የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች የተዘገቡ ሲሆን በጋምቤላ በክልሉ ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የክልል አመራር ለውጦች ተደርገዋል። በትግራይ ክልል በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል አንደኛው ቡድን አወዛጋቢ የሆነ ጉባኤ ማድረጉን ተከትሎ ልዩነቱ ሰፍቷል።
በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈፀሙት ጥቃት
በኦሮሚያ ክልል በታጣቂ ቡድኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፀሙ ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን የሰዎችን ሞት አስከትሏል። ነሐሴ 7 ቀን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) አባላት መሆናቸው የተጠረጠሩ — በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ቢያንስ ሶስት ሰዎችን ገድሏል። ከተጎጂዎች መካከል አንዱ የኦርቶዶክስ ቄስ ነው። በጥቃቱ ምክንያት 400 የሚሆኑ አባወራዎች ተፈናቅለዋል።1ኬኔዲ አባተ፣ ‘በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ 3 ሲቪሎች በታጣቂዎች ተገድለዋል ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ነሐሴ 11, 2016 በዚህ ዞን የኦርቶዶክስ ክርስትያኖችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ። በዞኑ የመጀመሪያው ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት የተከሰተው በህዳር 2015 ውስጥ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አክሌድ 18 የተለያዩ የኦርቶዶክስ ክርስትያኖችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን የመዘገበ ሲሆን በጥቃቶቹም 73 ሰዎች ተገድለዋል። በኅዳር 2016 መንግሥት የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ 36 የኦርቶዶክስ ክርስትያኖችን በመግደል የከሰሰ ቢሆንም የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ክሱን አስተባብሏል። ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ለጥቃቱ ተጠያቂ መሆኑን ቢክድም ከጥቅምት 2016 ጀምሮ በአርሲ ዞን እየተጠናከረ የመጣ አንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር እየተካረረ በሄደ ቁጥር የተለያዩ ቡድኖች የኃይማኖት ተቋማትን መሳሪያ ሊያደርጉ የሚችሉ ሲሆን የኃይማኖት አናሳ ቡድኖች የጥቃት ሰለባ መሆናቸው ሊቀጥል ይችላል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ወርሀዊ: ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ይመልከቱ)።
የትግራይ እና ጋምቤላ ክልሎችን የተመለከቱ የፖለቲካ ዘገባዎች
በትግራይ ክልል በደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ትህነግ/ህወሓት ቡድን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጉባኤው የፓርቲውን የምዝገባ ሂደት ለማጠናቀቅ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ያልተከተለ መሆኑን በመግለጽ የሰጡትን ማስጠንቀቅያዎችን ችላ በማለት 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጓል። ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ደብረጽዮንን በድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር አደርጎ በመሾም እና አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቋል።2ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ፣ ኂሩት መለሰ እና ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‘ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና በነፈገው ጉባኤ ደብረፅዮን የህወሓት ሊቀ-መንበር ሆነው ተመረጡ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 13, 2016 ጉባኤው ጌታቸው ረዳን — የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊ — ከኃላፊነት ያነሳ ሲሆን እና ሌሎች በጉባኤው ያልተሳተፉ በርካታ የትህነግ/ህወሓት የሥራ ኃላፊዎችንም ከፓርቲው የአመራርነት አሰናብቷል።3ሙሉጌታ አጽብሃ፣ ‘በዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን አቶ ጌታቸው ረዳን ማገዱን አስታወቀ፣’ ቪኦኤ አማርኛ ፣ ነሐሴ 14, 2016 ይህ በእንዲህ እንዳለ በጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን በበኩሉ ትህነግ/ህወሓትን ከመከፈፈል ለመታደግ መሠራት ስላለባቸው ሥራዎች ለመነጋገር ሌላ ስብሰባ አድርጓል። በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ጌታቸው አዲስ የተመረጠው የማዕከላዊ ኮሚቴ ፍላጎቶቹን ለማስፈፀም ማንነቱ ያልተገለፀ ታጣቂ ቡድንን የተማመነ መሆኑን እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ለመቆጣጠር ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል አመላክተዋል።4ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በአቶ ጌታቸው የሚመራው ቡድን “ህወሓትን ማዳን” ያለውን ስብሰባ ማድረግ ጀመረ፣”’ ነሐሴ 12, 2016፤ አዲስ ማለዳ፣ ‘የትግራይ ፀጥታ ሃይሎች ስልጣን ለሚፈልጉ አካላት መሳርያ ሊሆኑ አይገባም ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ፣’ ነሐሴ 11, 2016 የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የትግራይ ኃይሎች በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ውስጥ ገለልተኛ ሆነው እንዲቆዩ ጠይቋል።5አዲስ ማለዳ፣ ‘የትግራይ ፀጥታ ሃይሎች ስልጣን ለሚፈልጉ አካላት መሳርያ ሊሆኑ አይገባም ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ፣’ ነሐሴ 11, 2016፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በህወሓት መካከል ከተፈጠረው ክፍፍል የትግራይ ኃይሎች ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ፣’ ነሐሴ 13, 2016 ይህ በእንዲህ እንዳለ የ14ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ቃል አቀባይ “አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ ትግራይን ወደ ሌላ ጦርነት ሊያመራት የሚችል ነገር የለም” ብለዋል።6አማኑኤል ጀንበሩ፣ ‘”ጦርነት አስፈላጊ ሆኖ አማራጭ ቢሆን ኖሮ ትግራይ ውስጥ ያሉት ችግሮች ሌላ ጦርነት ይጋብዙ ነበር” አቶ አማኑኤል አሰፋ፣” አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 13, 2016 ይሁንና የትግራይ መከላከያ ኃይል ገና ትጥቅ ያልፈታ መሆኑ ሲታይ በሁለቱ የትህነግ/ህወሓት አንጃዎች መካከል እየተባባሰ የመጣው ውጥረት ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል።
በጋምቤላ ክልል የክልሉ ምክር ቤት “ጉዳዮችን በመመርመር ውሳኔ ለማሳለፍ” በሚል በተጠራ አስቸኳይ ስብሰባ አዲስ የክልል አስተዳዳሪ እና ምክትል አስተዳዳሪ መርጧል።7የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢሮ፣ ‘የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 3ኛ የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል፣’ ነሐሴ 9, 2016 በዚህም አለሚቱ ኦሙድ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት የክልል አስተዳዳሪ ሆነው ተመርጠዋል። ከስልጣን የተነሱት የክልሉ አስተዳዳሪ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ አዲስ ኃላፊነት የተሰጣቸው መሆኑን ዘገባዎች ያሳያሉ።8ጋምቤላ ስታር፣ ‘ወ/ሮ. አለሚቱ ኦሙድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የክልል አስተዳዳሪ፣’ ነሐሴ 12, 2016 የጋምቤላ ክልል አስተዳዳሪዎች ከ2015 አጋማሽ ጀምሮ በአዲስ መልክ በተከሰቱ ጥቃቶች ምክንያት የፀጥታ ስጋት ለማስወገድ እየጣሩ ሲሆን አዲሱ ሹመት ለክልሉ ሰላም እና ደህንነተ አዲስ የአመራር ስትራቴጂ መፈለጉን ያሳያል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ነሐሴ 4-10, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከነሐሴ 4 እሰከ 10, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 25 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 10 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት