የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል በከተሞች ውስጥ የሚደረጉ ውጊያዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች መካከል መጠነኛ ውጊያ መከሰቱ ተዘግቧል። በሁለቱ ክልሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችም ተዘግበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚጠይቅ ሰልፍ ተደርጓል።
በአማራ ክልል የሚደረጉ ውጊያዎች ወደ ከተሞች መስፋፋት
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን ውጊያዎች በባህርዳር፣ ሸዋ ሮቢት፣ ደምበጫ፣ ደብረ ማርቆስ እና መርዓዊ ከተሞች መደረጋቸው ተዘግቧል። ከእነዚህም ውጊያዎች አብዛኛዎቹ የተመዘገቡት በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ ነው። በባህርዳር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻ ያደረጉ ሲሆን በርካታ የፋኖ ታጣቂዎችን ተኩሰው መግደላቸውን እና መያዛቸውን ገልጠዋል።1አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ‘”ሕግ የማስከበር ዘመቻው በተሟላ ሁኔታ እየተከናወነ ነው” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣’ የካቲት 22, 2016 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማን መልሶ ለመቆጣጠር ያደረገውን ትልቅ ወታደራዊ ዘመቻ እና በሰሜን ወሎ ዞን የላሊበላ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የተደረገ ውጊያን ጨምሮ በመላው የአማራ ክልል ተጨማሪ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል።2የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መከላከያ ሠራዊት፣ ‘በፅንፈኛው ኃይል ላይ እየተወሠደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኮሩ ዋና አዛዥ አሥታወቁ፣’ የካቲት 19, 2016 በተጨማሪም በአዊ፣ ደቡብ ወሎ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል።
የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችም ቀጥለዋል። የካቲት 21 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አስተዳደር ኃላፊ ማንነታቸው ባልታወቀ — ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ የተገመተ — መሳሪያ በታጠቁ ግለሰቦች ተገድለዋል። በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ የሸዋ ሮቢት የፖሊስ አዛዥ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በፋኖ ታጣቂዎች ተገድለዋል።3ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በሸዋ ሮቢት የሰው ሕይወት የጠፋበት ከባድ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ነዋሪዎች ገለጹ፣’ የካቲት 25, 2016 እነዚህን ግድያዎች ተከትሎ በሸዋ ሮቢት ሳምንቱን ሙሉ ከፍተኛ ውጥረት የነበረ ሲሆን ይኽውም የካቲት 24 ቀን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በከተማዋ ውጊያ እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመጡ እና ለመስክ ስራ ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጓዝ ላይ የነበሩ ከ200 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች ታፍነው ተወስደዋል። የጎጃም ፋኖ የዘመቻ ኃላፊ ጠለፋው መፈፀሙን አምኖ ነገር ግን ወጣቶቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የቀበሌ ታጣቂዎች ናቸው በማለት የወጣቶቹን የጉዞ ምክንያት አስተባብሏል።4ዮናታን ዘብዴዎስ፣ ‘ለደን ምንጣሮ ወደ ሕዳሴ ግድብ የሚያመሩ 275 ወጣቶች መታገታቸው ተገለጸ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 26, 2016
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካቲት 16 ቀን ሁለት የፀረ–መንግሥት እንቅስቃሴዎች — በዘመነ ካሴ የሚመራው የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ፋኖ እና በሻለቃ ዝናቡ የሚመራው የፋኖ ታጣቂ ቡድን — በመዋሃድ የጎጃም አማራ ፋኖ የሚል ቡድን ፈጥረዋል።5የኢትዮጵያ ሚዲያ አግልግሎት፣ ‘ኢኤምኤስ ዜና እሁድ የካቲት 16, 2016፣’ የካቲት 16, 2016 በአማራ ክልል የሚገኙ የፀረ–መንግሥት እንቅስቃሴዎች አንድ ሆነው ለመንቀሳቀስ ትልቅ መሰናክል ገጥመዋቸዋል። ይሁንና ከየካቲት ወር ጀምሮ በከተሞች የሚደረጉ አዳዲስ ጦርነቶችን ጨምሮ ያለው የግጭት መጨመር ከእነዚህ መሰናክሎች የተወሰኑትን እየተሻገሩ መሆናቸውን ሊጠቁሙ ይችላሉ። ከዚህ ቀደም አብዛኛዎቹ ውጊያዎች የሚደረጉት በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች ነበር።
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች
የካቲት 20 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለፀ የታጠቁ ግለሰቦች በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ደጋ ጂጊ አካባቢ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ጥቃት በመፈፀም ሶስት ሰላማዊ ሰዎችን ገድለው ሁለቱን አቁስለዋል። የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ለጥቃቱ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ይኽውም በፋኖ ታጣቂዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ለአጭር ጊዜ የቆየ ውጊያ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ ክስተት ከመስከረም 2016 በኋላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመ ብሔርን መሠረት ያደረገ የመጀመሪያ ጥቃት ነው። ሁለቱም የአማራ እና የኦሮሞ ብሔሮች ሰሜን ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ላይ የሚኖሩ ሲሆን በሰላማዊ ሰዎች ላይ በታጠቂ ቡድኖች የሚፈፀም ጥቃት በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው —እና የፋኖ ታጣቂ አማጺዎች ጥቃቱ የከፋ እንዲሆን አድርገውታል። በዚህ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች ላይ በርካታ የግጭት ውስጥ ተሳታፊ አካላትን የሚያካትቱ ሲሆን ከፍተኛ ውጊታውች የተዘገቡት ከሕዳር 22 እስከ ታህሳስ 22, 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምንጮች በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን ይኽውም በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ወሰሌ ቀበሌ ውጊያዎችን እና ቁጥራቸው በውል ያልተገለፀ ህልፈተን አስከትሏል።6የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ‘በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚንቀሳቀሰው አሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ አሥፈላጊው እርምጃ ተወስዷል፣’ የካቲት 22, 2016
በትግራይ ክልል የተደረገ ሰልፍ
በትግራይ ክልል የካቲት 21 ቀን ጡረተኞች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጀመረበት ከጥቅምት 2013 ጊዜ ጀምሮ ያልተከፈላቸው የጡረታ ክፍያ እንዲከፈላቸው በመጠየቅ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ በተጨማሪም የፕሪቶሪያ ስምምነት — በመንግሥት እና በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር መካከል የተፈረመው— የያዛቸው ስምምነቶች እንዲተገበሩ ጠይቀዋል። ጥቅምት 2015 የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሰልፍ ኩነቶችበተደጋጋሚ እየተደረጉ ሲሆን ይኽውም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናንስ፣ የሰዎች መፈናቀል እና ለቀድሞ የትግራይ መከላለያ ኃይል ወታደሮች የህክምና ድጋፍን ለተመለከቱ ጉዳዮች መፍትሄ እንዲሰጥ ጫና ፈጥረውበታል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
የካቲት 16-22, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከየካቲት 16-22, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 32 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 7 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት