በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሚያዚያ 15, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,502
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 6,967
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 3,819
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
የተለያዩ ቡድኖች የሚያደርሱትን የኃይል ጥቃቶችን እና በመላው ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች መፈናቀልን በማውገዝ ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በሰልፎቹ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚጠይቁ መፈክሮችን አንግበው የነበረ ሲሆን የተወሰኑ ደግሞ በስልጣን ላይ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ከኦሮሞ አክራሪ ቡድኖች ጋር ያለውን ግንኙነት አዉግዘዋል፡፡ አብዛኞቹ ሰልፎች ሰላማዊ የነበሩ ቢሆንም በሦስተኛው ቀን በባህር ዳር ከተማ ሰልፈኞች ሰልፎቹን ለመበተን ከሞከሩ የደህንነት ሀይሎች ጋር ተጋጭተዋል፡፡
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ከጉሙዝ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች የአካባቢውን የደህንነት ሀይሎች በማጥቃት የሴዳል ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው ዲዛን ጨምሮ ወረዳውን ፟ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ፟ ተቆጣጥረዋል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሚያዚያ 13, 2013)።
በአማራ ክልል መአከላዊ ጎንደር አይከል ከተማ (ቺልጋ) የቅማንት ብሄርተኛ ቡድን አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ሀይል ጋር የተጋጩ ሲሆን ይህንን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት እና ተጨማሪ ሀይሎች ወደቦታው ገብቷል።
በኦሮሚያ ክልል በአማራ እና ኦሮሞ የብሄር ተዋጊዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በአያና ውስጥ በሚገኙት መንደር 8፣ መንደር 9፣ መንደር 10፣ እና አርኩምቢ አካባቢዎች ቀጥሏል። ዘገባዎች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ታጣቂዎች በግጭቱ መሳተፋቸውን ያሳዩ ሲሆን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች ተገድለዋል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ የፌዴራል ኃይሎች ከኦነግ–ሸኔ ሀይሎች ጋር መዋጋታቸውን ቀጥለዋል ፡፡
በመጨረሻም በትግራይ ክልል የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሃ.ት.) እና የትግራይ ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ላይ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ኃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፡፡
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
በትግራይ ክልል ከህ.ወ.ሀ.ት. ጋር ግንኙነት ባላቸው ሃይሎች እና የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወታደሮች መካከል በብዙ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ግጭቶች ነበሩ። የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት እውቅና ሰጥቶ አሁንም ድረስ የቀጠለው የፀጥታ ችግር ግን ሰብአዊ ስራዎችን ለማከናወን እንቅፋት መፍጠሩን አመልክቷል (የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ፣ ሚያዚያ 14, 2013)። በተጨማሪም የሳልሳዊ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ ሁለት ከፍተኛ አመራሮች በሚያዚያ 14, 2013 በመቀሌ ከተማ ታስረዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 15, 2013)። የተያዙበት ምክንያት ባይገለጽም ፓርቲው እስራቱ ፖለቲካዊ መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ባለው የትግራይ ህዝብ ላይ ያለውን የፀጥታ ችግር በመቃወማቸው የተፈፀመ መሆኑን ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የተቋቋመው ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ብሎ ባሳወቀው የጷጉሜ 2012 የትግራይ ክልል ምርጫ ላይ ከተሳተፉ አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ ነው፡፡
ክልላዊ ትኩረት :- አማራዎችን ኢላማ ያደረጉ ግድያዎች እና ማፈናቀል በመቃወም በአማራ ክልል የተደረጉ ሰልፎች
የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቡድኖች የሚፈፀሙ አማራዎችን ኢላማ ያደረጉ ግድያዎች እና ማፈናቀል ላይ ምላሽ አለመስጠቱ በአማራ ክልል ውስጥ ያስከተለው ቅሬታ ባለፉት አመታት እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት የነበሩ ሰልፎች ከመጋቢት 9 እስከ 22 ድረስ በአማራ ክልል በኦሮሞ ዞን እና ዙሪያውን ባሉ ከተሞች በኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰቦች መካከል የነበረው ግጭት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ዞን ውስጥ የተነሱ ጥቃቶችን ተከትሎ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ የተቀሰቀሱ ናቸው። ከኦነግ–ሸኔ መሆናቸው የታመነ ታጣቂዎች አና የአካባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች በአጣዬ፣ ሸዋ ሮቢት ፣ ካራቆሬ ፣ መቆያ (አንፆኪያ) ፣ ኤፍራታ ግድም፣ እና ማጀቴ ከተሞች (ለተጨማሪ መረጃዎች ያለፈውን ሳምንት ኢፒኦ ሳምንታዊ ይመልከቱ) ጥቃት አድርሰዋል፡፡ ከመጋቢት 9 እስከ 22 እና ከሚያዚያ 8 እስከ 10, 2013 የነበሩ ከፍተኛ ግጭቶች እና ዘርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች በግምት 350 ለሚሆኑ ሰዎች ሞት እና ከ328,000 በላይ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል (ዲደብሊው አማርኛ, ሚያዚያ 13, 2013, አፍሪካ ኒውስ, መጋቢት 26, 2013, ሬውተርስ, ሚያዚያ 12.2013)።
ሚያዚያ 11 በደሴ እና ደብረ ማርቆስ የተጀመሩት ሰልፎች በኋላ ወደ ባህር ዳር፣ ወልድያ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወሎ፣ ላሊበላ፣ ኮን፣ ዋድላ፣ ጎንደር፣ እንጅባራ፣ ደባርቅ፣ ደንበጫ፣ እናርጅ እና እናውራ፣ ደብረ ወርቅ፣ ደጀን፣ ዳንግላ፣ ቡሬ፣ አዲስ ቅዳሜ፣ ቲሊሊ፣ ቢቸና፣ እና ሰቆጣ ከተሞች ተስፋፍተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ) (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 12,2013፣ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 12, 2013፣ ሚያዚያ 13, 2013፣ ሚያዚያ 14, 2013 (ሀ)፣ ሚያዚያ 14, 2013 (ለ)፣ ሚያዚያ 15, 2013፣ አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 12, 2013፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 16, 2013 ፣ ሚያዚያ 17, 2013)። የሰልፎቹ ተሳታፊዎች ሳምንቱን ሙሉ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እና ድርጊቱን የፈፀሙትን ለህግ እንዲያቀርብ አሳስበዋል ፡፡
አብዛኞቹ ሰልፎች ሰላማዊ የነበሩ ቢሆንም ፀረ-መንግስታዊ መልእክቶች እና በአጣዬ እና ዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ለደረሰው ጥቃት የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲን2ብልጽግና ፓርቲ ብሄርን መሰረት አድርገው የተደራጁ ቡድኖች ውጤት ሲሆን በውስጡ ከሌሎች በተጨማሪ የኦሮሞ እና አማራ ክፍሎች አሉት። ተጠያቂ የሚያደርጉ የአማራ ብሄርተኝነት መፈክሮችን ያካተቱ ነበሩ (አካባቢው ላይ ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከመጋቢት 18, 2013 እስከ መጋቢት 24, 2013)። ለምሳሌ ሰልፎቹ የተጀመሩ እለት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ተሳታፊዎች ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን የብልጽግና ፓርቲን ማስታወቂያዎች አቃጥለዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 12, 2013). በአንዳንድ ሁኔታዎች ሰልፎቹ ፀረ-ኦሮሞ ድምጽ የተንፀባረቀባቸው ሲሆን አንዳንድ ሰልፈኞች “ኦሮሙማን አጥፉ” የሚሉ ምልክቶችን ይዘው ነበር። ድርጊቱ በአንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና የአባ ገዳ አመራሮች (የኦሮሞ ባህላዊ ሽማግሌዎች) ተወግዟል (ኦሮሚያ ግንኙነት ቢሮ፣ ሚያዚያ 16, 2013; ኦኤምኤን፣ ሚያዚያ 13, 2013; ታዬ ደንደአ አረዶ፣ ሚያዚያ 12, 2013)። የአማራ ክልላዊ መንግስትም እንደዚ አይነት ድርጊቶችን አውግዟል። የክልሉ መንግስት አብዛኞቹ ሰልፎች ሰላማዊ እንደነበሩ ገልፆ አንዳንድ ፟አክራሪ ሀይሎች ፟ ጥላቻ እና አለመተማመን የሚፈጥሩ እና በአማራ እና ኦሮሞ ብሄሮች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን የሚያበላሹ ድርጊቶችን በማድረግ የሰልፉን አቅጣጫ ለማስቀየር ሞክረዋል ብሏል (የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 13, 2013; የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 15, 2013)።
ሰልፎቹ በባህር ዳር ከተማ በሦስተኛው ቀን ወደ አመፅ የተቀየሩ ሲሆን የሰልፉ ተሳታፊዎች መንገዶችን ዘግተው ሰልፉን ለመበተን ከሞከሩ የፀጥታ ሀይሎች ጋር ተጋጭተዋል። ዘገባዎች 4 የሰልፉ ተሳታፊዎች እና 30 የፀጥታ ሀይሎች መጎዳታቸውን ያሳያሉ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 15, 2013; የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 15, 2013)። ሀላፊዎች የክልሉ መንግስት የሰልፉን ተሳታፊዎች ጥያቄ እንደተቀበለ እና አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር አብሮ እየሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል (የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 13, 2013)።.
በመላ ሀገሪቱ የሚደርሱ አማራዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች በክልሉ ውስጥ ለብልጽግና ፓርቲ ያለውን አመለካከት ሸርሽሯል። የብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ ደጋፊዎች እንኳን በፓርቲው የአማራ እና ኦሮሞ ክንፎች መካከል ችግር ያለው ልዩነት መኖሩን ይቀበላሉ፡፡ በመጋቢት እና ሚያዚያ 2013 ውስጥ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተው ያልተጠበቀ ከፍተኛ ጥቃት መራጮች የአማራ ብልጽግና ፓርቲ የክልሉን ደህንነት ማስጠበቅ ይችላል ብለው እንዳይተማመኑ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ ውስጥ አማራዎች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የመንግስት ምላሽ አለመስጠት እና የዘገየ ምላሽ መስጠት ያስከተለው ቅሬታ ለደህንነት ስርአቱ ክፍተት እርስ በእርስ በሚካሰሱት የኦሮሞ እና አማራ ክልላዊ መንግታት መካከል ጥልቅ ልዩነት እንዲፈጠር አድርጏል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት ችግሩን ለመፍታት ብቃት የላቸውም የሚለው ግንዛቤ ብሄርተኛ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያለው ድጋፍ እንዲጠናከር ምክንያት ሆኗል። ይህንን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ያሉ አናሳዎች ላይ የተፈጠረው ድንጋጤ ባለፈው ሳምንት የነበረ ስብሰባ ወደ ግጭት እንዲቀየር እና በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘው የቅማንት ማህበረሰብ ከአማራ ክልል ልዩ ሀይሎች ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል፤ በግጭቱ 32 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 14, 2013; የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 15, 2013; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 11, 2013)።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች እና ግጭቶች
ባለፈው ሳምንት ሁለት የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በአማራ ክልል ተገድለዋል። ግድያዎቹ በክልሉ በቅርቡ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ግንኙነት ነበራቸው። ሚያዚያ 8 2013 ላይ በኤፍራታ ግድም ወረዳ (ሰሜን ሸዋ፣ አማራ ክልል) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እጩ ተወዳዳሪ የነበረ ግለሰብ በአጣዬ ከተማ በኦነግ-ሸኔ (እና የአካባቢ ኦሮሞ ታጣቂዎች) እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይሎችና የፌደራል ሀይሎች መካከል በነበረው ግጭት ወቅት ባልታወቀ ታጣቂ ቡድን ተገድሏል (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ ሚያዚያ 13 2013)። ሚያዚያ 13, 2013 የአብን ፓርቲ አባል እና የወጣት ክንፉ መሪ የነበረው ግለሰብ በመተማ (ምዕራብ ጎንደር፣ አማራ ክልል) በተኩስ ተገድሏል (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ሚያዚያ 14 2013)። የምርጫውን መቅረብ ተከትሎ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ግጭት መጨመሩን ቀጥሏል።