ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 20, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,557
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,713
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,203
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013)
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 26
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 398
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 37
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በትጥቅ ግጭቶች ምክንያት የተፈጠረው አለመረጋጋት ባሳለፍነው ሳምንት ላይም የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች መንግስታትን መፈታተኑን ቀጥሏል፡፡ ግንቦት 14, 2013 ጠዋት ላይ የጉሙዝ ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ አባላት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 17 ታጣቂዎች የቤንሻንጉል/ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልል ወሰንን አቋርጠው ነጆ ወረዳ (ኦሮሚያ ክልል) በሚገኘው ያምበልጋራ ኦሊ ቀበሌ በግጭት ላይ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። ታጣቂ ቡድኑ ስድስት ሰዎችን ገድሏል፣ አንድ ሰው አቁስሏል፣ ቤቶችን አቃጥሏል፣ እንዲሁም ከ12 በላይ ከብቶችን ሰርቋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 16, 2013; ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 17, 2013)። የጉሙዝ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ተቀማጭነቱን ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያደረገ ሲሆን በክልሉ ውስጥ የሚሰነዘሩትን አብዛኞቹን ጥቃቶች እንደሚፈፅም ይታመናል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመንግስት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል የሚደረገው ውጊያ ባለፈው ሳምንትም ቀጥሏል። ግንቦት 14, 2013 የኦነግ-ሸኔ አባላት ለስራ ወደ ቦሬ ቀበሌ የሚጏዙ የገላን ወረዳ ሰላም እና ደህንነት ሀይሎች ላይ አድፍጠው ጥቃት አድርሰዋል። ጥቃቱ የተከሰተው በገላን ወረዳ ጨልቤሳ ሾሮ አካባቢ ነው። በዚህ ጥቃት ምክንያት የገላን ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊ፣ የጽ/ቤቱ ባለሙያ፣ እና አምስት የፀጥታ ሃይሎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል። ስድስት የኦነግ-ሸኔ አባላት ከጥቃቱ በኋላ ከአከባቢው ሲያፈገፍጉ በኦሮሚያ የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 16, 2013)። ይህ አካባቢ የኦነግ-ሸኔ አባላት እንደሆኑ በሚታመኑ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚደርስበት የአማሮ ልዩ ወረዳ ጋር ያዋሰናል (በአማሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ በቅርቡ ስለደረሱ ጥቃቶች ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 29, 2013ን ይመልከቱ)።
ኦነግ-ሸኔ ግንቦት 7, 2013 ላይ ከምዕራብ ወለጋ ዞን (ኦሮሚያ ክልል) መንዲ ተወስደው የታፈኑ ሶስት የቻይና ዜጎችን መልቀቁን ግንቦት 11, 2013 ላይ አስታውቋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 21, 2013); ቢቢሲ አማርኛ፣ ግንቦት 23, 2013)። የቻይና ዜጋ የሆኑት ግለሰቦች መንዲ አካባቢ ውስጥ በሚገኝ የማዕድን ማውጫ ድርጅት ውስጥ ይሠሩ ነበር። የኦነግ-ሸኔ (የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተብሎም ይጠራል) ቃል-አቀባይ እንዳሉት “በአካባቢው የሚሰሩ የማዕድን አውጭ ድርጅቶች በቂ ካሳ ያልተከፈላቸው በርካታ አርሶአደሮች ለመፈናቀላቸው ተጠያቂ ናቸው” (ኦዳ ታርቢ፣ ግንቦት 7, 2013; አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 7, 2013)። በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት ህጋዊ እንዳልሆነ እና ከዚህ መንግስት ጋር ከመስከረም 30, 2013 በኻላ የተደረገ ማንኛውም ስምምነት ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል (ኦዳ ታረቢ፣ ግንቦት 7, 2013; አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 7, 2013)።
በአማራ ክልል የፖለቲካ አለመረጋጋት በሰሜን ጎንደር ዞን ተመዝግቧል። ግንቦት 15 እና 17, 2013 ላይ የሱዳን ታጣቂዎች በመተማ ወረዳ ቱመት መንዶቃ ቀበሌ የኢንቨስተሮች መኖሪያ ላይ ጥቃት አድርሰዋል። የሶስት ባለሀብቶች ንብረቶችን ያወደሙት ሚሊሻዎች ከብት፣ ዶሮ፣ በግ፣ ጥጥ፣ እና ምግብ ሰርቀዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 17, 2013; ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 19, 2013)። የመተማ ወረዳ በጥጥ ምርት እና በሌሎች ለሽያጭ በሚቀርቡ ሰብሎች ይታወቃል። ለዲደብሊው (ግንቦት 19, 20131) ቃላቸውን በሰጡ ምስክር መሰረት የሱዳን ታጣቂዎች በጉሙዝ ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ፣ በህዝበ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)፣ ቅማንት ብሄር ታጣቂ ቡድን፣ እና ሳምሪ ወጣቶች ታጣቂ አባላት ይደገፋሉ። የሳምሪ ወጣቶች ታጣቂ ከትግሬ ወጣቶች የተወጣጣ ሲሆን ጥቅምት 30, 2013 ላይ በትግራይ ክልል ማይካድራ ውስጥ ከ600 በላይ አማራዎች ግድያ ላይ መሳተፋቸው ይታመናል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ህዳር 15, 2013)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቁስቋም፣ በላጂግላ ዳብረቃ እና አዘዞ ሰይድ አካባቢዎች ላይ ባልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች የደረሰውን ጥቃት የአማራ የፀጥታ ኃይሎች በተሳካ ሁኔታ መመከታቸውን የጎንደር አስተዳደር እና የጎንደር አማራ ወጣቶች ማህበር አስታውቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 20, 2013)። የተኩስ ልውውጥ ግንቦት 18 እና 19, 2013 ላይ ነበር። የሟቾች እና ጉዳት የደረሰባቸው ቁጥር አልታወቀም (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 20, 2013)። እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር አዲሱ አመት ከገባ በኻላ ጎንደር ከቅማንት ጋር ግንኙበት ባላቸው ቡድኖች የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መናህሪያ ሆናለች (ለዝርዝሩ የኢፒኦን የቅማንት ግጭት ገፅ ይመልከቱ)። የአማራ ክልል ባለስልጣናት የህዝበ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)ን ለቅማንት ብሄርተኛ ንቅናቄ ‘መሳሪያ እና ገንዘብ’ በማቅረብ ድጋፍ ይሰጣል ሲሉ ይከሳሉ (ቢቢሲ፣ ግንቦት 11, 2013)።
ሳምንታዊ ትኩረት: ግጭት በቤንች ሸኮ ዞን
በደህንነት ኃይሎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በማውገዝ በሸኮ ወረዳ (ቤንች ሸኮ ዞን) መሃል ሸኮ የተቃውሞ ሰልፎች ባለፈው ሳምንት ግንቦት 17, 2013 ቀን ላይ ተካሂደዋል (የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ ግንቦት 17, 2013)። የተቃውሞ ሰልፉ የተካሄደው ግንቦት 10, 2013 ላይ ያልታወቁ ታጣቂዎች በቤንች ሸኮ ዞን በሸኮ ወረዳ ውስጥ ዘጠኝ ሰላም ሰላም አስከባሪዎችን ገድለው ሶስት ደግሞ ካቆሰሉ በኋላ ነው፡፡ ይህ ክስተት አንድ ብቻ አጋጣሚ አልነበረም። ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ግንቦት 20, 2013 አክሌድ በቤንች ሸኮ ዞን 7 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን እና 93 የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን መዝግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ባለፈው ሳምንት የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች እና አስተዳደር የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት እና የፌዴራል መንግስት ዞኑን ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን እንዲረዳ ጠይቀዋል። የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር በአስተዳደር ዞኑ ውስጥ በቅርቡ የተከሰተውን ግጭት መቆጣጠር እንዳልቻለ አምኗል (የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ ግንቦት 16, 2013; South Bench የደቡብ ቤንች ወረዳ ኮምንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ ግንቦት 18, 2013)። እንደአስተዳደሩ መረጃ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በግጭት ምክንያት 151 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች እና 28 የፀጥታ ኃይሎች ሲሞቱ 29 የፀጥታ ኃይሎች ቆስለዋል። በተጨማሪም በቤንች ሸኮ ዞን ውስጥ 21,938 የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ (የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ ግንቦት 16, 2013)።
ቤንች ሸኮ (ወይም ቤንች ማጂ) ዞን ውስጥ ከመጀመሪያውም በክልሉ ውስጥ ነበሩ ተብለው የሚታሰቡ እንዲሁም ‘ሰፋሪዎች’ ተብለው የሚታሰቡ ሌሎች ብሄረሰቦች ይኖራሉ። ‘ሰፋሪዎቹ’ በ1970ዎቹ መጨረሻ እና ከ2007 እስከ 2008 ባለው ጊዜ ውስጥ በነበሩ የሰፈራ መርሃ ግብሮች ወደ ቤንች ሸኮ ዞን የመጡ ናቸው። በተጨማሪም ኑሮን ለማሸነፍ በንግድ እርሻዎች እና በእደ-ጥበብ የወርቅ ማዕድናት ላይ ለመስራት ወደ ክልሉ የሚጓዙ ስደተኞችም አሉ። በእነዚህ ከመጀመሪያውም በክልሉ ውስጥ ነበሩ እና ‘ሰፋሪዎች’ ተብለው በሚታሰቡ ብሄረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ለግብአት በሚደረግ ውድድር እና የድንበር ግጭቶች ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው (ለዝርዝሩ የኢፒኦን ቤንች ሸኮ (ቤንች ማጂ) ዞን ግጭት ገፅ ይመልከቱ)። ሰኔ 2013 ላይ በቤንች ሸኮ ዞን ህዝበ-ውሳኔ ይደረጋል። ህዝበ-ውሳኔው አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ (ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፣ እና ኮንታ ልዩ ወረዳ) ደቡብ ምዕራብ ክልል የሚባል የኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ይመስርቱ ወይ የሚለውን ይወስናል። ይህ በህዝበ-ውሳኔው ካልተመረጠ አካባቢው በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አስተዳደር ስር ይቀጥላል።
ለሚዛን አማን አየር ማረፊያ የተፈቀደው ቦታ መቀየሩን ተከትሎ የቤንጭ ሸኮ ዞን ነዋሪዎች በፌዴራል መንግስት ላይ ብስጭታቸውን ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እና የአከባቢው የመንግስት ባለስልጣናት ይህንን ውሳኔ በመቃወም ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን ይህ ውሳኔ ሌላ ግጭት ሊያቀጣጥል እንደሚችል ጠቁመዋል። አስተዳደሩ ይህ ውሳኔ “ህዝባችንን አሳንሶ ማየት” መሆኑን በአጽንኦት በመግለጽ ኃላፊነት የሚወስደው ተቋም ይቅርታ እንዲጠይቅ ጠይቋል (ቤንች ሸኮ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፣ ግንቦት 24 ቀን 2021) (የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ ግንቦት 16, 2013)።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ግብረሰናይ ድርጅቶች በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እርዳታ ለማድረስ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዳሉባቸው አስታውቋል። ይህም የሆነው አሁንም በቀጠለው ግጭት ምክንያት ነው (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ግንቦት 19, 2013)። በተጨማሪም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች ግንቦት 16, 2013 ላይ በትግራይ ክልል ሰሜን-ምዕራብ ዞን ሽሬ ከተማ ፀሃይ እና አዲ ወንፊቶ ውስጥ ከሚገኙት ተፈናቃዮች ካረፉባቸው ካምፖች ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎችን አስረዋል። እስረኞቹ ግንቦት 19, 2013 ላይ ተለቀዋል (የኢትዮጵያ ሰባዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ግንቦት 19, 2013; ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 18, 2013; ግንቦት 20, 2013)። በእነዚህ ሶስት ቀናት ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች መደብደባቸውን ሁለት ታሳሪዎች ገልልዋል። በሶስት ቀናት የእስር ቆይታቸው እስረኞቹ የህወሃት ታጣቂዎችን እንዲለዩ ተጠይቀዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 20, 2013)።
ግንቦት 18 2013 ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ህወሃት 22 የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላትን መግደሉን ገልጿል። በተጨማሪም ህወሃት ሌሎች አራት አባላትንም አቁስሎ 20 የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ደግሞ አፍኖ ወስዷል (የኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ፣ ግንቦት 18, 2013)። በተጨማሪም የትግራይ ሃይማኖት ተቋማት ም/ቤት 326 የሃይማኖት መሪዎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ኃይሎች መገደላቸውን ዘግቧል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 21, 2013)። የትግራይ ሃይማኖት ተቋማት ም/ቤት ሰባት የሃይማኖት ተቋማትን ያቀፈ ነው።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች ወቅታዊ ሁኔታ
ጠቅላላ ምርጫው ሶስት ሳምንት እየቀሩት የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች በተለያዩ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔዎችን እየሰጡ ይገኛሉ። ግንቦት 19, 2013 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎትን ሶስት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አባላት (ባልደራስ) ለእጩነት እንዲመዘገቡ የሰጠው ውሳኔ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የአሰራር ዝርዝሮች እንዲሰጡት ጠይቋል(የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 19, 2013)። በምዝገባ ወቅት የባልደራስ ፓርቲ እነዚህን ሶስት አባላት በምዝገባ ወቅት በእጩነት ለማስመዝገብ ሲሞክር ለፍርድ ቤት ክርክር በቁጥጥር ስር ውለው እየጠበቁ ስለሆነ ምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ ፈቃደኛ አልሆነም። ከሰሞኑ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ምርጫ ቦርድ በሕጋዊና አስተዳደራዊ ውስንነቶች ምክንያት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ገልጿል። የምርጫ ወረቀቶች ታትመው ለመሰራጨት ዝግጁ መሆናቸው የመጨረሻውን ደቂቃ ለውጦች ያወሳስበዋል።
የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር ለምርጫውን መመዝገብ ካልቻሉ ሶስት አባላት አንዱ ናቸው። ግለሰቡ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውስጥ ገዥው የብልጽግና ፓርቲን የሚገዳደሩ ትልቅ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ናቸው። አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎች ያላቸው በመሆኑ በመጪው ምርጫ በእጩነት ከተካተቱ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ይታመናል። መሳተፍ ከተከለከሉ የባልደራስ ፓርቲ ደጋፊዎች የሚሰጡት ምላሽ የምርጫ ብጥብጥን ሊያስነሳ ይችላል።
በተመሳሳይ ግንቦት 20, 2013 ላይ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩት የሐረሪ ተወላጆች ለሐረሪ ክልል ም/ቤት ድምፃቸውን መስጠት እንዲችሉ የሰጠውን ውሳኔ አፅድቋል (በዚህ የምርጫ ክርክር ላይ ተጨማሪ ዝርዝር ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ፡- ከመጋቢት 25, 2013 እስከ ሚያዚያ 1, 2013 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013) ይመልከቱ። ምርጫ ቦርድ ይህንን ውሳኔ በምርጫ ቀን እንዴት እንደሚተገብረው ግልፅ አይደለም ፡፡