በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 በጨረፍታ
- አበይት ክንውኖች
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ የተከሰቱ ቁልፍ ኩነቶች
- ወርሃዊ ትኩረት፡ በአማራ ክልል የአካባቢ ባለስልጣናት ለከፍተኛ ጥቃት መጋለጥ
ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 በጨረፍታ
አበይት ክንውኖች
- አክሌድ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ 87 የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች እና 273 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች መዝግቧል። አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ግጭቶች የተከሰቱት ከመጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግስት ኃይሎች እየተዋጉ በሚገኙበት በአማራ ክልል ነው።
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች የተመዘገበው በአማራ ክልል ሲሆን 50 ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሁለተኛው ከፍተኛ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች የተመዘገበው በጋምቤላ ክልል ሲሆን 14 ኩነቶች ተመዝግበዋል። በተቃራኒው ከፍተኛው በፖለቲካ ግጭት ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በጋምቤላ ክልል ሲሆን 129 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ሲመዘገብ በአማራ ክልል ሁለተኛው በፖለቲካ ግጭት ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ሲሆነ 82 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ተመዝግበዋል። በጋምቤላ በአኙዋክ እና በኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሟቾች ቁጥር ሪፖርት ተደርጓል።
- ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም ተደጋግሞ የተከሰቱት የኩነት ዓይነቶች ጦርነት እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲሆን 57 የጦርነት ኩነቶች እና 28 በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው የጦርነት ኩነት የተመዘገበው በአማራ ክልል ሲሆን ወደ ግማሽ የሚጠጋው በሰሜን ወሎ ዞን ተመዝግቧል።
ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ የተከሰቱ ቁልፍ ኩነቶች
ወርሃዊ ትኩረት፡ በአማራ ክልል የአካባቢ ባለስልጣናት ለከፍተኛ ጥቃት መጋለጥ
ከመጋቢት 2015 መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል ያለው አጠቃላይ አለመረጋጋት እየጨመረ ባለበት ወቅት ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሉ የአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን አክሌድ መዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በአማራ ክልል የፀጥታ አዛዦችን ጨምሮ ያለው አዲስ ዙር የአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ከዚህ በፊት በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎችም ተስተውሏል። ከጥቃት አድራሾቹ መካከል ምንም እንኳን የጥቂቶቹ ጥቃት አድራሾቹ ማንነት ብቻ ተለይቶ ቢታወቅም አብዛኛዎቹ ጥቃት አድራሾች ከብሔርተኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ይታሰባል። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ ጋር የተቆራኘ የአካባቢ አስተዳዳሪ መሆን በብዙ ቦታዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል አደገኛ ሆኗል። ከመጋቢት 2015 መጨረሻ ጀምሮ የአማራ ክልል አስተዳዳሪዎችም በእንደዚህ ያሉ ጥቃቶች ምክንያት ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ይህ ዘገባ በአማራ ክልል ከፍተኛ አለመረጋጋት በተፈጠረበት ጊዜ ይህን መሰል ጥቃቶችን የፖለቲካ አላማቸውን ለማሳካት ብሔርተኛ ቡድኖች በስፋት እየተጠቀሙ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በአካባቢ ባለስልጣናት ላይ እየጨምረ ስላለው የጥቃት ስጋት ይዳስሳል። ይህ በአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እና ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል ውስጥ የተመዘገበው መሰል ጥቃት የሚፈፀመው የፖለቲካ ውጥረት በበዛበት ወቅት ሲሆን የአካባቢ ባለስልጣናት ለታጣቂ ቡድኖቹ ተቃራኒ ፍላጎቶችን የሚወክሉ በመሆኑ ምክንያት ለዚህ ጥቃት ተጋላጭ ሆነዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተስተዋለው በአማራ ክልል ባሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት የተጀመረው በሰሜን ሸዋ ዞን ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ሃላፊ የነበሩትን አቶ ግርማ የሺጥላን ሚያዚያ 19 ቀን ከገደሉ በኋላ ነው (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ: ሚያዚያ 14-20, 2015ን ይመልከቱ)። ከግንቦት እስከ ሐምሌ ድረስ አክሌድ በአካባቢው ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ 10 ጥቃቶችን የመዘገበ ሲሆን ከነዚህ ጥቃቶች ውስጥ አራቱ የፀጥታ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። የእነዚህ የአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መጨመር በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ቤታቸውን እና ከተማቸውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል።1አዲስ ማለዳ፣ ‘የሸዋሮቢት ከተማ የመንግሥት የሥራ አመራሮች ወደ ደብረብርሃን እና አዲሰ አበባ ሸሽተዋል ተባለ፣’ ሐምሌ 11, 2015 ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አብዛኞቹ የጥቃቱ ፈጻሚ አካላት ተለይተው ባይታወቁም ከፋኖ ታጣቂዎች እና ከአማራ ብሔርተኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይገመታል። እነዚህ ሁለቱም ቡድኖች የክልል እና የፌዴራል መንግስታትን የአማራን ብሔርን ጥቅም ማስከበር አለመቻላቸውን እና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲቆጣጠሩ አድርገዋል ሲሉ ይከሳሉ።
የአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት መባባሱ የአማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ ቡድኖች አጠቃላይ የጥቃት እንቅስቃሴ መጨመሩ ጋር የተያያዘ ነው። ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ መረጋጋት ከጎደላቸው ክልሎች አንዱ ሲሆን ከሚያዚያ በፊት ከነበረው አራት ወራት ጋር ሲነጻጸር ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ወር ወደ 50% የሚጠጋ ተጨማሪ ግጭቶች የተመዘገቡ ሲሆን 48% ያህሉ ግጭቶች የፋኖ እና የአማራ ታጣቂዎችን ያሳተፈ ነው። በክልሉ እያሻቀበ ያለው አለመረጋጋት የጀመረው መንግስት መጋቢት 28, 2015 ዓ.ም ሁሉም የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅር እንደሚዋሃዱ ካሳወቀ በኋላ ነው። ይህ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲወገድ የተወሰነው ውሳኔ በአማራ ክልል የአማራን ህዝብ ከሌሎች ክልሎች ለሚነሱ ጥቃቶች መከላከል እንዳይችል ነው በሚል ተወስዷል (በአማራ ክልል ስላለው የፖለቲካ ጥቃት ምክንያት እና የቅርብ ጊዜ መንስኤዎቹ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 22-28, 2015ን ይመልከቱ)። ይህም በመንግስት ታጣቂዎች በተለይ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ እና በአማራ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ግጭትን አስከትሏል። በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል አክሌድ 39 የጦርነት ኩነቶችን የመዘገበ ሲሆን አብዛኛዎቹ ውጊያዎች በሰሜን ወሎ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ የተከሰቱ ናቸው።
ባለፉት አምስት አመታት ከሌሎቹ የሀገሪቱ ክልሎች ጋር ሲነፃፀር በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛው በአከባቢ አስተዳዳሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተስተውሏል። ኦሮሚያ በህዝብ ብዛትም ሆነ በግዛት በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ክልል ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፀረ-መንግስት የሆኑ ሰልፎች እና የአመፅ እንቅስቃሴ በክልሉ ውስጥ ታይተዋል። ከመጋቢት 2010 ዓ.ም መጨረሻ እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም ድረስ አክሌድ በኦሮሚያ ክልል በአካባቢ አስተዳዳሪዎች ላይ ያነጣጠሩ 24 ጥቃቶችን የመዘገበ ሲሆን በእነዚህ ጥቃቶች በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። አብዛኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ከታህሳስ 2015 ዓ.ም በኃላ (እ.ኤ.አ በ2023) ነው። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና ማንነታቸው ያልታወቁ ታጠቂ ቡድኖች እነዚህን ጥቃቶች በመፈፀም ይጠረጠራሉ። የኦነግ-ሸኔ አማፂ ቡድን በብዛት የመንግስት ባለስልጣናትን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን አድፍጦ የሚያጠቃ ሲሆን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጠቂ ቡድኖች በብዛት የአካባቢ ባለስልጣናትን የሚያጠቁት በባለስልጣናቱ ቤት ወይም በቤታቸው አቅራቢያ ነው። አባ ቶርቤ ከሚባለው ከኦነግ-ሸኔ የከተማ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚገመተው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በርካታ ከንቲባዎችን፣ አስተዳዳሪዎችን፣ ምክትል አስተዳዳሪዎችን እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን መግደላቸው ተዘግቧል።2 ቦርከና፣ ‘“አባ ቶርቤ – የኦሮሞ ድብቅ ነፍሰ ገዳይ ቡድን – አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግስት አስታወቀ፣’ ታህሥስ 19, 2011 ሆኖም አንዳንድ በአካባቢው ባለስልጣናት ላይ የተፈፀመው ጥቃት በሌሎች አካላት የተቀናበረ ሊሆን እንደሚችልም አመላካች ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ የነቀምቴ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ በመጋቢት 2015 ዓ.ም መገደላቸውን ተከትሎ የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ እና ሌሎች 11 ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለዋል።3 ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘በግድያ የተጠረጠሩ የነቀምቴ ከንቲባ እና ሌሎችም ባለሥልጣናት ታሰሩ፣’ መጋቢት 28, 2015፤ አዲስ ስታንደርድ፣ ‘#ኤስ ዴይሊስኩፕ: ጨፌ ኦሮሚያ በእስር ላይ የሚገኙትን የቀድሞ የነቀምቴ ከንቲባ ያለመከሰስ መብታቸውን አነሳ፣’ ሐምሌ 5, 2015 በሰኔ ወር ብቻ አምስት በአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል ተመዝግበዋል።
ከጥቅምት 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም በነበረው በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ወቅት አክሌድ በትግራይ ክልል ቢያንስ አምስት የአካባቢ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ጥቃቶችን መዝግቧል። በሰኔ 2013 ዓ.ም የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች በፌዴራል መንግሥት ከተቋቋመው ጊዚያዊ ክልላዊ መንግስት ጋር ግንኙነት አላቸው ይሏቸውን 38 የሚደርሱ ግለሰቦችን መግደላቸው ተዘግቧል። አብዛኛው በክልሉ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ከትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ጋር የተያያዘ ነው። በጥቅምት 2015 ዓ.ም ትህነግ/ህወሓት እና የፌዴራል መንግስት የዘላቂ ሰላም ስምምነትን ከፈረሙ በኋላ በክልሉ የሚከሰቱ የፖለቲካ ግጭቶች ቀንሰዋል።4ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ መሪ፣ የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት በተመለከተ የተካሄደውን የሠላም ንግግር አስመልክቶ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣’ ጥቅምት 24, 2015
በብልፅና ፓርቲ የሚመሩ የክልል መንግስታት የአካባቢ ባለስልጣናትን ለመጠበቅ ጥረት ቢያደርጉም እነዚህ ጥረቶች በብዙ ቦታዎች ያልተሳኩ በመሆኑ ባለስልጣናቱ የግድያ፣ የኃይል እርምጃ እና የማስፈራሪያ ኢላማ ሆነዋል። በሚደርሳቸው ዛቻ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በርካታ የአማራ እና የኦሮሚያ ባለስልጣናት የፀጥታ ሁኔታቸው ሊረጋገጥባቸው በሚችል ትላልቅ የአስተዳደር ማዕከላት በመሆን ተግባራቸውን በመወጣት ላይ በመሆናቸው በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል የፌዴራል መንግስትን አሻራ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል።
በኢትዮጵያ ባለው ውስን የመረጃ ምኅዳር ምክንያት ሁሉም የፖለቲካ ግጭቶች እንዳልተዘገቡ ይገመታል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በነሐሴ ወር ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የአካባቢው ባለስልጣናት መገደላቸውን በመግለጽ በዚህም ምክንያት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የአካባቢ አስተዳደር እና የፀጥታ ኃይል መዋቅር መፍረሳቸን አስታውቋል።5የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ‘በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ትግል በሰላማዊ ሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ተጽኖ፣’ ነሐሴ 8, 2015 የአክሌድ የግጭት ማስጠንቀቂያ ስርዓት (ካስት-አክሌድ ኮንፍሊክት አለርት ሲስተም) በመጪዎቹ ወራት በክልሉ የፖለቲካ ግጭት መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ የሚተነብይ በመሆኑ የአማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች እንቅስቃሴ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠቁማል። በክልሉ ካለው አለመረጋጋት አንፃር ታጣቂዎች በክልሉ ያለውን በብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን መንግስት ለማስወገድ በማለም በአካባቢው ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ።