የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት የሰላማዊ ሰዎችን ሞት አስከትሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እና በጋምቤላ ክልል እንደገና ግጭት ተቀስቅሷል።
በአማራ ክልል ውስጥ በተፈፀሙ የአየር ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ተመቱ
በአማራ ክልል በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በደቡብ ወሎ እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። ከውጊያዎቹ በተጨማሪ መንግሥት ግንቦት 4 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ውስጥ የሰባት ሰላማዊ ሰዎች ህይወትን እንደቀጠፈ የተነገረለትን ጥቃት ጨምሮ ብዙ የአየር ጥቃቶችን ፈጽሟል። በተመሳሳይ ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ በተፈፀመ ሁለተኛ የአየር ጥቃት ሦስት የፋኖ አባላት እና አራት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በመንግሥት የሚደረገው የአየር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ የነበረ ሲሆን አሁንም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የመንግሥት የፀረ አማፂያን ስትራቴጂ ዋና አካል ሆኖ ቀጥሏል። በተዋጊ አውሮፕላኖችም ሆነ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የሚፈፀሙ የአየር ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተላቸው ቅሬታ ፈጥረዋል። የካቲት 2016 በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃን ወደራ ወረዳ በተሽከርካሪ ላይ በመንግሥት የተፈፀመ የአየር ጥቃት 30 ሰዎችን በመግደል ሌሎች 15 ሰዎችን ማቁሰሉ ሪፖርት ተደርጓል። በአማራ ክልል ከነሐሴ 2015 ጀምሮ በተፈፀሙ 29 የአየር ጥቃት ክስተቶች ቢያንስ 323 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ውጊያዎች
ግንቦት 6 ቀን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የተነሱ ታጣቂዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ/አማሮ ዞን ከመጡ ማንነታቸው ካልተገለፀ ታጣቂዎች ጋር ለሁለት ቀናት የተዋጉ ሲሆን በዚህም ውጊያ ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። የአካባቢው የመንግሥት አካላት ውጊያው መደረጉን አረጋግጠው ውጊያውን ለማስቆም ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ጠይቀዋል።1ዮናታን ዘብዴዎስ፣ ‘በደቡብ ኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዳግም በተነሣ ግጭት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 7, 2016 የምዕራብ ጉጂ እና አማሮ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ሲሆን የሁለቱ ዞኖች የአስተዳደራዊ ወሰን የይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዙ ናቸው።
በጋምቤላ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ችግር
በጋምቤላ ክልል ለሁለተኛ ሳምንት ግጭት ቀጥሏል። ግንቦት 4 እና 5 በኢታንግ ልዩ ወረዳ ፉልኮርሴ በተባለ ቀበሌ የክልሉ ፖሊስ ማንነቱ ካልተገለፀ ታጣቂ ቡድን ጋር ተዋግቷል። በውጊያው ቢያንስ ስድስት ሰላማዊ ሰዎች እና ሶሰት የፀጥታ ኃይል አባላት የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎች ቆስለዋል። ታጣቂዎቹ ቤቶችን ያቃጠሉ ሲሆን ይህን ግጭት ተከትሎ ቢያንስ 10370 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።2 ገ/ሚካኤል ገ/መድህን፣ ‘በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተከሰተ ግጭት 11 ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ፣’ ቪኦኤ አማርኛ, ግንቦት 7, 2016 ውጊያውን ተከትሎ የጋምቤላ ከተማን ከኢታንግ ልዩ ወረዳ ጋር የሚያገናኘው መንገድ ለጊዜው ተዘግቶ ነበር። ውጊያው የተጀመረው የፀጥታ ኃይሎች ማንነቱ ያልተገለፀ ታጣቂ ቡድንን ትጥቅ ለማስፈታት ሙከራ ማድረጋቸውን ተከተሎ ነው።3ነጋሳ ደሳለኝ፣ ነጋሽ መሐመድ እና ታምራት ዲንሳ ‘በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት አለፈ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 6, 2016
ጋምቤላ ክልል ለዓመታት ሰላማዊ ሆኖ የሰነበተ ቢሆንም ከግንቦት 2015 ጀምሮ በኢታንግ ልዩ ወረዳ እየተከሰተ ያለው አለመረጋጋት የክልሉን ሰላም በመቀልበስ በክልሉ ግጭት እየጨመረ ይገኛል። ሚያዝያ 11 ቀን የክልሉ መንግሥት በክልሉ እየጨመረ ከመጣው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሥራ የተባረሩ የሥራ ኃላፊዎችን ለመተካት ለስምንት አዳዲስ ኃላፊዎች ሹመት ሰጥቷል።4የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ፣ ‘የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለስምንት አዳዲስ የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ሰጠ፣’ ሚያዝያ 11, 2016፤ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ፣ ‘የጋምቤላ ክልል መንግሥት በቅርቡ በክልሉ ከተከሰተው የፀጥታ ቀውስ ጋር በተያያዘ አራት ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነታቸው ማንሳቱን አስታወቀ፣’ መጋቢት 30, 2016
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ግንቦት 3-9, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከግንቦት 3 እስከ 9, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 13 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 5 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 20 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 2 ኩነቶች
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት