የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ተቃውሞ እየተደረገ ቢሆንም ተፈናቃዮች የይገባኛል ጥያቄ ወደ ሚነሳባቸው የትግራይ ደቡባዊ ዞን አካባቢዎች መመለሳቸውን ቀጥለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውጊያዎች እና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሪፖርት ተደርገዋል።
በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት የሱዳን ስደተኞችን እየጎዳ ይገኛል
ባለፈው ሳምንት የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች መዋጋታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ በሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ውጊያዎች መደረጋቸው ተመዝግቧል። በምዕራብ ጎንደር ቋራ ወረዳ የካሆ ቀበሌ ውስጥ በፋኖ እና በቀበሌ ታጣቂዎች መካከል ትልቅ ውጊያ መደረጉን የሚያሳዩ ዘገባዎች ባለፈው ሳምንት ወጥተዋል። ውጊያው ሰኔ 28 ቀን የጀመረ ሲሆን ለአራት ተከታታይ ቀናት ቀጥሏል። በአካባቢ ባለሰልጣናት መሠረት ውጊያው የተቀሰቀሰው የፋኖ ታጣቂዎች አብዛኛዎቹ የአገው ተወላጅ የሆኑ የቀበሌ ታጣቂዎችን መሳሪያቸውን እንዲሰጡዋቸው እና መንግሥትን መደገፉን እንዲያቆሙ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።1ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በምዕራብ ጎንደር ቋራ የ‘ፋኖ ታጣቂዎች’ ፈጸሙት በተባለ ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን እና 10 ሺህ የሚሆኑ መፈናቀላቸው ተነገረ፣’ ሐምሌ 12, 2016 የቀበሌ ታጣቂዎቹ መሳሪያቸውን ለመፍታት ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች ሐምሌ 2 ቀን አካባቢውን እስኪቆጣጠሩ ድረስ ውጊያው ቀጥሏል። በዚህ ውጊያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ግልጽ አይደለም። ይሁንና የየካሆ ቀበሌ አስተዳዳሪ በውጊያው ከ80 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው በመፍራት አካባቢውን ጥለው መሸሻቸውን ዘግቧል።2ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በምዕራብ ጎንደር ቋራ የ‘ፋኖ ታጣቂዎች’ ፈጸሙት በተባለ ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን እና 10 ሺህ የሚሆኑ መፈናቀላቸው ተነገረ፣’ ሐምሌ 12, 2016 ለቅማንት ብሔር (የአገው ብሔር አንድ ክፍል የሆኑ) የተሻላ እራስን በራስ የማስተዳደር ጋር ከሚቀርብ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በቅማንት የብሔር ታጣቂዎች፣ በፋኖ ታጣቂዎች፣ በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና በአካባቢ የቀበሌ ታጣቂዎች ጋር የሚደረጉ ውጊያዎች ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት በፊት የጀመሩ ሲሆኑ በጦርነቱ ወቅትም ቀጥለዋል።
በሌላ አካባቢ የፋኖ ታጣቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የተገመቱ ማንነታቸው ያልተገለፀ ታጣቂዎች ሐምሌ 10 ቀን በምዕራብ ጎንደር ዞን የሱዳን ስደተኞች የተጠለሉበት የኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሚገኘው የፀጥታ ኃይሎች ጣቢያ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። በጥቃቱ ቢያንስ ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የተገደሉ ሲሆን አንድ ህፃንን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ስደተኞች ቆስለዋል። ይህ ክስተት በመጠለያ ጣቢያው አካባቢ ከተከሰቱ ክስተቶች እጅግ የከፋው ሲሆን ይኽውም በኢትዮጵያ የሱዳን ስደተኞች እያጋጥማቸው ያለውን አደጋ ያሳያል። የሱዳን ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ድንበር አካባቢ በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያዎች ከግንቦት ወር ጀምሮ ትልቅ ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን ተመሳሳይ ክስተቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ‘አፍጥጥ’ የሚባል አዲስ የመጠለያ ጣቢያ እንደተዘጋጀ ያስታወቁ ሲሆን በአሁን ወቅት በአውላላ እና ኩመር መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ አብዛኛዎቹን ስደተኞችን ለተሻለ ደህንነት ሲባል ወደዚህ መጠለያ ጣቢያ ለማዘዋወር እቅድ አላቸው።3ዓለምነው መኮንን፣ አዜብ ታደሰ እና እሸቴ በቀለ ‘የስደተኞች ግድያና አዲሱ የመጠለያ ጣቢያ በመተማ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 15, 2016
በኦሮሚያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች
ልክ እንደ አማራ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ)—በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ በሚጠራ—እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል በሚደረጉ ውጊያዎች መሃል ሰላማዊ ሰዎች ባለፈው ሳምንትም ለአደጋ መጋለጣቸውን ቀጥለዋል። ውጊያዎች በሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች እና የሸገር ከተማ አካባቢ መደረጋቸው ተዘግቧል። ሐምሌ 8 ቀን በምዕራብ ወለጋ ቤጊ ወረዳ የመንግሥት ኃይሎች ሁለት ወጣቶችን ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን ደግፋቹኃል በሚል ክስ ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። በቀጣይ ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ ሌላ ሶሰተኛ ሰው በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉደቱ ቆንዳለ ወረዳ ውስጥ ተገድሏል።
በተመሳሳይ የፋኖ ታጣቂዎችም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሰማላዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ተከሰዋል። ሐምሌ 8 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ፣ አቡዬ ጀብላል ቀበሌ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ዘጠኝ ሰዎችን በመግደል ሶሰቱን አቁስለዋል። በሚቀጥለው ቀን ታጣቂዎቹ በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ ጅሩ ዳዳ ቀበሌ ተጨማሪ ሶስት ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል።
ተቃውሞ እየተደረገ ቢሆንም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በትግራይ ወደ ሚገኙ መኖርያ ቤቶቻቸው መመለሳቸውን ቀጥለዋል
በትግራይ ክልል ከ10,000 በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መሆኒ ከሚገኘው መጠለያ ጣቢያ (ከአላማጣ ከተማ በስተሰሜን ወደ 45 ኪሎሜትር አካባቢ ላይ የሚገኝ) ደቡባዊ ትግራይ ወደ ሚገኘው አለማጣ ከተማ ተመልሰዋል። ይህ ሁኔታ በከተማው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ከተመላሾቹ መካከል የታጠቁ የትግራይ የመከላከያ ኃይል አባላት አሉበት በማለት የሁለት ቀን የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ አድርጓል።4ሙሉጌታ በላይ፣ ‘ወደ አላማጣ ከተማ “ታጣቂ ኃይሎች እየገቡ ነው” ያሉ ነዋሪዎች ትላንት እና ዛሬ የተቃውሞ ሰልፎች አካሄዱ፣’ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 11, 2016፤ መስፍን አረጌ፣ ‘የጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ራያ አላማጣ እና አካባቢው በመመለስ ላይ ናቸው፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 12, 2016። የአለማጣ ከተማ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከሰኔ ወር መጨራሻ ጀምሮ ወደ መኖርያ አካባቢያቸው መመለስ ጀምረዋል።
በአላማጣ እና አካባቢው ያለው ውጥረት ለወራት ከፍተኛ ሆኖ ቀጥሏል። በአለማጣ ቀጠና ውስጥ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች አካላት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች በየካቲት ወር የጀመሩ ሲሆን ይኽውም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ የጣለ ጉዳይ ነው። በአካባቢው ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በሚያዝያ ወር ከበፊቱ የበለጠ የተሰፋፉ ሲሆን ይህም በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሰማሩ ምክንያት ሆኗል። ሰኔ 27 ቀን የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ኃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን አካባቢው ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ውጊያ ጊዜ ጀምሮ በአማራ አስተዳደር ስር ነበረ።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ሐምሌ 6-12, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከሐምሌ 6 አስከ 12, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 26 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 14 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት