የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር ግጭት የጨመረ ሲሆን በአማራ ክልል በሰሜን እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተጠናከሩ ውጊያዎች ተደርገዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) አንጃዎች መካከል የተፈጠረው የውስጥ ልዩነት እየተባባሰ የቀጠለ ሲሆን ወደ ግጭት እንዳያመራ ስጋት ፈጥሯል።
በምዕራብ አማራ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ውጊያዎች እንደገና ጀምረዋል
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ያለው ጦርነት ሳይቋረጥ የቀጠለ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በምዕራብ አማራ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ውጊያዎች እንደገና ጀምረዋል። መስከረም 6 እና 7 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ክልል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች በጋራ በመሆን ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሰሜን እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በጎንደር ከተማ እና አካባቢው እንዲሁም በቢ30 አውራ ጎዳና ላይ በሚገኙ የደባርቅ፣ ዳባት፣ አምባ ጊዬርጊስ እና አዘዞ ከተሞች ተዋግተዋል። የፋኖ ታጣቂዎች በፀጣታ ኃይሎች ወደ ኃላ እንዲመለሱ ከመደረጋቸው በፊት በብዙ አካባቢዎች ለአጭር ጊዜ ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠር ችለው ነበር። በከተሞች አካባቢ በተደረጉ ውጊያዎች ለበርካታ የሰላማዊ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎቶችም ለአጭር ጊዜ ተቋርጠው ነበር።1የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ‘በጎንደር ከተማ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎትና የንግድ ተቋማት የዕለት ተዕለት ተግባራት እየተከናወኑ ነው፣’ መስከረም 8, 2017
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። መስከረም 8 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በምስራቅ ጎጃም ሰነን ወረዳ የፋኖ ታጣቂዎች ያስተላለፉትን ትዕዛዝ በመተላለፍ ተማሪዎችን መዝግበዋል ብለው የከሰሱዋቸውን ሁለት አስተማሪዎችን መግደላቸው ተዘግቧል። የፋኖ ተወካዮች በግድያው መሳተፋቸውን ያስተባበሉ ቢሆንም በአካባቢው እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ተማሪዎች ትምህርት ቤት መሄዳቸውን እንደሚቃወሙ አረጋግጠዋል።2ደረጀ ደስታ፣ ‘በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ሁለት መምህራን መገደላቸውን የአካባቢው አስተዳደር አስታወቀ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ መስከረም 9, 2017 በአማራ ክልል ህፃናትን፣ አስተማሪዎችን፣ ስደተኞችን፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን እና የመንግሥት ሰራተኞችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በሰዎች የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። በአክሌድ የግጭት ተጋላጭነት ማስለያ መሠረት በአማራ ክልል ከሚያዚያ 2015 ጀምሮ ከ7 ሚሊዬን በላይ ህዝብ ለግጭት ተጋልጧል። በክልሉ በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ባለው በግጭት ምክንያት ከትምህርት ቤት ውጪ ሲሆኑ ይኽውም በብሔራዊ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመልቀቅያ ፈተና በክልሉ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛ ውጤት እንዲያመጡ አስተዋጽኦ አድርጓል።3ቦርከና፣ ‘ኢትዮጵያ : ሚኒሰቴሩ አስከፊ የሆነ የ12ኛ ክፍል ውጤት ይፋ አደረገ፣’ ጳጉሜ 4, 2016
በትግራይ ክልል በትህነግ/ህወሓት አንጃዎች መካከል ያለው ውጥረት መጨመር
በትግራይ ክልል በትህነግ/ህወሓት አንጃዎች መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ ሲሆን የትግራይ አስተዳደር አመራር በደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራውን አንጃ/ቡድን አመራሩን በማንሳት ስልጣን ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው ሲል ከሶታል።4ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ፣ ሸዋዬ ለገሠ እና ፀሐይ ጫኔ፣ ‘በህወሃት መሪዎች መካከል የቀጠለው ውዝግብ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 9, 2017 እነዚህ ውጥረቶች በቅርቡ በሁለቱም ወገኖች በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ ታይተዋል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በጌታቸው ረዳ የሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቡድን በተለያዩ ከተሞች እና አካባቢዎች ህዝባዊ ውይይቶችን አድርጓል። መስከረም 5 ቀን በሽረ ከተማ ስብሰባ ለማድረግ ሙከራ በተደረገበት ወቅት አንዳንድ በደብረጽዮን አንጃ ተጽዕኖ እንደተደረገባቸው የሚገመቱ ተሳታፊዎች ሲጮኹ እና በጌታቸው ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ሌሎች ደግሞ ለእሳቸው ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። በተፈጠረው የረብሻ ጩሀት ምክንያት ስብሰባው መቀጠል ባለመቻሉ ጌታቸው ስብሰባውን ትተው ወተዋል።5ሚልዮን ሃይለስላሴ፣ ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር እና ፀሐይ ጫኔ፣ ‘የተሰናከለው ስብሰባ ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 6, 2017 ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት የደብረጽዮን ቡድን በክልሉ ረብሻ እና አለመረጋጋትን እየፈጠረ ያለው የጌታቸው ቡድን መሆኑን ህዝቡን ለማሳመን በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ ጀምሯል።6ዩቲዩብ@ኢትዮሪፖርተር፣ ‘”እነ ጻድቃን ‹‹ከሃገር እንድወጣ ይገፋፉኝ ነበር” – ዶ/ር ደብረጽዮን፣’ መስከረም 13, 2017
በሁለቱ የትህነግ/ህወሓት አንጃዎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ በመሄዱ በክልሉ አስተዳደር እና በፓርቲው አመራር መካከል የውስጥ ክፍፍል የፈጠረ ሲሆን ወደ ግጭት እንዳያመራም ስጋት ፈጥሯል። የትህነግ/ህወሓት ሊቀመንበር ለሆነው ለደብረጽዮን የወገኑ የትህነግ/ህወሓት ኃላፊዎች የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ነገሮችን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት የደብረጽዮን ደጋፊ የሆኑ አመራሮችን ከሥራ በማባረር እና በቁጥጥር ስር በማዋል እንዲሁም ሰልፎችን በመከልከል ይከሱታል።7አብረሃም ተክሌ፣ ‘በትህነግ/ህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል እየተባባሰ ሲመጣ ለገልተኝነት የሚደረጉ ጥሪዎች እየተሰሙ ነው፣’ ሪፖርተር፣ መስከረም 4, 2017 በቅርቡ 16 የትህነግ/ህወሓት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ከፓርቲው በመታገዳቸው በደብረጽዮን የሚመራው አንጃ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የትህነግ/ህወሓት ውክልና እንዲስተካከል ጥሪ እያደረገ ይገኛል።8ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በደብረጽዮን የሚመራው ማዕከላዊ ኮሚቴ እነ አቶ ጌታቸውን አገደ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩም እንዲስተካከል ጠየቀ፣’ መስከረም 7, 2017 ጌታቸው ረዳን ጨምሮ እነዚህ የታገዱ አመራሮች በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎችን የያዙ ናቸው። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ በበኩሉ ልዩነቱ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በትህነግ/ህወሓት መካከል ሳይሆን በትህነግ/ህወሓት አመራሮች መካከል ብቻ መሆኑን አፅኖት ሰጥቷል።9ሙሉጌታ አጽብሃ፣ ‘በህወሓት ክፍፍል ውስጥ ለማንም አልወግንም ሲል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ አስታወቀ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ መስከረም 13, 2017 በተጨማሪም ተገቢነት ባላቸው ደንቦች መሠረት የሥራ ኃፊዎችን መሾሙን እና ማሰናበቱን እንደሚቀጥልም አሳውቋል።
መስከረም 2 ቀን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አተገባባር ላይ ለመወያየት ከክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደር ጋር የተገናኙ ሲሆን ሁለቱ የትህነግ/ህወሓት አንጃዎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጠይቋል።10ኤክስ@ዩኤስኢምባሲአዲስ፣ መስከረም 2, 2017፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው በህወሓት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በንግግር እንዲፈታ ጥሪ አቀረቡ፣’ መስከረም 4, 2017 ሁለቱም አንጃዎች በሰላም ስምምነቱ ይዘት እና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰበት መንገድ ላይ ያላቸውን ልዩነትም ገልፀዋል። የደብረጽዮን ቡድን ጌታቸው ረዳን እና የእሳቸውን ቡድን ትህነግ/ህወሓትን ለማፍረስ የታቀደበት ያሉትን ስምምነት በመፈረም ተጠያቂ ያደርጉዋቸዋል።11አማኑኤል ጀንበሩ፣ ‘“የፕሪቶሪያው ስምምነት አደራዳሪዎች ህወሃትን የማጥፋት ስራ ሰርተዋል’’ አቶ አማኑኤል አሰፋ፣’ አዲስ ማለዳ ፣ ነሐሴ 30, 2016 በሌላ በኩል በጌታቸው የሚመራ ቡድን ይህንን አባባል የማይቀበል ሲሆን የሰላም ስምምነቱ መከበር ያለበት የአለም አቀፍ ሰነድ መሆኑን ደጋግሞ ያሰረዳል።12መስፍን ፈለቀ፣ ‘“ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ውል ነው መከበር አለበት” ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ፣’ አዲስ ማለዳ ፣ ጳጉሜ 1, 2016
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
መስከረም 4-10, 2017
ይህ መረጃ/ዳታ ከመስከረም 4 እስከ 10, 2017 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 25 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 0 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 7 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 1 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት