የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ካሉ የፀረ መንግሥት አመፆች ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸውን ቀጥለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊላንድ ወታደሮች በኢትዮጵያ ስልጠና የጀመሩ ሲሆን ይኽውም ውጥረት እንዲጨምር አድርጓል።
በኦሮሚያ ክልል እየታየ ያለው የፀጥታ ሁኔታ
በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት(ኦነሠ)—በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራ— እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ባለፈው ሳምንት መቀነስ ያሳዩ ሲሆን በምስራቅ፣ ምዕራብ እና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውጊያዎች ተመዝግበዋል። ቀደም ባለው ሳምንት ከ100 ተማሪዎች በላይ ታግተው ከመወሰዳቸው ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ከፍተኛ ውጥረት ባለፈው ሳምንትም በተመሳሳይ ሁኔታ የቀጠለ ሲሆን ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና መንግሥት እርስ በእርስ መወነጃጀላቸውን ቀጥለዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከታገቱት 167 ተማሪዎች መካከል 160 ተማሪዎችን ማስለቀቁን ገልጧል።1ገልሞ ዳዊት፣ ‘“ከታገቱት ተማሪዎች የሚበዙት አስለቅቀናል” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 5, 2016 ይሁንና የተጎጂዎች ቤተሰቦች አብዛኛዎቹ ተማሪዎች አሁንም በአጋቾች እጅ የሚገኙ መሆኑን የገለፁ ሲሆን አጋቾቹም ተማሪዎቹን ለመልቀቅ ከ500,000 እስከ 1 ሚሊዮን ብር (ከ8,000 እስከ 17,000 የአሜሪካን ዶላር) በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።2ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባቸው ተማሪዎች ከታገቱ ከ10 ቀናት በላይ ሆናቸው፣’ ሐምሌ 5, 2016 ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ለድርጊቱ ተጠያቂ አለመሆኑን በመግለጽ ለተማሪዎቹ እገታ የመንግሥት ኃይሎችን፣ የአካባቢ ካድሬዎችን እና ስራ አጥ ወጣቶችን ከሷል።3ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባቸው ተማሪዎች ከታገቱ ከ10 ቀናት በላይ ሆናቸው፣’ ሐምሌ 5, 2016 በኦሮሚያ ክልል በቅርብ ዓመታት እገታ እና አጠቃላይ የደህንነት እጦት ትልቅ ችግር ሆኖ ቀጥለዋል4ፍሬድ ሃርተር፣ ‘ይህ ወረርሽኝ ነው’፡ የኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የአፈና ስጋት፣’ ዘ ጋርዲያን፣ ጥር 14, 2016 (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ጥቅምት 3-9, 2016 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ ጥቅምት 10-16, 2016 ይመልከቱ)። ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ መሻሻል የሳየ ቢመስልም ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ በግንቦት ወር የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተሳተፉባት በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ በሚገኘው አዲሱ አየር ማረፊያ መደበኛ በረራዎች እያረፉ ይገኛሉ።5ፋና፣ ‘የነቀምቴ አየር መንገድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የበረራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፣’ ሰኔ 9,2016 ወደ ደምቢዶሎ የሚደረጉ በረራዎችም በየካቲት ወር ውስጥ ጀምረዋል።6አብዲ ቢያንሳ፣ ‘ምዕራብ ኦሮሚያ ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሰ ነው?፣’ አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 21, 2016
በአማራ ክልል የተኩስ ልውውጥ
በአማራ ክልል የተመሠረተው የሰላም ኮሚቴ ጥረቱን ቢቀጥልም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ ውጊያ ሳይቋረጥ ቀጥሏል። የመንግሥት እና ከመንግሥት በተቃራኒ የቆሙ ምንጮች እንደዘገቡት በሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ አዊ፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃም እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች ውጊያዎች ተደርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም በአማራ ክልል በሱዳን ስደተኞች ላይ በታጣቂዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ሁለት ጥቃቶች፤ አንዱ በምዕራብ ጎንደር የኩመር ካምፕ አቅራቢያ እና ሁለተኛው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሸሂዲ እና ጎንደር መካከል ያለውን መንገድ ተከትሎ ባለው አካባቢ ሰኔ 28 እና ሐምሌ 2, 2016 ተፈፅመዋል። የሱዳን ስደተኞችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ከግንቦት ወር ጀምሮ በድንበር አካባቢ ባሉ ካምፖች ትላልቅ ሰልፎችን ቀስቅሰዋል። ሰኔ 29 ቀን የሱዳን ስደተኞች ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች አንድ ቀን ቀደም ብሎ የታገተ የሀገራቸው ስደተኛ እንዲለቀቅ በመጠየቅ በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በግንቦት ወር ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞችን ደህንነት ለማሻሻል ቃል ገብቶ ነበር።7ነፊሳ አልጣሂር፣ ‘የሱዳን ስደተኞች በተፈፀሙባቸው ጥቃቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ደን ውስጥ እየተንገላቱ ነው፣’ ሮይተርስ፣ ግንቦት 30, 2016
የሶማሊላንድ ወታደሮች ሶማሊ ክልል መግባት
በሺህ የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ለውትድርና ስልጠና የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የገቡ ሲሆን ይኽውም በጥር ወር በሁለቱ ወገኖች መካከል የመግባቢያ ሰነድ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ ጥብቅ ትብብር ስለመፈጠሩ ግልጽ ማሳያ ነው። መጋቢት 26 ቀን ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ውጥረት ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሯ ያባረረች ሲሆን የራሷንም አምባሳደር ከአዲስ አበባ መልሳ ጠርታለች።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ሰኔ 29-ሐምሌ 5, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 5, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 26 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 4 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 10 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 2 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት