በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሐምሌ 1, 2014-ሐምሌ 8, 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,068
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 4,634
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 1,965
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሐምሌ 1-7, 20151በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 16
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 25
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 11
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያች እና በፀጥታ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ግድያ የቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ኃይሎች ከመንግስት ኃይሎች ጋር ተዋግተዋል። በጋምቤላ ክልል እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልም ግጭቶች ተከስተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በቆቦ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች ሐምሌ 6 ቀን በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ኃይሎች መካከል ውጊያ የነበረ ሲሆን ቢያንስ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል። ውጊያው ከመከሰቱ ከሶስት ቀናት በፊትም የፋኖ አባላት በቆቦ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ የእጅ ቦምቦችን በመወርወር በፖሊስ ጣቢያው ታስረው የነበሩ እስረኞችን መፍታታቸውን እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኃይሎች ጋር ውጊያ መቀስቀሱን ታውቋል። ሐምሌ 7 ቀን ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ ሰራ ላይ የነበረ ፖሊስ አዛዥን ተኩሰው ገድለዋል። የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጅማ ከተማ በተካሄደው የሠራዊቱ የማዕከላዊ ዕዝ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር የፋኖ ታጣቂ አባላት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በመጠየቅ የመከላከያ ሠራዊትን “ከፋኖ ጋር የሚያዋጋ አጀንዳ አለመኖሩን” ተናግረዋል2ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ‘የመከላከያ ሰራዊትን “ከፋኖ ጋር የሚያዋጋ አጀንዳ አለመኖሩን” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፣’ ሐምሌ 4, 2015 (በአማራ ክልል ስላለው የፖለቲካ ግጭት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ግንቦት 24- ሰኔ 23, 2015ን ይመልከቱ)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን በጨንቃ፣ መቻራ፣ ሮብ ገበያ እና ጋቦኦ ሮቢ ከተሞች የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኃይሎች ጋር ተዋግተዋል። በዚህ ምክንያት ከሁለቱም ወገን በርካታ ተዋጊዎች እንዲሁም ቢያንስ ሰባት ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። ሐምሌ 5 ቀን በመንግስት የተቋቋመውን አዲስ የምስራቅ ቦረና ዞን አስተዳደር መዋቅር እና የአካባቢው ባለስልጣናት በፀጥታ አካላት መታሰራቸውን በመቃወም በጉጂ ዞን ሁከት ፈጣሪ ወጣቶች ተሽከርካሪዎችን በማቃጠል መንገዶችን ዘግተዋል። እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ረብሻው የጀመረው የአካባቢው አመራሮች ከጎሮ ዶላ ወደ ነጌሌ ለስብሰባ በተጓዙበት ወቅት በክልሉ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኃላ ነው3ሥዩም ጌቱ፣ እሸቴ በቀለ እና ነጋሽ መሐመድ፣ ‘የፀጥታ ስጋት የፈጠረው ግጭት በጉጂ ዞን፣’ ዶይቸ ቬለ አማርኛ፣ ሐምሌ 7, 2015 (የምስራቅ ቦረና ዞን መመስረትን በመቃወም ስለተነሱ ሰልፎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከየካቲት 18–24, 2015 ይመልከቱ)።
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ሁለት የተቃውሞ ሰልፎች በመዲናዋ መቀሌ ተመዝግበዋል። የመጀመሪያው በሐምሌ 2 ቀን የተካሄደው በትግራይ የተፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት ያወገዘ ሲሆን ተቃዋሚዎች የመንግስት ባለስልጣናት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በማግስቱ የተካሄደው ሁለተኛው የተቃውሞ ሰልፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ የሚገኘውን የስደተኞች ካምፕ መጎብኘቱን አውግዟል። ተቃዋሚዎቹ በግጭቱ ወቅት የቤተክርስቲያኑ አመራር አባላትን ትተዋል ሲሉ ከሰዋል።
በጋምቤላ ክልል ሐምሌ 6 ቀን የአኝዋ ብሔር ታጣቂዎች ወደ ዋና ከተማዋ ጋምቤላ በመጓዝ ላይ በነበረ በህዝብ አውቶብስ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ቢያንስ የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 23 ቆስለዋል። በተመሳሳይ ቀን በሌላ አውቶብስ ላይ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሔር ታጣቂዎች በኢታንግ ልዩ ወረዳ ጥቃት አድርሰዋል። ጋምቤላ ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ከነበሩ ክልሎች አንዱ የነበረ ሲሆን ከሰኔ 2014 ጀምሮ ግን ተለዋዋጭ እና ያልተጠበቁ ግጭቶች በክልሉ እየተፈፀሙ ነው።
በመጨረሻም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አሌ ልዩ ወረዳ ከሚገኝ ገበያ ተነሥተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የነበሩ ሦስት ሰዎችን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ተኩሰው መግደላቸው ተዘግቧል። በአሌ ልዩ ወረዳ ከብሔር እና ከወሰን ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ጥቃቶች በየጊዜው ይከሰታሉ (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።