በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 24, 2014-ሰኔ 30, 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,067
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 4,832
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 2,128
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 24-30, 20151በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 12
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 48
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 7
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በአካባቢው የፀጥታ ኃላፊዎች ላይ የሚደርሰው ግድያ የቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እንደቀጠሉ ነው። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ከብሔር ግጭት ጋር የተያያዘ እንደሆነ በተገመተ ምክንያት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በርካታ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የጉሙዝ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች የፀጥታ ኃላፊዎችን ኮንቮይ መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት ካደረሱ በኃላ ግጭት ተቀስቅሷል።
በአማራ ክልል በአካባቢው የፀጥታ አባላት ላይ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመ ግድያ ቢያንስ አራት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ሰኔ 26 ቀን በምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ከተማ ታጣቂዎች በፖሊስ መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት አድርገው የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥን እና ምክትላቸውን ሲገድሉ የተሽከርካሪውን ሹፌር አቁስለዋል። በማግስቱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የሸዋ ሮቢት ከተማ የፀጥታ ክፍል ኃላፊን በጥይት መተው በመግደላቸው የፀጥታ ኃላፊዎች በከተማው ከረፋድ እስከ ማለዳ የሚቆይ የሰዓት እላፊ አዋጅ እንዲያውጁ አድርጓቸዋል። ነገር ግን የሰአት እላፊው እያለ ሰኔ 29 ቀን ታጣቂዎች ምሽት በስራ ላይ የነበረ ፖሊስን ተኩሰው ገድለዋል።
ልዩ ኃይል ፈርሶ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ የፀጥታ አካላት እንደሚቀላቀል መንግስት ይፋ ካደረገ ወዲህ በአማራ ክልል ውጊያዎች፣ ግድያዎች እና ሞትን ያስከተሉ ሰልፎች እየተለመዱ መተዋል። ከትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ጋር በተደረገው ድርድር ቀድሞውንም ከፍተኛ የነበረው የፖለቲካ ውጥረት ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል ጋር የተያያዙ የማንነት እና የወሰን ጉዳዮችን ለመፍታት ህዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ የክልሉ ባለስልጣናት ካሳወቁ በኋላ እንደገና ውጥረቱ ተባብሷል2አዲስ ስታንደርድ፣ “ዜና፡ የአማራ ክልል የማንነት ጥያቄዎችን፣ ከትግራይ ክልል ጋር ያሉ የድንበር ችግሮችን በህዝበ ውሳኔ ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ፣” ሐምሌ 1, 2015 (በአማራ ክልል ስላለው የግጭት እና ደህንነት አዝማሚያ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2015 ወርሀዊ ሪፖርትን ይመልከቱ) ።
በኦሮሚያ ክልልም ግጭት የቀጠለ ሲሆን በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ቱቺሱ እና በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አሰበ ተፈሪ በኦነግ-ሸኔ እና የኢትዮጵያ የፌደራል ጦር ወታደሮች መካከል ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ባለፈው ሳምንት በወጣ እንድ ሪፖርት መሠረት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረ መሆኑን በመግለጽ ግጭቶቹ በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች በሚገኙ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያለውን ችግር አጉልቶ አሳይቷል።3ሥዩም ጌቱ፣ ሸዋዬ ለገሠ፣ ኂሩት መለሰ፣ ‘በኦሮሚያ ክልል የጤናው ዘርፍ ችግር፣’ ዶይቸ ቬለ አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2015
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከበርካታ ወራት አንጻራዊ ሰላም በኋላ የጉሙዝ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች ግልገል በለስ ከተማ አቅራቢያ የፀጥታ ኃላፊዎች ኮንቮይ መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት በማድረስ 18 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ግጭት ተቀስቅሷል። ጥቃቱ የተፈጸመው የፀጥታ ኃይሎች ከአንድ ቀን በፊት በቡድኑ የተገደለን የሰላማዊ ሰው አስከሬን ለማንሳት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት ነው።
በመጨረሻም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ በበቼ ቀበሌ ከማረቆ ብሔር ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሶስት ተማሪዎችን ጨምሮ አምስት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። የማረቆ እና የመስቃን ህዝቦች በጉራጌ ዞን የሚኖሩ እና የራሳቸው ወረዳ – ማረቆ እና መስቃን ወረዳ ያላቸው ብሔረሰቦች ናቸው። በመስቃን ወረዳ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ በሚነሳ የባለቤትነት ጥያቄ ምክንያት በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ አለመግባባት አለ።4ጌታሁን አስናቀ፣ ‘በጉራጌ ዞን በታጠቁ ኃይሎች አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል፣’ አዲስ ማለዳ፣ ሰኔ 27, 2015፤ ቦርከና፣ ‘በመስቃን ጉራጌ በተፈጠረው ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸው ተነግሯል፣’’ ግንቦት 11, 2012 ሰኔ 28 ቀን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በመስቃን ወረዳ ብሔራዊ ፈተና በሚወስዱ ተማሪዎች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው በድጋሚ ግጭት ተቀስቅሷል። አዲስ የታቀደውን የአስተዳደር መዋቅር በመቃወም የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስዎች ከታሰሩ በኃላ ከህዳር 2015 ዓ.ም ጅምሮ የጉራጌ ዞን በወታደራዊ ኮማንድ ስር ይገኛል።