በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሐምሌ 15, 2014-ሐምሌ 21, 2015
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,052
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 4,445
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 1,931
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሐምሌ 15-21, 20151በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 11
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 49
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 3
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል ባለፈው ሳምንት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በርካታ ውጊያዎች የተዘገቡ ሲሆን በአንፃራዊ የተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ሰላማዊ ሆኖ ሰንብቷል። ባለፈው ሳምንት አክሌድ በአማራ ክልል በመንግስት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ስምንት የውጊያ ኩነቶችን መዝግቧል። እነዚህ ውጊያዎች በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ወሎ፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር እና በደቡብ ወሎ ዞኖች የተመዘገቡ ስሆን (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ) አብዛኛዎቹ ውጊያዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የተደረጉ ናቸው። ከእነዚህ ውጊያዎች በተጨማሪ ሐምሌ 16 ቀን በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ ወጣቶች መንገድ በመዝጋት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተይዟል የተባለ የፋኖ አባል እንዲፈታ ጠይቀዋል። በምላሹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥይት በመተኮሱ ሁለት ሰዎችን ሲገድል ስድስት ሌሎች ሰዎችን አቁስሏል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮችም ቆስለዋል።
መንግስት በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅር እንደሚቀላቀሉ ከተናገረ ጊዜ ጀምሮ የአማራ ክልል በሀገሪቱ ካሉት መረጋጋት ከጎደላቸው ክልሎች አንዱ ሆኗል (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2015 ወርሀዊ ሪፖርትን ይመልከቱ)። ከመጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ በመንግስት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ አብዛኛው ውጊያዎች በሰሜን ሸዋ እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ተመዝግበዋል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት በሰሜን ሸዋ ዞን የቤት ለቤት ፍተሻ ሲያደርጉ የፋኖ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ ብለው የተጠረጠሩትን ወይም ፋኖን የሚደግፉ ሙዚቃዎችን እና ምስሎችን በስልካቸው በማውረድ (በመጫን) የተጠረጠሩ ነዋሪዎችን እንደደበደቡ ተነግሯል።2ጌታሁን አስናቀ፣ ‘በሸዋሮቢት ከተማ የጸጥታ ኃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻ እና ወከባ እየፈጸሙ ነው ተባለ፣’ አዲስ ማለዳ፣ ሐምሌ 23, 2015 ሐምሌ 21 ቀን አንድ ሰላማዊ ሰው በጥይት ተመቶ መገደሉን እና ሌላ አንድ ሰው ደግሞ ተደብድቦ መገደሉ ተዘግቧል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት የክልሉ ፕሬዝዳንት የክልሉን የፀጥታ አማካሪን እና የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊን ከስልጣናቸው አንስተዋል። የክልሉ የፀጥታ አማካሪ ከኃላፊነት የተነሱት “ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ነው” ቢባልም የፀጥታ አማካሪው ግን ይህንን ክስ ውድቅ በማድረግ ከስልጣናቸው ከመነሳታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ ጥሩ ግምገማ ተስቷቸው እንደነበር አስረድተዋል።3አማኑኤል ይልቃል፣ ‘የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የጸጥታ አማካሪ ከስልጣናቸው ተነሱ፣’ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 19, 2015 የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ከስልጣን የመነሳታቸው ምክንያት ምን እንደሆነ አልታወቀም።
በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል በአኙዋክ እና በኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭት ቀጥሏል። ሐምሌ 17 ቀን የአኙዋክ እና የኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች በኢታንግ ልዩ ወረዳ ሑልዴ ቀበሌ ውስጥ የተዋጉ ሲሆን በዚህም ቢያንስ 12 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በእነዚህ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተከስተው ግጭት የጀመረው በሐምሌ ወር መጀመሪያ ነበር (ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 8-14, 2015 ይመልከቱ)።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሐምሌ 16 ቀን በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ በበቼ ቀበሌ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሦስት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው መግደላቸው ተሰምቷል። ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ በምስራቅ መስቃን ወረዳ የመስቃን እና የማረቆ ብሔረሰብ ሰላማዊ ሰዎች ላይ አዲስ ጥቃት መፈፀም ጀምሯል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 24-30, 2015 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 8-14, 2015 ይመልከቱ)።
በሀገሪቱ ካለው የማዳበሪያ እጥረት ጋር ተያይዞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አርሶ አደሮች የሚያካሂዱት ሰልፎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት የሀዲያ ዞን አርሶ አደሮች በሆሳዕና ከተማ ተቃውሞ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ የማዳበሪያ ኮታቸው ወደ አካባቢው ነጋዴዎች መተላለፉን እና ነጋዴዎቹ ያወጡትን ከፍተኛ ዋጋ በመሸፈን መግዛት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። የደቡብ ክልል ፖሊስ አባላት ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ዞን አስተዳደር እያቀኑ በነበሩ አርሶ አደሮች ላይ ወደ አየር በመተኮስ ድብደባ ፈጽመዋል። በድብደባው እና በመረጋገጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች ቆስለዋል። በሰልፉ ላይ የተሳተፉ 11 ሰዎችንም ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በቡራ ጃሌ እና ዋጂ ጉሽ ቀበሌዎች አርሶ አደሮች ለእርሻቸው ማዳበሪያ ጠይቀዋል። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን በመደብደብ እንዲበተኑ አድርገዋል።
በመጨረሻም ባለፈው ሳምንት የአካባቢ ባለስልጣናት ለፈጸሙት ‘ስህተት’ ይቅርታ የጠየቁባቸው ሁለት ከዚህ ቀደም ታይተው የማያውቁ ክስተቶች ተዘግበዋል። ሐምሌ 21 ቀን በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች ሰልፍ በማዘጋጀት በ“ብልሹ አሠራር፥ ጉቦ በመቀበል፥ ባለጉዳይን በማጉላላት እና የመንግሥትን የሥራ ሰዓት በመስረቅ” ህብረተሰቡን በአግባቡ አገልግሎት ባለመስጠታቸው ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።4ዮናታን ዘብዴዎስ፣ ‘ኅብረተሰቡን በተገቢው ባለማገልገላችን በድለናል ያሉ የሲዳማ ክልል ሠራተኞች በሰልፍ ይቅርታ ጠየቁ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 21, 2015 በተመሳሳይ በኦሮሚያ በጅማ ዞን የጌራ ወረዳ ኃላፊዎች የጸጥታ አካላት፣ የወረዳው ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ በቦርቾ ደቃ ቀበሌ በህዝብ ፊት አራት አርሶ አደሮችን አስገድደው ልብሳቸውን በማስወለቅ እንዲንበረከኩ ካደረጉ በኃላ በመደብደባቸው ምክንያት ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ የሆነው አርሶ አደሮቹ የመሬት ግብር ከከፈሉ በኋላ የግብር ደረሰኝ ከአካባቢው ባለስልጣናት ከጠየቁ በኃላ ነበር።5አዲስ ስታንደርድ፣ ሐምሌ 22, 2015 ይህን ድርጊት የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በማህበራዊ ድረ-ገጾች በስፋት ከተሰራጨ እና በህብረተሰቡ መካክል ቁጣ ከቀሰቀሰ በኃላ የዞኑ ባለስልጣናት ጥቃቱን በማውገዝ ድርጊቱን የፈፀሙ የአካባቢው ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።