የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ከሚደረጉ ውጊያዎች ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ተዘግበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ በሚጠራው — የታወጀው የትራንስፖርት አድማ ውጊያዎች እና በሰላምዊ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈፀም ምክንያት ሆኗል። በትግራይ ክልልም የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል።
በአማራ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች
ውጊያዎች በአማራ ክልል የቀጠሉ ሲሆን በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በደቡብ ወሎ እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ውጊያዎች ተከስተዋል። በመርዓዊ ከተማ ከባድ ውጊያ መደረጉ የተዘገበ ሲሆን በውጊያው ሁለት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርሰትያናት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተዋጊዎች ተገድለዋል። ውጊያውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኃይሎች ከአማራ ክልል ፖሊስ እና ከቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር ቢያንስ 50 ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል።
ከመንግሥት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ለኢትዮጵያ መንግሥት አስቸጋሪ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው። በመርዓዊ ከተማ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት መካከል ውጊያ ሚያዝያ 2015 ከጀመረ በኋላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት ክስተት ነው። አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመንግሥት ኃይሎችን እና ፀረ መንግሥት የሆኑ አማፂ ቡድኖችን ያሳተፉ ተመሳሳይ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበባቸው ክስተቶች በኢትዮጵያ እየተበራከቱ መጥተዋል (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2015ን ይመልከቱ)። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባቸው ክስተቶች ከጥቅምት 2013 አስከ ጥቅምት 2015 በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ወቅትም የተለመዱ ነበሩ።1ካትሪን ሁረልድ፣ ሜግ ኬሊ እና ስቴፈን ሊ፣ ‘በኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት እየተደረገ ባለበት እንኳን በመቶዎች የሚቀጠሩ ተገድለዋል፣’ ዋሽንግተን ፖስት፣ የካቲት 22, 2015
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ላይ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር 24 ቀን ለተጨማሪ አራት ወራት ለማራዘም ድምጽ ሰጥቷል።2ዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: ፓርላማው በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማራዘም ድጋፍ ሰጠ፣’ ጥር 24, 2016 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጀመሪያ በነሐሴ 2015 የታወጀው የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ሁሉ እንዲወስድ ከጠየቀ በኋላ ነበር (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ነሐሴ 27- ጳጉሜ 3, 2015 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ሐምሌ 22-ሐምሌ 28, 2015ን ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ክልል በትራንስፖርት ላይ የተጣለ እገዳ
በኦሮሚያ ክልል በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ የታወጀው የትራንስፖርት አድማ በመላው የኦሮሚያ ክልል የእንቅስቃሴ መቀነስ ማስከተሉ ተዘግቧል።3አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: የትራንስፖርት እና የገበያ እገዳ ለማድረግ የተደረገው ጥሪ በኦሮሚያ እንቅስቃሴን አስተጓግሏል፣ የክልሉ መንግሥት ኦነሠን ወቀሰ፣’ ጥር 21, 2016 ታጣቂዎቹ የታወጀው የትራንስፖርት አድማ ለማስፈፀም በወሰዱት እርምጃ በጉጂ እና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች አድማውን ተላልፈዋል ባሉዋቸው አሽከርካሪዎች ላይ ጥቃቶችን ፈፅመዋል። በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳና ማሊማ ወረዳ የሪፐብሊካን ጋርድ ኃይሎች4ሪፐብሊካን ጋርድ የተቋቋመው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በ2010 ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ ነው። የሪፐብሊካን ጋርድ ዋና ዋና ኃላፊነቶች ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን እና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን መጠበቅ ነው። ዳንኤል መምበረ፣ ‘ፎቶ፡ ‘ሪፐብሊካን ጋርድ’ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጠበቅ ዝግጁነቱን አሳየ፣’ አፍሪካ ኒውስ፣ ታኅሣሥ 14, 2011 ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጋር በመዋጋት በቡድኑ በተሸከርካሪዎች ላይ ሊፈፀም የታቀደን ጥቃት መቀልበሳቸውን ተናግረዋል።
የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር የትራንስፖርት አድማ በየጊዜው እያወጀ ይገኛል። በቅርቡ በታህሳስ ወር ውስጥ በኢትዮጵያ የገና በዓል ወቅት ተመሳሳይ አድማ ታውጆ ነበር። እርምጃው ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር እና ወደፊት ለሚደረገው የሰላም ድርድር ራሱን የተሻለ ሁኔታ ላይ ለማስቀመጥ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ፍንጭ የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። ከሁለት ሳምንት በፊት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት በሰጡት ፍንጭ መሠረት በቅርቡ ተጨማሪ የሰላም ንግግር ሊኖር ይችላል። የትራንስፖርት አድማ ቀደም ሲል ከ2006 እስከ 2012 (እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2018) በኦሮሚያ ክልል በቄሮ ወጣቶች በተደረጉ እና በመጋቢት 2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሾም ምክንያት በሆኑ ሰልፎች ላይ በጥቅም ላይ የዋለ ዋነኛ መሳሪያ ነበር። አብዛኛዎቹ የቄሮ አባላት አሁን ላይ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን ተቀላቅለዋል።
በትግራይ ክልል የቀጠሉ የተቃውሞ ሰልፎች
የቀድሞ የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች አባላት — የትግራይ መከላከያ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) — የትግራይ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በመቐለ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮችን ለቀድሞ ወታደሮች በቂ የሕክምና አገልግሎት ድጋፍ በማቅረብ የተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። ከዚህ የተቃውሞ ሰልፍ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በስምንት የትግራይ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በክልሉ ባለፉት ጥቂት ወራት የተቃውሞ ሰልፎች እየተዘወተሩ የመጡ ሲሆን አብዛኛዎቹ የተቃውሞ ሰልፎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሰዎችን ወይም የቀድሞ የትህነግ/ህወሓት/የቲዲኤፍ ተዋጊዎችን ያሳተፉ ነበሩ። ሰልፎቹ ለጊዜው ከቁጥጥር ውጪ ባይሆኑም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ያለው ቅሬታ እየሰፋ ከሄደ ሰፊ አለመረጋጋት እና ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ጥር 18-24, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከጥር 18 እስከ ጥር 24, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 7 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 1 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 7 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 3 ኩነቶች
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት