ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 በጨረፍታ
አበይት አሃዞች
- አክሌድ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 120 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች እና 398 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች መዝግቧል።
- በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 215 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። የትግራይ ክልል በ135 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ጦርነት ሲሆን 61 ኩነቶች ከ77 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር ተመዝግበዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በ40 ኩነቶች እና 147 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
አበይት ክንውኖች
- ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ በደረሰ የአየር ድብደባዎች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
- የመንግስት ኃይሎች በትግራይ ክልል ግዛቶችን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ውጊያ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥቃት ተመዝግቧል። በወሩ መገባደጃ ላይ የመንግስት ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ በርካታ ዋና ዋና ከተሞችን መቆጣጠር ችለዋል።
- በሀገሪቱ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ትላልቅ መንግስትን የሚደግፉ ሰልፎች ተመዝግበዋል።
- በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች – የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች – መዋጋታቸውን ቀጥለዋል።
- በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ቀጥሏል።
በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ
- ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሀዊ ትኩረት፡ በሀገሪቱ በደረሱ የአየር ድብደባዎች ምክንያት ከፍተኛ የሞት አደጋዎች እየተከሰቱ ባሉበት ወቅት በመንግስትና በትህነግ/ህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረሰ
ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ በመንግስት ኃይሎች እና በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች መካከል ውጊያ የቀጠለ ሲሆን ሁለቱ ወገኖች የተሳተፉበት 42 የጦርነት ኩነቶች በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ተመዝግበዋል። በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፣ ምዕራብ ጎንደር እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ትግራይ፣ በምስራቅ ትግራይ፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ በደቡብ ምስራቃዊ ትግራይ እና በደቡብ ትግራይ ዞኖች የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። አብዛኛው የጦርነት ኩነቶች የተመዘገቡት በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ሲሆን በትግራይ ክልል ደቡባዊ ትግራይ ዞን ውስጥ ነው። በአማራ ክልል ቆቦን እና ጎቢዬን እንዲሁም በትግራይ ሽሬን፣ አላማጣን እና ኮረምን ጨምሮ የመንግስት ኃይሎች በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በርካታ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ስር አውለዋል። መስከረም 22 ቀን ትህነግ/ህወሓት “ታክቲካል ጂኦግራፊያዊ ማስተካከያ ለማድረግ” ኃይሉን ከሰሜን ወሎ ዞን ማስወጣቱን ያሳወቀ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ኃይሉን እንደገና ወደ ዞኑ ሊያስገባ እደሚችል አሳውቋል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 23, 2015)። ነገር ግን ሌሎች ዘገባዎች እና አንዳንድ የአካባቢው እማኞች የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ከዚህ አካባቢ በመንግስት ኃይሎች ተገፍተው መውጣታቸውን ይናገራሉ (ኢኤምኤስ.፣ መስከረም 23, 2015፤ ኢኤምኤስ፣ መስከረም 24, 2015)።
በጥቅምት 12 እና 13 በኢትዮጵያ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ ከ37 በላይ ከተሞች ውስጥ ትህነግ/ህወሓትን እና ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ያደርጋሉ ያሏቸውን ጣልቃ ግብነት የሚቃውሙ ሰልፎች ተካሂደዋል። እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱት “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምፄ አሰማለው” በሚል መሪ ቃል ስር ነው። አብዛኛዎቹ እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱት በአማራ ክልል ውስጥ ነው። ባለፈው አመት ህዳር 2014 ላይ ተመሳሳይ ትህነግ/ህወሓትን፣ ኦነግ-ሸኔን፣ የአሜሪካን በኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነትን እና አለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለ ኢትዮጵያ ይዘግባሉ ስለተባለው አድሏዊ ዘገባዎች በመቃወም በ27 ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን አብዛኛዎቹ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱት በኦሮሚያ ክልል ነበር (ስለእነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከጥቅምት 22, 2014 እስከ ህዳር 21, 2014ን ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና ውጊያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ወር አክሌድ ኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች የተሳተፉባቸው 11 ውጊያዎችን በምስራቅ ሸዋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ መዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ብዙም ያልተለመዱ በኦነግ-ሸኔ ላይ ያነጣጠሩ ነው የተባሉ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተፈፀሙ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች በክልሉ ተዘግበዋል። እነዚህ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች የተመዘገቡት በምዕራብ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ውስጥ ነበር።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በወሩ ውስጥ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንደነበረ ቆይቷል። ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሉ 32 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ የጥቃት ኩነቶች ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ በመንግስት ኃይሎች የተፈፀሙ ሲሆን እነዚህ ጥቃቶች በአብዛኛው በምዕራብ ሸዋ ዞን የተከሰቱ ሲሆን በአጠቃላይ 31 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ሶስት ጥቃቶች የተሳተፉ ሲሆን በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት የ14 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተነግሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በሰባት ሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሱ ጥቃቶች የተሳተፉ ሲሆን 50 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
ከነሐሴ 2014 ጀምሮ አንጻራዊ መረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ ባለፈው ወር በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እና ውጊያዎች ተመዝግበዋል። ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የጉሙዝ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ውስጥ የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪን እና ሌሎች ሰባት ሰዎችን ገድለዋል። ይህንን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የጉሙዝ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በኤጀንታ፣ ወላምሻ ማያ እና ኢፍታውን ቀበሌዎች ከ”ጉሙዝ አማፂ ቡድን” ጋር ተዋግተዋል (ኢኤምኤስ፣ ጥቅምት 8, 2015)። ጥቅምት 3 ቀን ይኸው ታጠቂ ቡድን በማንዱራ ወረዳ ቱኒ ዳቢሻ ቀበሌ የጉሙዝ ተወላጅ በሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ባልታወቀ ምክንያት ጥቃት ፈፅሟል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥቅምት 9 ቀን የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር በአሶሳ ከተማ የሰላም ስምምነት ተፈራርሟል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 5-11, 2015 ይመልከቱ)።
በመጨረሻም በሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና በጅግጅጋ ጋራዲ ዊልዋል አየር ማረፊያ አንድ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል በፌዴራል ፖሊስ አባል መገደላቸውን ተከትሎ ሰልፍ ተደርጓል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 12-18, 2015 ይመልከቱ)። አንዳንድ የስልፉ ተሳታፊዎች ከፀጥታ አካልት ጋር የተጋጩ ሲሆን ፀጥታ አካልትም ስልፈኞችን ለመበተን አስለቃስ ጭስ ተኩሰዋል።
ወርሀዊ ትኩረት፡ በሀገሪቱ በደረሱ የአየር ድብደባዎች ምክንያት ከፍተኛ የሞት አደጋዎች እየተከሰቱ ባሉበት ወቅት በመንግስትና በትህነግ/ህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረሰ
ከአንድ ሳምንት በላይ መደበኛ የሰላም ውይይት ካደረጉ በኋላ ጥቅምት 23, 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት እና የትህነግ/ህወሓት መሪዎች በደቡብ አፍሪካ ለዘለቄታዊ ሰላም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል (አልጀዚራ፣ ጥቅምት 23, 2015)። በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውጊያ የጀመረው ጥቅምት 24, 2013 ዓ.ም ነነር። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሁለቱ ወገኖች የተፈረመውን ስምምነት ይፋዊ ዕውቅና የሰጠ ሲሆን የተኩስ አቁምን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 23, 2015)። ምንም እንኳን ስምምነቱ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ውጊያ በተሳካ ሁኔታ ማስቆም ቢችልም ተጨማሪ ተግዳሮቶች እና በመላ ሀገሪቱ የአየር ድብደባ እና በመንግስት ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች ሰላማዊ ሰዎች ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሳቢያ የሰላማዊ ሰዎች ሞት እየጨመረ ቀጥሏል።
ስምምነቱ 15 አንቀጾችን ያቀፈ ነው። ሌሎች ጉዳዮች ጨምሮ ሁለቱ አካላት የትህነግ/ህወሓት ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ በትግራይ ክልል “የህገ-መንግስት ሥርዓትን” በመመለስ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ለመመስረት እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥቅምት 23, 2015፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 25 ቀን 2015)። የጥገና ቡድኖች በሰቆጣ (ዋግ ኽምራ፣ አማራ) እና ቆቦ-አላማጣ (ደቡብ ትግራይ ዞን) መስመሮች የመብራት አገልግሎቱን ወደ ነበረበት መልሰዋል። የተወሰኑት እነዚህ አካባቢዎች ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው ናቸው (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 22, 2015)። ነገር ግን ስምምነቱ እንደ ወልቃይት ፀገዴ አካባቢ ያሉ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እና የክልል አስተዳደር ጥያቄዎች እንዴት እንደሚፈቱ አልገለጸም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥቅምት 24 ቀን በሰጡት መግለጫ ሁለቱ ወገኖች እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች በ”ንግግር እና በሀገሪቱ ህግ” መሠረት ለመፈታት መስማማታቸውን አመላክተዋል (ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015)።
ከስምምነቱ በፊት በነበረው አንድ ወር የመንግስት ኃይሎች – የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የአማራ እና ፋኖ ታጣቂዎች – ከኤርትራ ከመጡ ወታደሮች ጋር በመሆን በደርዘን የሚቆጠሩ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ከተሞችን እና መንደሮችን እንደገና ተቆጣጥረዋል። ። በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ የመንግስት ኃይሎች አድዋን፣ አክሱምን እና አዲግራትን መልሰው በቁጥጥር ስር በማዋላቸው የክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ ለመድረስ ተቃርበው ነበር (ኤፒ ኒውስ፣ ጥቅምት 15, 2015፤ ኢኤምኤስ፣ ጥቅምት 17, 2015)።
በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኃይሎች ከኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተዋጉ ሲሆን የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምዕራብ ወለጋ ዞን ገጠራማ አካባቢዎች አንዳንድ የተወሰኑ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 24, 2015)። በሰሜን ምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አንዳንድ ከኦነግ-ሸኔ ጎን የተሰለፉ የኦሮሞ ታጣቂዎች እና የአማራ ታጣቂዎች የሚሳደርጉት ውጊያ ቀጥሏል።
ከመስከረም 2015 ዓ.ም ጀምሮ የመንግስት ኃይሎች በአማፂ ኃይሎች ላይ በሁለቱም በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚያደርጉት የአየር ጥቃቶች እየጨመሩ ነው። ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 21, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አክሌድ ቢያንስ 16 የአየር ድብደባ ኩነቶችን የመዘገበ ሲሆን ይህም በግምት 163 ሪፖርት የተደረጉ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፤ ይህም በሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተከሰተ ከፍተኛ ቁጥር ነው (ከታች ያለውን የግራፍ ምስል ይመልከቱ)። በአሁኑ ወቅት ባለው ውጊያ እና የሚዲያ ሽፋን ባለመኖሩ ምክንያት ማረጋገጥ ባይቻልም ባለፈው ወሩ ውስጥ በትግራይ ክልል ተጨማሪ ድብደባዎች እና የሞት አደጋዎች መከሰታቸው ይገመታል።
በኦሮሚያ ክልል በኦነግ-ሸኔ ኃይሎች ላይ ያነጣጠሩ የአየር ጥቃቶች በምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የተደረጉ ሲሆን ቢያንስ አንድ የአየር ድብደባ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፈተኛ ጉዳት አድርሷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 15, 2015)።
በተጨማሪም ከተመዘገቡት ክስተቶች መካከል በመስከረም 24 ቀን በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን አዲ ዳዕሮ ላይ በተፈፀመ የአየር ድብደባ ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት አድርጓል (ሮይተርስ፣ በመስከረም 25, 2015)። ጥቅምት 4 ቀን በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ሽሬ በትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ድብደባ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተፈፀመ ሲሆን አንድ የአለም አቀፍ አድን ኮሚቴ ሰራተኛ እና ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ሶስት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ወር ተጠናክሮ በቀጠለው ውጊያ ምክንያት በትግራይ የሚደረሰው ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ ድርጅቶች ስጋታቸውን የሚገልፅ መግለጫዎች አውጥተዋል። ባለፈው ወር ውጊያው በትግራይ ክልል የተካሄደ በመሆኑ በኢትዮጵያ የፌዴራል ኃይሎች ወታደራዊ ዘመቻ የተገደሉት ሁሉም ማለት ይቻላል የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ይህም በርካታ ቡድኖች – የዩኤስ ሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየምን ጨምሮ – በትግራይ ክልል ስላለው “የከፋ የዘር ማጥፋት አደጋ” ስጋታቸውን እንዲገልጹ አድርጓቸዋል (የዩኤስ ሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም፣ ጥቅምት 15, 2015)። በምላሹም በጥቅምት 12 እና 13 አዲስ አበባን ጨምሮ ከ37 በላይ ከተሞች “የተለያዩ የምዕራባውያን አካላት” “ኢትዮጵያ ላይ ስም የሚያጠፋ ውሸት እያተሰራጩ ነው” በማለት ከፍተኛ ፀረ-ምዕራባውያን ሰልፎች በአካባቢው ባለስልጣናት ተዘጋጅተው ነበር (የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ጥቅምት 18, 2015)። ምንም እንኳን የተሳካ የሰላም ድርድር ይህን አካሄድ ሊቀይር ቢችልም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና በምዕራባውያን – እንደ አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት እና አየርላንድ ያሉ ኢትዮጵያን በትግራይ የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚከሱ – ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት ባለፈው አመት ጨምሯል።
ለኢትዮጵያ ፌዴራል ኃይሎች ከአየር ድብደባዎች ጋር በፍጥነት ቦታዎችን የመቆጣጠር ግስጋሴ ቅንጅት አዲስ ምዕራፍ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ተወላጆች አመራሮች መክዳት ምክንያት፣ በሰሜናዊው እዝ ላይ በደረሰው ጥቃት እና የአየር ሃይል መዳከሙ በ2013 እና 2014 በተከሰቱ ውጊያዎች ሁሉ ደካማ እንቅስቃሴ ነበረው (ኒውዮርክ ታይምስ፣ ጥቅምት 2, 2015)። ባለፈው አንድ አመት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ሰፈ ያለ ምልመላ፣ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ እና የአመራር ለውጦች ለመከላከያ ሠራዊቱ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ አምጥተዋል (ፋና ቴሌቪዥን፣ ጥር 13, 2014)። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የአየር ድብደባ ለብዙ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ቢሆንም ከትህነግ/ህወሓት ጋር በሚደረገው ውጊያ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከጥቅምት 2013 ከነበረው አቅም የተሻለ አሁን አቅም ያለው ይመስላል። ይህም ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ቱርክ እና ኢራን የተገኙ ድሮኖችን ጨምሮ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ ነው (ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ታህሳስ 11, 2015)።
በትግራይ ወስጥ የተደረገው ፈጣን ግስጋሴ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ተመሳሳይ አቅም ጋር አንድ አለመሆኑን ያመላክታል። ይህ የታደሰው እና የተጠናከረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ባሻገር ሌሎች ለውጦችን ያስከትላል። ለምሳሌ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሰላም ተጨማሪ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችን ነጻ የሚያደርግ ከሆነ በኦሮሚያ ክልል እየተጠናከሩ ያሉት የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች ጠንካራ ተቃውሞ ሊገጥማቸው ይችላል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 24, 2015፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 27, 2015)። ምንም እንኳን ባለፈው ወር የተደረጉ የአየር ጥቃቶች በኦነግ-ሸኔ ቡድን ላይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ከአካባቢ ህዝብ ጋር አብሮ በመመሳሰሉ ምክንያት አነስተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ቢመስልም ኦነግ-ሸኔን ለመዋጋት የበለጠ ጠንከር ያለ እርምጃ ወደፊት ሊደረግ ይችላል። እንደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል እና ደቡብ ኢትዮጵያ ወስጥ ያሉ አማፂ ቡድኖችም እንዲሁ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።
የተጠናከረ የፌዴራል ጦር እና የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ሰላም ሀገሪቱን ወደ መረጋጋት ጎዳና ላይ መሆኗን ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ እንደተገለጸው ባለፈው ወር በደረሰው የአየር ድብደባ በደረሰው ከባድ የሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ሰላማዊ ሰዎች በሀገሪቱ ያለውን ግጭት መሸከማቸውን ቀጥለዋል። በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች አማፂ ቡድኖች ጋር ሰፊ ሰላም እስካልተገኘ ድረስ የፖለቲካ ብጥብጥ ከፍ ባለ ደረጃ እንደሚቀጥል ይገመታል።