የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከመንግሥት ጋር የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሰኚ ነጋሳ የሚመራ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — ቡድን ተዋጊዎች በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተሃድሶ ጣቢያ ገብተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች በሸዋ ሮቢት፣ በደላንታ እና በደጋ ዳሞት ወረዳዎች ተባብሰዋል።
በኦሮሚያ ክልል ተዋጊዎች የተሃድሶ ጣቢያዎች ገቡ
ኅዳር 22 ቀን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ የቀድሞ የማዕከላዊ ዞን አዛዥ ሰኚ ነጋሳ ቡድን መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች የመንግሥት የተሃድሶ ጣቢያ ገብተዋል። በስምምነቱ መሠረት ታጣቂዎቹን ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ ለማዋሀድ በመንግሥት የሚተዳደሩ ካምፖች ተዘጋጅተዋል። በመንግሥት ምንጮች መሠረት በአብዛኛው ከምዕራብ እና ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተወጣጡ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች1ገልሞ ዳዊት፣ ‘የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ወደ ማዕከላት እየገቡ መኾኑን ክልሉ አስታወቀ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ኅዳር 25, 2017 እጅ በመስጠት በምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች የሚገኙ የተሃድሶ ጣቢያዎች የገቡ ሲሆን አብዛኛዎቹ ወደ ሰማይ ጥይት በመተኮስ ደስታቸውን ገልፀዋል። ኅዳር 29 ቀን በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባ በነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤን የፈጠረ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ የከተማዋ ፖሊስ ባወጣ መግለጫ የቀድሞ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች ወደ ተሃድሶ ጣቢያ በመሄድ ላይ እያሉ በዋና ከተማዋ ሲያልፉ ደስታቸውን ለመግለጽ መሳሪያቸውን ወደ ሰማይ መተኮሳቸውን አብራርቷል።2ፌስቡክ @አዲስአበባፖሊስ፣ ኅዳር 29, 2017 ተመሳሳይ የተኩስ ድምጾች በሌሎችም የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተሰምተዋል።3ሥዩም ጌቱ፣ አዜብ ታደሰ እና ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር፣ ‘በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተከፈተ የተባለው የተኩስ እሩምታ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ኅዳር 30, 2017
ኅዳር 27 ቀን በመንግሥት ቴሌቪዥን በተላለፈ የጋዜጣዊ መግለጫ የቀድሞ አዛዥ ሰኚ ነጋሳ የተፈረመውን ስምምነት በማስመልክት የፀጥታ እና የተዋጊዎች ተሃድሶን የሚመለከቱ የስምምነቱ አንቀጾችን በመጥቀስ አጠቃላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከእነዚህም መካከል የቀድሞ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች ከመንግሥት ወታደሮች፣ ከፖሊስ እና ከአካባቢ ታጣቂዎች ጎን በመሆን በፀጥታ እና ደህንነት ዘርፍ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ነጋሳ የተሃድሶ ሂደቱን ለመከታተል የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅሰው በአሁኑ ስምምነት ውስጥ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ያልሆነ ቡድን በአፈፃፀሙ ላይ ድርሻ ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ አድርገዋል።4ዩቲዩብ @ኢቢሲወርሊድ፣ ‘ጃል ሰኚ ምን አሉ?|ኢቲቪ | ኢትዮጵያ | ዜና፣” ኅዳር 27, 2017 ይህ ኮሚቴ በ2010 በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረው አይነት አለመግባባት እንዳይከሰት ለመከላከል የተመሠረተ ይመስላል። በ2010 ስምምነት ላይ የተፈጠረው አለመግባባት ኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ከኦነግ ፓርቲ እንዲገነጠል ምክንያት የሆነ ሲሆን ይህን ተከትሎ በ2011 በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና በመንግሥት መካከል ውጊያ እንዲቀሰቀስ አድርጓል። አሁን ላይ በሰኚ ነጋሳ እና በመንግሥት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ዝርዝር ይዘቱ ለጊዜው ለህዝብ ይፋ አልተደረገም። የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ኦፊሴላዊ ቃል አቀባይ ሰኚ ነጋሳ ከብዙ ወራት በፊት ከድርጅቱ አመራርነት መባረሩን በማስታወስ ስምምነቱን “የፈጠራ ድራማ” በማለት አጣጥሎታል።5ኤክስ @ኦነግ_ኦነሠ፣ ኅዳር 24, 2017
በዚህ ሳምንት የተፈጠሩ ክስተቶች አወንታዊ ቢሆኑም በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት በቅርቡ የሚቆም እንደሆነ ተደርገው መወሰድ ግን የለበትም። በተለይም በአማራ ክልል በሚገኙ ከፋኖ ጋር የተያያዙ ታጣቂዎችን ያሳተፉ በክልሉ ወሰን አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች የመንግሥትን የፀጥታ ዘርፍ በማሳሳት እና ለተጨማሪ ግጭቶች መንገድ በመክፈት ጫና እየፈጠሩ ይገኛሉ። ኅዳር 23 ቀን ከኪረሙ ወረዳ የመጡ የፋኖ ታጣቂዎች በአሙሩ ወረዳ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ወሰን አቅራቢያ ቢያንስ አምስት ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። በባለፈው አንድ ዓመት አክሌድ በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ 104 ውጊያዎችን እና የፋኖ ታጣቂዎች ዋና ጥቃት ፈፃሚ የሆኑበትን ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ክስተቶችን መዝግቧል። የፋኖ ታጣቂዎች በስፋት እየተንቀሳቀሱ በመጡባቸው አካባቢዎች ሁለቱም የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና የመንግሥት ኃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በሚደረጉ ውጊያዎች ውስጥ የተሳተፉ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ እርስ በእርሳቸውም — የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና የመንግሥት ኃይሎች — ተዋግተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምንጮች ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ኃይሎች ጋር በጉጂ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውጊያ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
በአማራ ክልል ከ30 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገደሉ
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ኅዳር 24 ቀን ውጊያ የተጀመረ ሲሆን በኅዳር 25 እና 27 ላይም ውጊያዎች መቀጠላቸው ተዘግቧል። በውጊያው ቁጥራቸው በውል ካልታወቀ ተዋጊዎች በተጨማሪ ቢያንስ ስድስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምንጮች የፋኖ ታጣቂዎች የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤትን ኢላም ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የሚትገኘውን ፀሃይ መውጫ ከተማን መልሶ ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የቀጠሉ ውጊያዎች ተደርገዋል። ውጊያው ኀዳር 19 ቀን የጀመረ ሲሆን ቤቶች እና የአርሻ ሰብል በከባድ መሣሪያ በተደረጉ ውጊያዎች ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ በፈረስ ቤት ከተማ ኀዳር 26 ቀን የፋኖ ታጣቂዎች የወረዳው ኃላፊን ጨምሮ ከ30 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ከያዙ በኋላ መግደላቸው የተዘገበ ሲሆን እነዚህን የሥራ ኃላፊዎች ሌሎች ከ70 በላይ ከሆኑ ሰዎችን ጋር ለሁለት ወራት በማገት ከቤተሰቦቻቸው የማሰለቀቅያ ገንዘብ ሲጠይቁ ነበር። ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን የገደሉት በአካባቢው ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ከተዋጉ በኋላ ነው። ፈረስ ቤት ከተማ ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የቆየች መሆኑ የተዘገበ ሲሆን ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ ታጣቂዎቹ ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል።6ዓለምነው መኮንን እና እሸቴ በቀለ፣ ‘በአማራ ክልል የደጋ ዳሞት ወረዳ 37 አመራሮች መገደላቸው ተገለፀ፣’ ኅዳር 28,2017 በውጊያው ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብዙ የድሮን ጥቃቶችን የፈፀመ ሲሆን በእነዚህ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች እና የፋኖ ታጣቂዎችን ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገድለዋል።7ዓለምነው መኮንን እና እሸቴ በቀለ፣ ‘በአማራ ክልል የደጋ ዳሞት ወረዳ 37 አመራሮች መገደላቸው ተገለፀ፣’ ኅዳር 28,2017 የድሮን ጥቃቶቹ በዚህ አካባቢ ብቻ አልተገደቡም። ኅዳር 23 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን ቢልብላ ከተማ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተፈፀመ የድሮን ጥቃት አንድ እድሜያቸው የገፋ ሴት እና ሁለት የጤና ባለሙያዎችን መግደሉ ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ኅዳር 21 እስከ 27, 2017
ይህ መረጃ/ዳታ ከኅዳር 21 እስከ 27, 2017 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 23 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 4 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 4 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 0 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት