የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል በደቡብ ትግራይ ዞን አወዛጋቢ አካባቢዎች ዳግም ውጊያ ሲቀሰቀስ በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን (ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) የኃይማኖት አባቶችን ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋምቤላ ክልል የአካባቢ ግጭት ቀጥሏል።
በትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ዳግም የተቀሰቀሰው ውጊያ
መጋቢት 16 እና 17 በትግራይ እና በአማራ ብሔር ታጣቂዎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው በደቡብ ትግራይ ዞን ውስጥ ዳግም ውጊያ የተቀሰቀሰ ሲሆን በአላማጣ ወረዳ በር ተክላይ አካባቢ ጦርነት ተመዝግቧል። በአላማጣ ወረዳ የጣኦ እና አዲስ ብርሃን ቀበሌዎችን የትግራይ ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋል። በዚህ ውጊያ አራት የአማራ ታጣቂዎች መሞታቸው ሲታወቅ 12 ሰዎች ቆስለዋል። በትግራይ እና በአማራ ብሔር ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መፈጠሩን ተከትሎ ተጨማሪ የአማራ ተዋጊዎች እንዳይቀላቀሉ ለመከላከል ሲሞክር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ብሔር ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል። እነዚህን ውጊታዎች ተከትሎ መጋቢት 22 ቀን በደቡብ ትግራይ ዞን ኮረም ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ሰልፈኞቹ ተጨማሪ ግጭት ከመፈጠሩ በፊት የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎችን እጣ ፋንታ መንግስት እንዲፈታ ጠይቀዋል።1ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘የአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲፈታ የኮረም ነዋሪዎች ጠየቁ፣’ መጋቢት 23, 2016
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በጥቅምት 2015 ካበቃ በኋላ በደቡብ ትግራይ ዞን — በይፋ የትግራይ ክልል አካል የሆነ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ባለስልጣናት የሚተዳደር — ውጊያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበው በየካቲት ወር ነበር። በአማራ እና ትግራይ ክልል መንግስታት መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መቷል። ባለፈው ሳምንት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአማራ ክልል ባለስልጣናት የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን ቦታዎች በአማራ ክልል አድርገው የሚያሳዩ የመማሪያ መጽሐፍትን አስመልክቶ ለአማራ ክልል ማስጠንቀቂያ ስጥቷል።2ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘የአማራ ክልል በመጽሐፍት ላይ ያወጣውን ካርታ በአስቸኳይ እንዲያስተካክል የትግራይ ክልል አስጠነቀቀ፣’ መጋቢት 16, 2016 የአማራ ክልል መንግስት በሰጠው ምላሽ በታሪክ እነዚህ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን ቦታዎች የአማራ መሆናቸውን በመግለጽ የትግራይ አስተዳደር ከሁከት ቀስቃሽ መግለጫዎች እንዲቆጠብ ጠይቋል።3አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ‘ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሠጠ መግለጫ፣’ መጋቢት 18, 2016 በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱት ጦርነኦች አንጻር በቅርብ የተቀሰቀሰው ውጊያ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘው ሰላም ላይ ቀጥተኛ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ በዚህ አካባቢ የሚከሰቱ ለውጦች ጉልህ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጋቢት 13 እና 14 የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር 212 ምርኮኞች መልቀቁን ያስታወቀ ሲሆን ይህም በአፍሪካ ህብረት ምሪት የክልል እና የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት እና የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር አባላት ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ የተደረገ መልካም እንቅስታሴ ነው።4ትግራይ ቴሌቪዥን፣ ‘የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር 100 ምርኮኞችን ለቀቀ፣’ መጋቢት 13, 2016፤ የትግራይ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ ‘የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር ተጨማሪ ምርኮኞችን ለቀቀ፣’ መጋቢት 14, 2016
ጦርነት በኦሮሚያ ክልል
በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ የነበረ ሲሆን በዚሁም የሶስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተዘግቧል። መጋቢት 13 እና 14 በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ እና በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ተጨማሪ ውጊያዎች መከሰታቸውም ታውቋል። በእነዚህ ወረዳዎች የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ የመንግስት ኃይሎች ኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ይደግፋሉ በማለት የከሰሷቸውን 16 ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸው ተዘግቧል።5ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘በወለጋ ዞኖች በቀጠለው ግጭት 16 ሲቪሎች መገደላቸው ተገለጸ፣’ መጋቢት 19, 2016
በሌላ ቦታ በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ዶዶላ ከተማ መጋቢት 16 ቀን ታጣቂዎች ሁለት የኃይማኖት አባቶችን ከአምስት ቤተሰባቸው እና ሌሎች አራት ሰላማዊ ሰዎች ጋር መግደላቸው ታውቋል። የአካባቢው የወረዳ አስተዳደር ምንጮች ኦነሠ/ኦነግ–ሸኔን ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ ሲያደርጉ ሌሎች ምንጮች ጥቃቱ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈፀመ መሆኑን ጠቁመዋል።6ስዩም ጌቱ፣ ነጋሽ መሐመድ እና ማንተጋፍቶት ስለሺ፣ ‘በምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላ የንጹሃን ግድያ፣’ መጋቢት 18, 2016፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በምሥራቅ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ታጣቂዎች አገልጋዮችን እና ምዕመናንን መግደላቸው ተነገረ፣’ መጋቢት 18, 2016 የመንግስት ምንጮች በጥቃቱ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።7ገልሞ ዳዊት፣ ‘በዶዶላ ከተማ ጥቃት 11 አገልጋዮች እና ምእመናን ተገደሉ፣’ መጋቢት 18, 2016 በኦሮሚያ ክልል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት አልፎ አልፎ የሚፈጸም ሲሆን በቅርብ የተከሰተው ጥቃት በየካቲት ወር በምስራቅ ሸዋ ዞን ዝቋላ ገዳም ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው።
በጋምቤላ ክልል የቀጠለው ግጭት
በጋምቤላ ክልል በአቦቦ ወረዳ አኝዋክ ዞን መጋቢት 17 ቀን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አምስት አርብቶ አደሮችን ተኩሰው መግደላቸው ተከትሎ በክልሉ ያለው ግጭት ቀጥሏል። በማግስቱ የአኝዋክ ብሔር ታጣቂዎች በአቦል ወረዳ እና ታራፓም የስደተኞች ካምፕ መካከል ሲጓዝ በነበረ የህዝብ አውቶቡስ ላይ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ጥቃት በመሰንዘራቸው አምስት ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። የጋምቤላ የመንግስት ባለስልጣናት ችግሩን አምነው የክልሉን የፀጥታ መዋቅር አካላት ተጠያቂ በማድረግ እሰር መፈፀማቸውን አመልክተዋል።8የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት፣ ‘የጋምቤላ ህ/ብ/ክ/መንግሥት በወቅታዊ የክልሉ ፀጥታ ሁኔታ ላይ የሰጠው መግለጫ፣’ መጋቢት 20, 2016
ከ2013 ጀምሮ የጋምቤላ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት እጅግ ሰላማዊ አካባቢዎች አንዱ ነበረ። ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተከታታይ ግጭቶች መከሰታቸው ግን ይህ ሰላም እየተቀየረ የመጣ ይመስላል። መጋቢት 9 ቀን በጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አባል ላይ የተከፈተው ተኩስ በክልሉ በቅርቡ የተከሰተ ኩነት ነው።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
መጋቢት 14–20, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከመጋቢት 14 እስከ 20, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 14 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 17 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 4 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት