በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሚያዚያ 14, 2014-ሚያዚያ 20, 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,106
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 5,997
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,600
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሚያዚያ 14-20, 20151በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 8
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 26
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 8
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
የአማራ ክልል በሀገሪቱ ካሉት ክልሎች መካከል በጣም ያልተረጋጋ ክልል ሆኖ ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሚያዚያ 16 ቀን በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና በባህር ዳር እና ሚያዚያ 17 ቀን በደብረ ማርቆስ ከተማ ጠዋት ላይ የንግድ ማዕከላት በመዘጋታቸው የቤት ያለመውጣት አድማ ምልክቶች በመታየታቸው በክልሉ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷ ነበር። ነገር ግን ከአንድ ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ አንድ እማኝ እንደተናገሩ ከሆነ እኩለ ቀን ላይ በእነዚህ ከተሞች መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ተናግረዋል። በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ማንነቱ ያልታወቀ አካል መንግስትን በመቃወም በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር የተዘገበ ሲሆን በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎችም በራሪ ወረቀቶች መበተናቸው ተነግሯ።2የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን፣ ‘ኢትዮጵያ -ኢሳት የአማርኛ ዜና ሚያዝያ 17, 2015፣’ ሚያዝያ 17, 2015፤ ኢሳት፣ ‘ኢትዮጵያ -ኢሳት የአማርኛ ዜና ሚያዝያ 18, 2015፣’ ሚያዝያ 18, 2015 የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማድቀቅ እና የህዝቡ ኑሮ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር እየተንቀሳቀሱ ናቸው ያሏቸውን ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት አስጠንቅቀዋል።3አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ‘የሥራ እንቅስቃሴን በመገደብ የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲደቅቅ እና የሕዝቡ ኑሮ እንዲጎሳቆል የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ እንደሚገባ ተገለጸ፣’ ሚያዝያ 15, 2015
ሚያዚያ 18 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፈራታና ግድም ወረዳ በአላላ ቀበሌ ውስጥ ወይም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢ ባልታወቀ ቦታ ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጠቂ ቡድን ወደ እርሻቸው እየሄዱ በነበሩ አርሶ አደሮች ላይ ተኩስ ከፍቷል። እንደ እማኞች ገለጻ ከሆነ ጥይቱ የተተኮሰው ከጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ ነው። በጥቃቱ አንድ ሰው ቆስሏል። ከ2010 ጀምሮ በሁለቱ ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች በየጊዜው ይቀሰቀሳሉ።
ከአንድ ቀን በኋላ ሚያዝያ 19 ቀን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን ይጓዙ በነበሩ ተሸከርካሪዎች ላይ የአድፍጦ ጥቃት በመንዝ ጉዋሳ አካባቢ ያደረጉ ሲሆን (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ) በዚህም ጥቃት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ እና የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን አቶ ግርማ የሺጥላን፣ ሹፌራቸውን፣ ጥበቃዎቻቸውን እና ሌሎች የአካባቢው ባለስልጣናት ጨምሮ ስድስት ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል።4አሚኮ፣ ‘ከአቶ ግርማ የሺጥላ ጋር በጉዞ ላይ የነበሩ ተጨማሪ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፣’ ሚያዝያ 22, 2015 በጥቃቱ የአቶ ግርማ ባለቤትን እና የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ሌሎች 14 ሰዎች ቆስለዋል። “የክልሉን ስልጣን በኃይል ለመቆጣጠር አላማ ያደረጉ ጽንፈኞች ኃይሎችን” ለግድያው ተጠያቂ ያደረገው የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ ግድያው ግብረ ኃይሉን ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ አድርጎታል።5ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ‘በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር በሚጥሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፣’ ሚያዝያ 20, 2015 በመሆኑም ግብረ ኃይሉ የ“ጽንፈኞች” ኔትወርክ አባላት ናቸው ያላቸውን እና “በአሸባሪነት” ተግባር ውስጥ ተሳትፈዋል ያላቸውን 47 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሏል። ግብረ ኃይሉ በአብዛኛው በምዕራባውያን አገሮች የሚኖሩ “ተፈላጊ ሰዎችን” ስም ዝርዝርም አውጥቷል።6የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ‘ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ፣’ ሚያዝያ 22, 2015 በአማራ ክልል በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሲነፃፀር አነስተኛና ያልተለመደ ቢሆንም የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ አልፎ አልፎ ተፈጽሟል። ሰኔ 2011 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት “መፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ሲል በገለፀው በአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የሚመራ ኃይል የአማራ ክልል ፕሬዝዳንትን እና ሌሎች ስድስት የክልሉ መንግስት አባላት ተገድለዋል።7 ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት – ኢትዮጵያ፣ ‘በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ ዝርዝር ጋዜጣዊ መግለጫ፣’ ሰኔ 16, 2011
በተመሳሳይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ሃና ከተማ የመስክ ጉብኝት በማድረግ ላይ የነበሩ አንድ የሳላማጎ ወረዳ ከፍተኛ ኃላፊን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ተኩሰው ገድለዋል። ይህ ግድያ በአካባቢው በቦዲ እና በደሚ ጎሳ አባላት መካከል ግጭት አስነስቷል። የየትኛው ጎሳ አባል እንደሆኑ ግልጽ ባይሆንም የተገደሉት ኃላፊ ከእነዚህ ጎሳዎች የአንዱ ጎሳ አባል ነበሩ። በግጭቱ 10 ሰዎች ሲሞቱ ስድስት ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ቢያንስ 13 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።8የአሜሪካ ድምፅ አማርኛ፣ ‘በደቡብ ኦሞ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ግጭት 22 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ፖሊስ ገለጸ፣’ ሚያዚያ 23, 2015
በተጨማሪም በሚያዝያ 14 ቀን ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በደራሼ ልዩ ወረዳ በጋቶ ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ሁለት ሰዎችን ገድሎ አምስት ሰዎችን አቁስሏል። ጥቃቱ የተከሰተው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ኃይል በቅርቡ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅር እንዲገቡ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ አካባቢውን ለቀው ከወጡ በኋላ ነው (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: መጋቢት 23-29, 2015ን ይመልከቱ)። ቡድኑ በቀበሌው በሚገኘው የመለስ ዜናዊ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበረን ምግብ ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ዘርፏል። ይህ ታጣቂ ቡድን ቀበሌው በከተማ ደረጃ እውቅና እንዲሰጠው ጥያቄ የሚያቀርብ ነው። ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።9ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘በደቡብ ኦሞ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ግጭት 22 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ፖሊስ ገለጸ፣’ ሚያዚያ 23, 2015
ከአንድ ቀን በኋላ ሚያዚያ 15 ቀን በጉራጌ ዞን በኤኖር ኤነር ወረዳ ጉንችሬ ከተማ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሱቆች ላይ የእስልምና ተከታይ የሆኑ ስዎች ጥቃት ያደረሱ ሲሆን በማግስቱ አጸፋውን ለመመለስ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑ ሰዎች የሙስሊሞችን ሱቆች በማጥቃት ሱቆችን አቃጥለዋል። የሁከቱ መሠረታዊ መነሻ በሙስሊም እና በኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተማሪዎች መካከል በጉንቺሬ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትምህርት ቤት የአለባበስ ሥርዓት ላይ – ቡርቃ (የሙስሊም ሙሉ ሰውነት የሚሸፍን ልብስ) እና ነጠላ (የኦርቶዶክስ ክርስትያን ራስ መሸፈኛ) መለበስ እንዲፈቀድ – በተነሳ አለመግባባት ሲሆን ምንም እንኳን ተማሪዎች እና ወላጆች ቀደም ሲል ተማሪዎች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ብቻ እንዲለብሱ በመስማማት ትምህርት የቀጠለ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በከተማው በሁለት ወጣቶች መካከል የተፈጠረ ግጭት በሁለቱ ቡድኖች መካከል አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል።10አዲስ ማለዳ፣ ‘በደቡብ ክልል በልዩ ኃይል መፍረስ የተፈጠረው ግጭት፣ በደብረ ብርሃን የተፈናቃዮች የደኅንነት ስጋት፣ በጉራጌ ዞን የነዋሪዎች ቤት ውድመት፣’ ሚያዚያ 16, 2015
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ሳምንት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሶስት ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል። ሚያዚያ 16 ቀን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በምስራቅ ሸዋ ዞን በፋንታሌ ወረዳ ጊዳራ ቀበሌ አራት ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። ተጎጂዎቹ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ተጠርጥረው ነበር። ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ከሶስት ወራት በፊት ታስረው የነበሩ ሲሆን ከእስር ቤት ተወስደው በጥይት ተመተው ተገድለዋል። ከሁለት ቀናት በኋላ ሚያዝያ 18 ቀን በምዕራብ ሸዋ ዞን በግንደ በረት ወረዳ በጮኔ ቀበሌ በድጋሚ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት እንደሆኑ የሚገመት የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከቤተሰቦቹ ጋር በእርሻ ላይ የነበረን አንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪን ገድለዋል። ሚያዝያ 19 ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት ናቸው ተብለው የተገመቱ ታጠቂዎች ከአላማጣ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ አውቶቡስ ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ እና ወለንጭቲ ከተሞች መካከል በሚገኝ ቦታ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በጥቃቱ ምክንያት አሽከርካሪው እና ረዳቱ የተገደሉ ሲሆን በእረፍት ላይ የነበሩ (ስራ ላይ ያልነበሩ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ አምስት ሰዎች ቆስለዋል። ታጣቂ ቡድኑ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ከአንድ ሚኒባስ ውስጥም አፍኖ ወስዷል።11አዲስ ማለዳ፣ ‘ከአላማጣ በተነሱ መንገደኞች ላይ በመተሀራ በተፈፀመ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ፣’ ሚያዚያ 22, 2015
በመጨረሻም ሁሉም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እና የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከንቲባዎች እንዲሁም ሌሎች ባለስልጣናት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ጋር ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ ተገናኝተዋል። የልዑካን ቡድኑን የመሩት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ናቸው። ጉብኝቱ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ ለመገንባት ያለመ ሲሆን12ሪፖርተር፣ ‘የክልል አመራሮች ከትግራይ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ጋር በመቀሌ ተገናኙ፣’ ሚያዝያ 19, 2015 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሁሉም የክልል ፕሬዝዳንቶች ትግራይን እንዲጎበኙ ሀሳብ ካቀረቡ ከቀናት በኋላ የተደረግ ጉብኝት ነው። ይህንን ሃሳብ ያቀረቡት ሚያዚያ 15 ቀን በአዲስ አበባ በሰሜን ኢትዮጵያ ሠላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጀ ስነ-ሥርዓት ላይ ነው። በስነ-ሥርዓቱ ላይ የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) መሪዎች፣ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ ቡድን አባላት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የድርድር ቡድን አባላት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እና የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስጋና የምስክር ወረቀት እና የሠላም ምልክት ተሸልመዋል።13የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ‘#ኢቲቪ ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናጽና’ ሚያዚያ 15, 2015