የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በዋና ዋና የአማራ ክልል ከተሞች ውጊያዎች የተደረጉ ሲሆን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ዳግም ግጭት ተቀስቅሷል።
ወደ አማራ ክልል ከተሞች ጦርነት መመለስ
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋር የአማራ ክልል ኃይሎች መካከል የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችው ባህርዳርን እና የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ የሆነችውን ደብረ ማርቆስን ጨምሮ በብዙ የክልሉ ትላልቅ ከተሞች እንደ አዲስ ጦርነት መደረጉ ተዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በገጠራማ አካባቢዎች ውጊያዎች ቀጥለዋል። ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ከመጋቢት 2016 በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በባህርዳር ነሐሴ 11 ቀን በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ ያነጣጠረ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሟል። በቀጣዩ ቀን በከተማዋ በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ፖሊስ ኃይሎች መካከል በበላይ ዘለቀ አየር ማረፍያ አቅራቢያ፣ በዘንዘሊማ እና ሰባት አመት ማረሚያ ቤት አካባቢ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በደብረ ማርቆስም ውግያ መደረጉ ተመዝግቧል። ጦርነቱ ከሳምንት በፊት የፋኖ ታጣቂዎች ከተማ ለመግባት ማቀዳቸውን በመጥቀስ ህዝቡ ጉዳት እንዳይደርስበት ቤት እንዲቀመጥ በባህርዳር ከተማ ያወጁትን የእንቅስቃሴ አድማ ተከትሎ የመጣ ነው። ይኽውም እንቅስቃሴ እንዲገታ እና የንግድ ተቋማት ለተወሰኑ ቀናት እንዲዘጉ አድርጓል። አድማው በባህርዳር ብቻ የተገደበ አልነበረም። ተመሳሳይ አድማዎች ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ እና ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች መደረጋቸው ተዘግቧል።1ቢቢሲ አማርኛ ፣‘ባለፉት ቀናት ውጥረት ውስጥ የገቡት አንዳንድ የአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች ሰሞናዊ ሁኔታ፣’ ነሐሴ 13, 2016
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፋኖ ታጣቂዎችን ኢላማ በማድረግ በሰሜን ሸዋ፣ በማዕከላዊ ጎንደር እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ወታደራዊ ዘመቻዎችን ማድረጉን ገልጧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የፋኖ ታጣቂዎች በአዊ ዞን፣ በምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ ዞኖች የመንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ገልጧል (ጽንፍ ስለያዘው የኢትዮጵያ የሚዲያ ምህዳር እና ወታደራዊ እርምጃዎችን የተመለከቱ የመንግሥት ዘገባዎችን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ፣ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2016 ይመልከቱ )።
ሰገን ዙሪያ ወረዳ ዳግም ግጭት ተቀሰቀሰ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደራሼ ብሔር ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ሰገን ከተማ የተዋጉ ሲሆን ከሐምሌ 2015 ጀምሮ ሰላም በነበረ አካባቢ ዳግም ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርጓል። ውጊያው ነሐሴ 11 ቀን የጀመረ ሲሆን በቀጣዩ ቀን በነሐሴ 12 ቀንም የታጣቂ ቡድኑ ከተማዋን እስኪቆጣጠራት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል። ታጣቂ ቡድኑ ነሐሴ 16 ቀን ከተማዋን ለቆ እስኪወጣ እና በተመሳሳይ ቀን የፌዴራል ኃይሎች አካባቢውን መልሶ እስኪቆጣጠሩ ድረስ የህዝብ እና የግል ንብረቶችን አውድሟል።
የኮንሶ እና የሰገን ዙሪያ ህዝቦች ዞኖች ግጭት በ2010 የኮንሶ ወረዳ ወደ ዞን ማደጉን ተከትሎ በተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያት የተጀመረ ነው። የደራሼ ወረዳ ከቡርጂ፣ ኮንሶ እና አማሮ ጋር በተመሳሳይ ‘የልዩ ወረዳ’ ደረጃ የነበረው ሲሆን የኮንሶ ወረዳ ወደ ዞን ደረጃ ሲያድግ ይህንን ‘የልዩ ወረዳ’ ደረጃ አጥቶታል። የኮንሶ እና የሰገን ዙሪያ ህዝቦች ዞኖች ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር በተያያዘ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ተደጋጋሚ ግጭቶች የሚታይባቸው አካባቢዎች ሆነው የቆዩ ሲሆን እነዚህ ግጭቶች በ2015 ቆመው ነበር። በነሐሴ 2014 አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ እና አሌ የዞን ደረጃ አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ነሐሴ 11-17, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከነሐሴ 11 እስከ 17, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 31 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 3 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 9 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት