የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ሰላማዊ ሰዎች በአማጺ ቡድኖች በሚፈጽሙት ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ፈፅመዋል ተብሏል። እነዚህ ጥቃቶች ቢያንስ የሰባት ሰላማዊ ሰዎችን ሞት አስከትለዋል። በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በጥቃቱ ምክንያት በታጣቂው ቡድን እና የፀጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
በአማራ ክልል በታጣቂዎች የተፈፀመ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት
በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች በባህርዳር በተካሄደ የሰላም ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ከመንግሥት ጋር ተባብራቹኋል በሚል 16 ሰላማዊ ሰዎችን በምዕራብ ጎጃም ዞን መጫ ወረዳ በማገት ቢያንስ አራቱን ገድለዋቸዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል የተለያዩ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች የሚገኙበት መሆኑ የተዘገበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የቀበሌ መሪ (ቄስ) ይገኙበታል።1ሰለሞን ሙጨ፣ እሸቴ በቀለ እና ፀሐይ ጫኔ፣ ‘አማራ ክልል ደቡብ ሜጫ ውስጥ በታጣቂዎች የተገደሉት ሰዎች ጉዳይ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 19, 2016 የአማራ ክልል መንግሥት ድርጊቱን በመኮነን መግለጫ ያወጣ ሲሆን 16ቱ ሰላማዊ ሰዎች ታጣቂዎቹ እንዳሉት በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ በባህርዳር በተካሄደ የሰላም ጉባኤ ላይ የተቋቋመው የሰላም ኮሚቴ አባል አይደሉም ብሏል።2የአማራ ኮሙኒኬሽን፣ ‘ንፁሃን ዜጎችን በመግደል የትኛውንም ዓላማ ማሳካት አይቻልም፣ በምንም መስፈርት ሰላም እንጂ ጦርነት አትራፊ አለመሆኑን ዓለም በተረዳበት፣’ ሐምሌ 16, 2016 ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሌላ ዘገባ ሰላማዊ ሰዎቹ ባህርዳር የሄዱት በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ለመሳተፍ መሆኑን አመላክቷል።3ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በሰሜን ጎጃም የፋኖ ታጣቂዎች ፈጸሙት ስለተባለው ማሰቃየት እና ግድያ እስካሁን የምናውቀው፣’ ሐምሌ 20, 2016
በአማራ ክልል ሳምንቱን ሙሉ ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን በደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ማዕከላዊ ጎጃም፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግበዋል። በባህርዳር የከተማ አስተዳደርሩ የፀጥታ ስጋቶችን በምክንያትነት በመጥቀስ በምሸት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የሰዓት እላፊ ጥሏል።4አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ‘የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት የተለያዩ የክልከላ ውሳኔዎችን ማሳለፋን አስታወቀ፣’ ሐምሌ 21, 2016
ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የተከሰቱ ውጊያዎች
በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች አዋሳኝ አቅራቢያ ሐምሌ 17 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች መሆናቸው የተጠረጠሩ ታጣቂዎች የኦሮሞ ማህበረሰብ ተወላጆች ላይ የፈፀሙትን ጥቃትን ተከትሎ የአካባቢው የቀበሌ ታጣቂዎች እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በዚህም በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሰው የህይወት ህልፈት ያስከተለ ውጊያ ተደርጓል። የፋኖ ታጣቂዎች በኦሮሚያ የፀጥታ ኃይሎች ወደኋላ እንዲመለሱ ከመደረጋቸው በፊት ቢያንስ ሶስት ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸው ተነግሯል።
በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራ — መካከል በሚያዝያ 2015 ይደረግ የነበረው የመጀመሪያ ዙር የሰላም ንግግር አለመሳካቱን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ያለው ግጭት ጨምሯል። የግጭቶቹ መጨመር ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጋር የተያያዘ ነው፤ ይሁን እንጂ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች በአካባቢው ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈፀም እና ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ጋር መጋጨትን ጨምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ ጀምረዋል። እ.ኤ.አ በ2024 (ከታኅሣሥ 2016 ጀምሮ) አክሌድ በዞኑ ፋኖን ያሳተፉ 14 ውጊያዎችን መዝግቧል። በመሆኑም እ.ኤ.አ በ2024 (ከታኅሣሥ 2016 ጀምሮ) የሰሜን ሸዋ ዞን በሀገሪቱ ካሉ ከፍተኛ ግጭት ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ሐምሌ 13-19, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከሐምሌ 13-19, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 25 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 2 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 12 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 0 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት