – 22 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የጥቃት ኩነቶች እና 10 የጦርነት ኩነቶች – በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው።
ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ የተከሰቱ ቁልፍ ኩነቶች
ወርሀዊ ትኩረት፡ በሰላም ዕድሎች መካከል የፖለቲካ ግጭት አዝማሚያዎች መቀነስ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ግጭት አዝማሚያዎች
ከጥቅምት 2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ የፖለቲካ ግጭቶች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። ከመስከረም 2013 በኃላ – የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከመከሰቱ በፊት – ለመጀመሪያ ጊዜ ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ዝቅተኛ ግጭት እና ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ተመዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ግራፍ ይመልከቱ)። ይህ አዎንታዊ አዝማሚያ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ግጭት በመቆሙ፣ በኦሮሚያ ግጭት መቀነሱ እና ቀደም ሲል በግጭት በተጎዱ ክልሎች የሰላም ጥረቶች በመኖራቸው ምክንያት የተከስተ ተድርጎ መውሰድ ይችላል።
ይህ ወርሃዊ ሪፖርት የኢትዮጵያን የተለያዩ የሰላም ሂደቶች በመተንተን አዲስ የግጭት ሊይስከትሉ የሚችሉ ነጥቦችን ይዘረዝራል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለው እንቅስቃሴ አዎንታዊ ይመስላል። ሆኖም እየተካሄደ ያለው የሰላም ሂደት ደካማ ሲሆን አዲስ ዙር ግጭት ሊከሰት ይችላል።
በኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራ እና ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች የሰላም ሂደቶች
ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በፌዴራል መንግስት መካከል የተካሄደው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ዋና ዜናዎች ላይ ማዕከል የሆነበት የሰላም ሂደቶች የበላይነትን አግኝተው ስንብተዋል። ሌሎች በርካታ የሰላም ሂደቶች ከሌሎች ፀረ-መንግስት ታጣቂ ቡድኖች ጋር በተለያዩ ስኬት ደረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳን አዎንታዊ አዝማሚያዎች ቢኖሩም የሰላም ስምምነቱ ጥቅምት 2015 ከተፈረመ በኋላ በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጦች ምክንያት በፊት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አዲስ የግጭት አዝማሚያዎች ከአዲስ የኩነቶች ስፍራ (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ) እና በእነዚህ ኩነቶች የሚሳተፉ አካላት ጋር ተስተውለዋል። ካለፉት አራት ዓመታት ጋር አንፃር እ.ኤ.አ ከዲሴምበር 2022 ጀምሮ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚከሰት ግጭት ተደጋጋሚ እየሆነ መጥቷል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እየተካሄደ ያለው የትጥቅ ትግል ቢቀጥልም በኦሮሚያ ክልል ደቡብ እና ምስራቅም ግጭት ታይቷል።
መጋቢት 13 ቀን የኢትዮጵያ ፓርላማ ትህነግ/ህወሓትን ከ“አሸባሪ” ድርጅቶች ዝርዝር እንዲሰረዝ ድምጽ ሰጥቷል።1ሃሚድ አወል፣ ‘ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ተሰረዘ፣’ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት13, 2015 ከቀናት በኋላ የፍትህ ሚኒስቴር በትህነግ/ህወሓት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የመሰረተውን የወንጀል ክስ አንስቷል።2የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፍትህ ሚኒስቴር፣ ‘የክስ መነሳትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ፣’ መጋቢት 21, 2015 የኢትዮጵያ መንግስት በሚያዚያ 23, 2013 ከኦነግ-ሸኔ ጋር ትህነግ/ህወሓትን “አሸባሪ” ብሎ ፈረጇቸው ነበር።3የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት– ኢትዮጵያ፣ ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት መሰየም የውሳኔ ሐሳብ አስተላልፏል፣’ በሚያዚያ 23, 2013 ውሳኔው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን ሁለቱም ትህነግ/ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች እና በመሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ጨምሮ የተለያዩ የ”ሽብርተኝነት” ድርጊቶች ፈፅመዋል ሲል በመንግስት ማረጋገጫ ላይ የተመሰረተ ነው።4ይህ ውሳኔ በሚያዚያ 29,2013 በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። ሲሳይ ሳህሉ፣ ‘ምክር ቤት ቲፒኤልኤፍን፣ ሸኔን በአሸባሪነት መፈረጃቸውን አፅድቋል፣’ ሪፖርተር፣ ሚያዚያ 29,2013 ይመልከቱ
ትህነግ/ህወሓትን ከ”አሸባሪ” ድርጅት ዝርዝር ውስጥ ለማስወገድ እና በቡድኑ ላይ የወንጀል ክስ እንዲቋረጥ የተደረገው ውሳኔ በአንዳንድ የኢትዮጵያ የፖርላማ አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል። እርምጃውን የሚቃወሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የብልጽግና ፓርቲ አባላት በግጭቱ ሂደት ለደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ጉዳት ትህነግ/ህወሓት ተጠያቂ እንዲሆን ይፈልጋሉ።5ሮይተርስ፣ ‘ኢትዮጵያ የትግራይን ቲፒኤልኤፍ ፓርቲ ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ ሰረዘች’፣ መጋቢት 13, 2015 ይህ ተቃውሞ እንዳለ ሆኖ ጦርነቱ ዳግም እንዳይቀሰቀስ ያለውን እድል በመቀነስ በፌዴራል መንግስት እና በትህነግ/ህወሓት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እነዚህ ዋና ዋና እርምጃዎች ናቸው። በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በትህነግ/ህወሓት ከፍተኛ የበላይነት የተያዘ ለትግራይ ክልል የተሾሙት ባለስልጣናት በፌዴራል መንግስት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሆነው በይፋ ተሹመዋል (ስለ ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስብጥር የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከየካቲት 18–24, 2015 ይመልከቱ)።6የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት– ኢትዮጵያ፣ ‘የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስለማቋቋም፣’ መጋቢት 14, 2015
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ግጭት መቀነሱ ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት እድል ሊኖር እንደሚችል ቢጠቁምም በኦሮሚያ ክልል የሠላም ሒደቱ የትግራይን ያህል ለውጥ አላሳየም። በሕዳር 26 ቀን ከኦሮሚያ የተወከሉ የፓርላማ አባላት በትግራይ ክልል የተጀመረው የሰላም ሂደት በኦሮሚያ ክልልም እንዲደገም እና የፌዴራል መንግስት ከኦነግ-ሸኔ ጋር እንዲደራደር ለፌዴራል መንግስት በደብዳቤ ጠይቀዋል።7ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ ‘የኦሮሞ ህዝብ እንዲያርፍ በትግራይ የተካሄደው እርቅ በኦሮሚያ ሊደረግ ይገባል’ – የፓርላማ አባላት፣’ መጋቢት 4, 2015 ተመሳሳይ ደብዳቤ ለአፍሪካ ህብረት የተላከ ሲሆን ድርጅቱ “ጣልቃ እንዲገባና በድርድር ስምምነት ላይ እንዲደርስ” አሳስቧል።8 አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና፡- የኦሮሚያ የህግ አውጭዎች የአፍሪካ ህብረት በኦሮሚያ ግጭት እንዲቆም “ጣልቃ እንዲገባ እና እንዲያደራደር”፣ የተፋላሚ ወገኖች ጥሪ እንዲደግም አሳሰቡ፣’ መጋቢት 11, 2015 ከቡድኑ ጋር ለመደራደር የአካባቢውን የሀገር ሽማግሌዎች ለመላክ የተደረገው ሙከራ እስካሁን አልተሳካም። መጋቢት 19 ቀን በወጣ መግለጫ የኦነግ-ሸኔ (የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመባልም የሚታወቀው) አመራሮች የመንግስትን የድርድር ሙከራዎች ከልብ አይደለም ሲሉ አውግዘው ማንኛውም ከመንግስት ጋር የሚደረግ ንግግር በአለም አቀፍ የሶስተኛ ወገን በኩል እንዲካሄድ ደግመው አፅኖት ሰተዋል።9የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ‘በቅርብ ጊዜ አብይ አህመድ የሰላም ድርድርን አስመልክቶ የተናገረውን በተመለከተ፣’ መጋቢት 19, 2015
በሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ መሰረታዊ የፖለቲካ ልዩነቶች በኦሮሞ እና በአማራ ፖለቲከኞች መካከል እንደቀጠለ እና ይህም በማህበረሰቡ ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር እያደረገ ነው። ነገር ግን እነዚህ በብሔር ታጣቂዎች መካከል እየታዩ ያሉት ግጭቶች ባለፉት ሁለት ወራት እየቀነሱ መሆኑ አንዳንድ ምልክቶች ያሳያሉ። በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሮ ወለጋ ዞኖች በህዳር እና ታህሳስ 2015 በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል የተቀሰቀሰው ከባድ ግጭት ቀዝቀዝ ያለ ሲሆን ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ባለው ጊዜ ውስጥ የአማራ ታጣቂዎች የተሳተፉበት ምንም አይነት የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች አለመፈጸሙ እና ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ አራት ኩነቶች ተመዝግበዋል (በአማራ እና በኦሮሞ ማህበረስብ መካከል ስለሚነሱ ግጭቶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ፡ ከሕዳር 22 እስከ ታህሳስ 22, 2015 ይመልከቱ)። በተመሳሳይ በአማራ ክልል በጥር ወር በኦሮሚያ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ለስድስት ቀናት የዘለቀ ጦርነት ከ98 የማያንሱ ሰዎች በመሞታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ አሁን በአማራ ክልል ግጭት ቀንሷል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥር 13-19, 2015 ይመልከቱ)። የካቲት 22 ቀን የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት ተወካዮች በጋራ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው በጋራ ባወጡት መግለጫ “የጋራ መፍትሄ ላይ መደረሱን” አመልክተዋል።10የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ‘በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው፣’ የካቲት 22, 2015
በአማራ ክልል በብዛት በጎንደር አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባል የሆኑ ከ1,000 በላይ ታጣቂዎች የአማራ ክልል መንግስት እና ታጣቂ ቡድን ባደረጉት የሰላም ውይይት ባለፉት 6 ወራት ውስጥ “ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተመልሰዋል”።11ዶይቸ ቬለ አማርኛ፣ ‘የመጋቢት 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የዓለም ዜና፣’ መጋቢት 25, 2015
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የተደረጉ ሰላም እና ድርድር ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ2022 ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ተለቀዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 1–8፣ 2015 ይመልከቱ)። ባለፈው አንድ አመት በክልሉ የሚስተዋሉ ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ የሰላም ንግግሮቹን ውጤታማነት ያሳያል። በሰኔ 2013 በክልሉ በርካታ አካባቢዎች አለመረጋጋት ስለነበረ የባለፈው ሃገራዊ ምርጫ የተሰረዘ ሲሆን አሁን ግጭት መቀነሱን ተከትሎ ያለው ሁኔታ በዚህ አመት ምርጫ እንዲካሄድ ሊያስችል ይችላል።12ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ የተስተጓጎለው ምርጫ እንዲካሔድ ጠየቁ፣’ መጋቢት 20, 2015
ግጭት የመቀስቀስ አቅም ያላቸው ጉዳዮች
በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም ጥረቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን የሚያሳዩ አበረታች ምልክቶች ቢኖሩም አሁን ያለውን አቅጣጫ የሚቀይሩ እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍተኛ የግጭት ደረጃ የሚመልሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ማለትም ልክ እንደ ምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ጉዳዮች ነባር ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ አዲስ ሁኔታዎች ናቸው።
በመጀመሪያ በኦሮሚያ ክልል ያለው የሰላም ሂደት በይፋ የለም። ምንም እንኳን ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ቢያሳዩም፣ የፖለቲካ ልዩነቶች እና በመሠረታዊ የፖለቲካ አደረጃጀቶች ላይ እንኳን ለመስማማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መጪውን መንገድ ረጅም እና አስቸጋሪ ያደርገዋል። ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ባለው ጊዜ ውስጥ ግጭቶች መቀነሳቸ መልካም ለውጥ ቢሆንም በቅርቡ በነቀምት የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ በመጋቢት 21 ቀን መገደላቸው ጥሩ ውጤት አያመጣም። ይፋዊ ውይይት በቅርቡ ካልተጀመረ በቀር የኦሮሚያ ክልል ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊመለስ ይችላል።
በትግራይ ክልል ተመሳሳይ ሁኔታዎች አሉ። እስካሁን ድረስ አዎንታዊ የሰላም ሂደት ቢኖርም የምዕራብ እና የደቡብ ትግራይ ዞኖች ሁኔታን በተመለከተ ግልፅ መንገድ/መፍትሔ የለም። መጋቢት 10 ቀን በደቡብ ትግራይ ዞን አላማጣ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች መንግስት ከትግራይ ክልል በይፋ አካባቢያቸውን እንዲያነሳ ጠይቀዋል። በቅርቡ የተሾሙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ሰልፉን አውግዘዋል።13ቦርከና፣ ‘ራያ የማንነት ጥያቄውን አስመልክቶ ከፌዴራል መንግስት ህጋዊ ምላሽ ጠየቀ፣’ መጋቢት 11, 2015 የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚዲያ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቀዳሚ ተግባራት መካከል አንዱ ነው።14ዋዜማ ሬዲዮ፣ ‘ለቸኮለ! ዓርብ መጋቢት 15/2015 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች፣’ መጋቢት 15, 2015 የምዕራብ ትግራይ ዞን በተለይም ወልቃይት፣ ሁመራ እና ፀገዴ አካባቢዎች በይፋ በትግራይ ክልል ወሰን ውስጥ ቢሆኑም አሁንም በአማራ ክልል በተሾሙ ባለስልጣናት የሚተዳደሩ ናቸው። የአማራ ክልል ኃይሎች እነዚህን አካባቢዎች የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሲጀመር ተቆጣጥረዋል። ላለፉት 30 አመታት የምዕራብ ትግራይ ዞን የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት ሲሆን የምዕራብ ትግራይ ዞን የትግራይ ክልል አካል የሆነው በትህነግ/ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር – ከ1983 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ገዥው ጥምረት ፓርቲ – የብሄር ፌዴራሊዝምን ተግባራዊ ካደረገ በኋላ ነው። ለአማራ ክልል ነዋሪዎች የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ የብሔርተኝነት መገለጫ እየሆነ ሲሆን መንግስት አካባቢውን ለትህነግ/ህወሓት የሚመልስ ከሆነ መንግስት የትጥቅ ትግል እንደሚገጥመው በመላው አማራ የሚናፈሰ የተለመደ ወሬ ነው (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013፤ ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 እና የኢፒኦ ልዩ ዘገባ The Northern Ethiopia Conflict: A Step Towards Peace? ይመልከቱ)።
በተጨማሪም የሰላም ስምምነቱ ፌዴራል ያልሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት እንዳለባቸው በግልፅ ቢደነግግም በመጋቢት ወር የኤርትራም ሆነ የአማራ ኃይሎች በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ እና ይህም አካባቢውን እንዲለቁ በፌዴራል መንግስት በኩል ፍላጎትም ሆነ ቁጥጥር አለመኖሩን ያሳያል።15ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ‘የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ የመውጣት ሂደት “ዘገምተኛ ሆኗል” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክትል ኮሚሽነር ተቹ፣’ የካቲት 27, 2015
በአጠቃላይ በየካቲት እና መጋቢት 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የታዩት የግጭት አዝማሚያዎች ከወራት በፊት ከነበሩት በእጅጉ የተለዩ ሲሆኑ ይህም የግጭት ሊጨምር እንደ የሚችል ያሳያል። የዚህ ለውጥ ማእከል በኢትዮጵያ ውስጥ በኃይማኖት፣ በጎሳ እና በርዕዮተ ዓለም ቡድኖች መካከል አዲስ የፀጥታና የፖለቲካ ትብብር ጥምረት መፈጠር እና መገጣጠም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ገዥው የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞ ብሔርተኛ የፖለቲካ ጥያቄዎች በማስተናገድ እና እነዚህ ጥያቄዎቹ በመንግስት ላይ የበላይነት እንዲኖራቸው አድርገዋል በሚል በፓን-ኢትዮጲያውያን (የኢትዮጵያ እንድነት የሚደግፉ) እና በአማራ ክልል የፖለቲካ አካላት እየተከሰሱ ነው።16ቦርከና፣ ‘አዎ! አብይ አህመድ ስልጣን መልቀቅ አለባቸው፣’ መጋቢት 27, 2015 በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንን የሚመለከቱ ግጭቶች እነዚህ ለውጦች ወደ ግጭት እንዴት እንደሚገለጡ አንዱ ማሳያ ነው (በእነዚህ ሁኔታ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ከጥር 24 እስከ የካቲት 21, 2015 ወርሃዊ፡ የኃይማኖት አለመግባባቶች እና የመንግስት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ይመልከቱ)። በኢትዮጵያ የሰሜኑ ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መጋቢት ወር ዝቅተኛው ግጭት እና ግድያ የታየበት ወር መሆኑ አዎንታዊ ምልክት ነው፣ ከእነዚህም መካከል በሀገሪቱ መረጋጋት እንደሚቀጥል እና የሰላም ሂደቶች ተፋላሚ ወገኖችን ወደ አንድ ማምጣት ሊሳካ ይችላል። ሆኖም ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የተፈጠረውን ስስ ሚዛን የሚያናጉ እና ግጭት እንዲመለስ ሊያደርጉ የሚችሉ አሳሳቢ ጉዳዮች አሉ።