በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 3, 2014-ሰኔ 9, 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,103
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 5,676
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,587
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 3-9, 20151 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 19
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 100
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 35
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አለመረጋጋት እንደቀጠለ ሲሆን የተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ በአንፃሩ ሰላማዊ ሆኖ ቆይቷል። በአማራ ክልል የተዘገቡት የፖለቲካ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች መንግስት ‘በጽንፈኛ’ ኃይሎች ላይ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የተለያዩ የኩነት አይነቶች ተመዝግበዋል። በክልሉ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግስት ኃይሎች የተሳተፉባቸው ሶስት የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሰኔ 3 ቀን የፋኖ ታጣቂ አባላት ከምዕራብ ጎጃም ወደ አዊ ዞን በመግባት የወረዳ ባለስልጣናት አፍነው ለመውሰድ ባደረጉት ሙከራ – የአማራ ክልል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች እንደሆኑ ከተገመቱ – የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተዋግተዋል። ከውጊያው በኋላ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና የአካባቢው ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩትን የወረዳ ባለስልጣናት ማስለቀቅ ችለዋል። የወረዳ ባለስልጣናትን ለማስፈታት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ሲሞክሩ የነበሩ የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ታውቋል። በማግስቱ በሰሜን ሸዋ ዞን መራቤቴ እና ሚዳ ወረሞ የፋኖ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተዋግተዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች በመንግስት ‘ፅንፈኛ’ ኃይሎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም መንገድ መዝጋታቸውን ቀጥለዋል (ስለ ኦፕሬሽኑ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 21- ግንቦት 11, 2015 እና ኢፒኦ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2015 ወርሀዊን ይመልከቱ)። ሰኔ 4 ቀን በደምበጫ ከተማ ወጣቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በከተማቸው መግባቱን በመቃወም ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ መንገዶችን የዘጉ ሲሆን በምላሹ የተዘጋውን መንገድ ለማስከፈት እና ስልፈኞቹት ለመበተን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ተኩስ ከፍተዋል። ይህን ተከትሎ በተነሳው ግጭት ሁለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን እና ሦስት ስልፈኞችን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሞተዋል። ወደ 18 የሚጠጉ ሰዎችም ቆስለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው የገባው በደብረ ኤልያስ ወረዳ በስላሴ እንድነት ገዳም ከግንቦት 18 እስከ 22 ድረስ በተፈጠረው ውጊያ ይፈለጋል የተባለውን የአማራ ህዝባዊ ግንባር አመራር የሆነውን እስክንድር ነጋን ለማሳደድ እንደሆነ ተዘግቧል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 19-25, 2015 ይመልከቱ)። ሰኔ 5 ቀን ስልፉ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም እና ጅጋ ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን ሰልፈኞች በከተሞቻቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መኖሩን በመቃወም ዋና መንገዶችን ዘግተዋል። በፍኖተ ሰላም የፖሊስ አባል በህዝቡ ላይ ተኩስ ከፍቶ እንድ ተቃዋሚን ሲገድል ከስምንት በላይ አቁሱሏል። በአማራ ክልል እየታየ ባለው “የፀጥታ ችግር” ምክንያት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልሉ መረጋጋት እንዲሰፍን መንግስት የሰላም ድርድር እንዲጀምር ጠይቋል።2አዲስ ማለዳ፣ ‘በአማራ ክልል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ተጠየቀ፣’ ሰኔ 11, 2015
በክልሉ ውስጥ ሁለት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ የጥቃት ኩነቶችም ተመዝግበዋል። ባለፈው ሳምንት የፋኖ ታጣቂዎች በመራቤቴ ዙሪያ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ ሰላማዊ ሰውን ከአውቶቢስ ውስጥ ጎትተው አውርደው ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። በተጨማሪም ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 8 ባለው ጊዜ ውስጥ የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ለጊዜው ስሙ ባልተጠቀሰ መንደር አምስት የአማራ ተወላጆችን በጥይት ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። ድርጊቱ የተከሰተው በተከዜ ወንዝ አካባቢ በትግራይ እና በአማራ ክልል መካከል ውዝግብ ባለበት አካባቢ ነው።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እንደቀጠሉ ነው። አክሌድ በክልሉ ውስጥ ሰባት የውጊያ ኩነቶችን መዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ የውጊያ ኩነቶች በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች – በአብዛኛው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት – መካከል የተደረጉ ናቸው። የአማፂ ቡድኑ አባላቱን ለማስፈታት በምሽት እስር ቤቶችን የማጥቃት አዲሱ አካሄድ ምክንያት ከመንግስት ኃይሎች ጋር መዋጋቱን ቀጥሏል። ሰኔ 4 ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን ዝዋይ ሀይቅን በጀልባ አቋርጠው ወደ ባቱ (ዝዋይ) ከተማ ገብተው ሀይቅ ዳር (የቅድሞ ጤና ጣብያ) አካባቢ ከሚገኝ እስር ቤት አባላቱን ለማስለቀቅ ሲሞክሩ ከመንግስት የፀጥታ ኃይሎች – የእስር ቤት ጠባቂዎች እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ – ጋር ተዋግተዋል። በዚህ ውጊያ ሶስት ፖሊሶች እና አንድ የኦነግ-ሸኔ አባል መሞታቸው ታውቋል። ከግንቦት ወር ጀምሮ ቡድኑ በክልሉ ቢያንስ አራት ቦታዎች በሚገኙ እስር ቤቶች ላይ ጥቃት የፈፀመ ሲሆን ይህም ከመንግስት ኃይሎች ጋር ውጊያ አስከትሏል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ሸዋ ዞን በሜታ ሮቢ፣ ጀልዱ እና አዳ በርጋ ወረዳ የኦነግ-ሸኔ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተዋግተዋል። ሰኔ 9 ቀን ኦነግ-ሸኔ በሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ ጉምቢቹ ቀበሌ ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር ከተዋጋ በኃላ ቀበሌዋን መቆጣጠሩ ተነግሯል።3አዲስ ማለዳ፣ ‘የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በምትገኝ ወረዳ አንድ ቀበሌ መቆጣጠራቸው ተገለጸ፣’ ሰኔ 11, 2015
በምስራቅ ወለጋ ዞን ተጨማሪ ሁለት የውጊያ ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሰኔ 8 ቀን በኪረሙ ወረዳ ዋሴት ቀበሌ የፋኖ ታጣቂዎች በመግባት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ካደረሱ በኃላ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስና ከቀበሌ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። የፋኖ ታጣቂዎች ወደ መንደሩ በመግባት ተኩስ ከፍተው ስምንት ሰላማዊ ሰዎችን ገድለው 13 ሰላማዊ ሰዎችን ማቁሰላቸው ተዘግቧል። ቡድኑ እንስሳትን የዘረፈ ሲሆን የሰላማዊ ሰዎችን ንብረቶችን አውድሟል። በማግስቱ ኦነግ-ሸኔ ከአማራ ብሔር ታጣቂዎች ጋር በኪረሙ ተዋግቷል። በውጊያው ቢያንስ ሶስት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በክልሉ በተለያዩ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችም ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት አብዛኞቹ እነዚህ ጥቃቶች የተፈፀሙት በምዕራብ ኦሮሚያ ነው። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች በዋሰት ቀበሌ የተፈፀመውን ጥቃት ጨምሮ የፋኖ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሶስት ጥቃቶችን መፈፀማቸው ተነግሯል። በተጨማሪም ሰኔ 7 ቀን በምስራቅ ወለጋ ዞን በሲቡ ስሬ ወረዳ በበካኒሳ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት አምስት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ከተጎጂዎቹ ውስጥ ሁለቱ የኦነግ-ሸኔ አባላት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ እነርሱን ደብቀዋል በሚል ተከስዋል። በሌላ በሰሜን ሸዋ ዞን የኦነግ-ሸኔ አባላት በደብረ ሊባኖስ አንድ ሰላማዊ ሰው ተኩሰው ገድለው ሰባት ሰዎችን ማገታቸው ተነግሯል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን በየኪ ወረዳ ባያ ቀበሌ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የፖሊስ መኪናን አድፈጠው በማጥቃታቸው የጋምቤላ ክልል የጎደሬ ወረዳ ፖሊስ ኮማንደርን ገድለው አንድ ፖሊስን መኮንን አቁስለዋል። ፖሊሶቹ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚዛን ከተማ ስልጠና ወስደዋል ወደ ጎደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ እየተመለሱ ነበር። ሰኔ 9 ቀን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለስልጣናት የድርጊቱን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።4የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን፣ ‘ኢትዮጵያ-ኢሳት አማርኛ ዜና ሰኔ 9, 2015፣’ ሰኔ 9, 2015
በመጨረሻም በአፋር ክልል አንድ የአፋር ክልል ፖሊስ አባል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል መገደሉን ተከትሎ ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን መተሐራን ከድሬዳዋ እና ከሀረር የሚያገናኘው ዋናው መንገድ ተዘግቶ ነበር።5 አዲስ ማለዳ፣ ‘የአፋር ክልል ፖሊስ አባል በመከላከያ መገደሉን ተከትሎ የአዋሽ አርባ መንገድ መዘጋቱ ተገለጸ፣’ ሰኔ 10, 2015 ከግድያው በስተጀርባ ያለው ምክንያት አልታወቀም።