በቁጥር: ኢትዮጵያ, መስከረም 13, 2015- መስከረም 18, 2016
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 1,180
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 3,282
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 1,688
በቁጥር: ኢትዮጵያ,12-18 መስከረም 20161በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በመረጃ ቋታችን ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች ብዛት: 24
- በፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 90
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር: 27
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ከኢፒኦ የመረጃ መዝገብ እንዲሁም በዋናው የአክሌድ ኤክስፖርት መሳሪያ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ከፍተኛ ውጊያ መከሰቱ የተዘገበ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል።
በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች መካከል ውጊያዎች የተመዘገቡ ሲሆን አብዛኛው ጦርነት የተካሄደው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነው። ባለፈው ሳምንት አክሌድ በአማራ ክልል 13 ውጊያዎችን የመዘገበ ሲሆን ወደ ግማሽ የሚጠጋው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተከሰተ ነው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። መስከረም 13 ቀን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ማዕከል በሆነችው በጎንደር ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ ተቀስቅሶ ነበር። ውጊያው የተቀሰቀሰው የፋኖ አባል ናችሁ ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩ እስረኞችን ለማስፈታት በማቀድ በከተማው ቀበሌ 18 አካባቢ የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ መሆኑ ተነግሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ መሰረት በውጊያው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 50 የፋኖ ተዋጊዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል።2የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሳዊ ሪፕብሊክ መከላከያ ሠራዊት፤ ‘የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት እሁድ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም፣’ 13 መስከረም 2016 በተጨማሪም የፋኖ ተወካዮች የማራኪ አካባቢ የቀበሌ ሚሊሻ ኃላፊን፣ በእርሱ ስር የነበሩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የቀበሌ ሚሊሻ አባላትን እንዲሁም ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮችን መግደላቸውን ተናግረዋል።3የኢትዮጵያ ሚዲያ ሰርቪስ፣ ‘በጎንደር የፋኖ ድንገተኛ ጥቃት፣’ 13 መስከረም 2016 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረጉ ተጨማሪ ውጊያዎች በምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ተመዝግበዋል።
በኦሮሚያ ክልል የክልል ፖሊስ አባላት እና ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የቀበሌ ታጣቂዎችን ጨምሮ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥሏል። በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ባቢሌ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ቆሎጂ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጣቢያ አካባቢ ውጊያ ተካሂዷል። ውጊያው የጀመረው የሶማሌ ኃይሎች በባቢሌ ከተማ የግብር መሰብሰቢያ ኬላ በከፈቱበት ወቅት ነበር (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ መስከረም 5, 2016- መስከረም 11, 2016ን ይመልከቱ)። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ ስጋቱን የገለፀ ሲሆን “በሁለቱ ክልሎች በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት” የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸውን አመላክቷል።4ኢሰመኮ፣ ‘በሶማሊ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ላይ በክልሎቹ የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተገቢ የሆነ ምርመራ በማድረግ ለተጎጂዎች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፣’ 21 መስከረም 2016 በተጨማሪም መስከረም 15 ቀን በአርሲ ዞን ቢሎ ቀበሌ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ስድስት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ባለፉት ጥቂት አመታት በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ባሌ ዞኖች ውስጥ አልፎ አልፎ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት ተከስቷል (በኢትዮጵያ ስላለው ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ከጥር 24 እስከ የካቲት 21, 2015ን ይመልከቱ)።
በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበርን በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር አውሏል። የታሰሩበት ምክንያት እስካሁን አልታወቀም። ኢሰመኮ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሰረት አዲሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ እና አማራ “የተስፋፋና የዘፈቀደ እስር” ተካሂዷል።5ኢስመኮ፣ ‘አማራ ክልል:- ከትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ አሳሳቢነታቸው የቀጠለ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣’ 4 መስከረም 2016 የኦሮሚያ ክልል መንግስት የኢሰመኮን ክስ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የማቆያ ማዕከላት በክልሉ መኖራቸውን ክደዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስትም በአማራ ክልል በኮምቦልቻ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር እና ሸዋ ሮቢት እንዲሁም በአፋር ክልል አዋሽ አርባ ከሚገኙ አምስት እስር ቤቶች ብቻ እንዳሉ አስታውቋል።6አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና፡ የኦሮሚያ መንግስት ሰለ ማቆያ ስፍራዎች የወጡ ሪፖርቶች “ሐሰተኛ መረጃ” ናቸው ብሏል፣’ 5 መስከረም 2023 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው በአማራ ክልል እየጨመረ የመጣውን ግጭት ተከተሎ የአማራ ክልል መንግስት ለፌዴራል መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነበር (ስለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የበለጠ መረጃ ለማግኛት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ሐምሌ 22-28, 2015 ይመልከቱ)።
በመጨረሻም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስከረም 18 ቀን በርካታ የጉራጌ ተወላጆች በቀቤና ልዩ ወረዳ በአጉማና ሄራና ቀበሌ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን በወረዳው የብሔር ውክልና እንዲስጣቸው ጠይቀዋል። የጉራጌ ማህበረሰብ እራሱን በራሱ ለማስተዳድር የራሱን ክልል አስተዳደር እንዲቋቋም ለብዙ አመታት ሲጠይቅ ቆይቷል (የጉራጌ ህዝብ እራስን የማስተዳደር ጥያቄ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሃዊ: ሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ይመልከቱ)። ሆኖም በቅርቡ የተቋቋመው የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞንን በሦስት የአስተዳደር እርከኖች የከፈለ ሲሆን የምስራቅ ጉራጌ ወረዳ ራሱን የቻለ ዞን እንዲሆን እና የቀቤና እና ማረቆ ወረዳዎች ደግሞ ልዩ ወረዳ እንዲሆኑ ተደርጓል።7ዋዜማ ሬዲዮ፣ ‘የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕልውና በይፋ አከተመ፣’ 13 ነሐሴ 2015