የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተከሰተ ብዙም ያልተለመደ ጥቃት የቀበሌ አስተዳዳሪን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። በኦሮሚያ ክልል ውጊያ በቀጠለበት በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ በሚጠራው — አንድ ቡድን እና በመንግሥት መካከል የሰላም ስምምነት ተፈርሟል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተከሰተ ብዙም ባልተለመደ ጥቃት 20 ሰዎች ተገደሉ
ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን አንደራቻ ወረዳ ሸኪቢዶ ቀበሌ ውስጥ የመዥንገር ብሔር ታጣቂዎች በፈፀሙት ብዙም ያልተለመደ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰላማዊ ሰዎቸ መገደላቸው ተዘግቧል። በአካበቢው ነዋሪዎች መሠረት ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከጋምቤላ ክልል መዣንግ ዞን ወሰን ተሻግረው ወደ ሸካ ዞን በመግባት ገበሬዎችን እና የመንግሥት ሠራተኞችን አጥቅተዋል። የሸኪቢዶ ቀበሌ አስተዳዳሪ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ናቸው።1ሸዋንግዛው ወጋየሁ፣ ሸዋዬ ለገሠ፣ ፀሐይ ጫኔ ‘የአንዳራቻ ነዋሪዎች ሥጋት፣’ ኅዳር 20, 2017 የፌዴራል ፖሊስ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈፀም ለመከላከል አካባቢውን ተቆጣጥሯል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኅዳር 14, 2014 ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በመውጣት የተመሠረተ ነው። በክልሉ በሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰት የፖለቲካ ብጥብጥ ታሪክ ቢኖርም አካባቢው በአንፃራዊነት ሰላማዊ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል የሰላም ስምምነት ተፈረመ
ኅዳር 22 ቀን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በጥቅምት ወር ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ዋና አመራር መለየቱን ካሳወቀው ከቀድሞ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ከሰኚ ነጋሳ ጋር የሰላም ስምምነት ፈርሟል። የክልሉ መንግሥት ስምምነቱ ታጣቂ ቡድኖችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የተደረገው ‘የሰላም ጥሪ’ ውጤት መሆኑን አብስሯል።2ፌስቡክ@ኦሮሚያቢሲ፣ ኅዳር 22, 2017 በተቃራኒው የዋናው ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ አመራር ቃል አቀባይ የሰላም ስምምነቱን ‘ቀልድ’ በማለት ያጣጣሉ ሲሆን ሰኚ ነጋሳን ክብሩ ተዋርዶ ከኃላፊነቱ የተባረረ የቀድሞ አባል በማለት ገልጾታል።3ቪኦኤ አማርኛ፣ ‘የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከኦነግ የጦር መሪ ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ፣’ ኅዳር 22, 2017 የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ይፋዊ መግለጫዎች ከፌዴራል ወይም ከክልል መንግሥት ጋር እየተካሄደ ያለ ምንም ዓይነት የሰላም ንግግር አለመኖሩን ይገልፃሉ።4አሸናፊ እንዳለ ፣‘ኦሮሚያ ክልል ከኦነሠ ጋር የሰላም እየተካሄደ ነው አለ፣ የታንዛንያ የሰላም ንግግርን ማዘጋጀቱንም ገለፀ፣ ’ ዘ ሪፖርተር ፣ ኅዳር 21, 2017
ሰኚ ነጋሳ ከዋናው አመራር እንደተለየ ከመንግሥት ጋር የሰላም ድርድር ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ለድርድር ፍቃደኛ መሆናቸው የግጭት መጠንን እንደሚቀንስ የፈጠረው ተስፋ በአካበቢው ከትንሽ እፎይታ በኋላ ውጊያ እንደገና በመጀመሩ ምክንያት በፍጥነት ተመናምኗል። በሰኚ ነጋሳ የሚመራ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ የማዕከላዊ ዕዝ የሰሜን ሸዋ ዞንን የሚሸፍን ሲሆን —ዞኑ ከግንቦት 2015 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ግጭት ያስተናገደ ያለ ዞን ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች እና ውጊያዎች ቀጥለዋል። የመንግሥት ኃይሎች በምሥራቅ ወለጋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔን ኢላማ ያደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን መጀመራቸውን ገልፀዋል። በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ተዋጊዎች በርካታ ሰዎችን ከቤታቸው አግተው ከወሰዱ በኋላ ዘጠኝ ሰዎቸን ተኩሰው መግደላቸው ተዘግቧል። ባለፈው ሳምንት ሌሎች ሦስት ተጨማሪ ሰዎች በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ኃይሎች መገደላቸው ተዘግቧል። አንዳንድ ነዋሪዎች ጥቃቱ ክርስቲያኖችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።5ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዘጠኝ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ተናገሩ፣’ ኅዳር 20, 2017 በአርሲ ዞን ክርስትያኖችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ (እነዚህን ጥቃቶች በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢትዮጵያ ሳምንታዊ ዘገባ (ነሐሴ 14, 2016) እና የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ኅዳር 15 አስከ ኅዳር 21, 2016 ይመልከቱ)። ከጥቅምት 21, 2016 አስከ ኅዳር 20, 2017 በአርሲ ዞን አክሌድ 48 ሟቾች የተመዘገቡበት ዘጠኝ ተመሳሳይ ጥቃቶችን መዝግቧል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ኅዳር 14-20, 2017
ይህ መረጃ/ዳታ ከኅዳር 14 እስከ 20, 2017 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 32 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 3 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 10 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 0 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት