ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 2, 2013) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,630
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 8,373
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,488
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። በተለይም በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ጥቃት በተመለከተ ዘገባዎች ቀስ ብለው በሚቀጥሉት ሳምንታት ሊወጡ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 4
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
መንግስት ያሳለፈውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እና የክልሉ መዲና መቀሌ በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መውደቅ ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ከፍተኛ ውጊያ ባለፈው ሳምንት ረግቧል። ሆኖም ግን የተኩስ አቁም ውሳኔው ተከብሮ ይቆያል ተብሎ አይገመትም። የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔው እንደተላለፈ ትህነግ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ፣ እና የአማራ ክልል ኃይሎችን ለማሳደድ ቃል ገብቷል (ሮይተርስ፣ ሰኔ 23, 2013)፡፡ በዚህ መሰረት የትህነግ ሃይሎች እንደገና እየተደራጁ እና የትግራይ ያልሆኑትን ሃይሎች ከክልሉ ለማስወጣት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። በርካታ ምንጮች ትህነግ መቀሌን እና ሌሎች የክልሉን ዋና ዋና ከተሞች ከተቆጣጠረ በኋላ በፌደራል መንግስት ለተቋቋመው ጊዜያዊ የትግራይ መንግስት ድጋፍ ያደረጉ የመንግስት ደጋፊ ባለስልጣናት እና በግጭት ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦችን ኢላማ እንዳደረገ እና እንደገደለ ዘግበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ 26, 2013 ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ሃይሎች በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ዞን ሆሮ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ገበርጉም ቀበሌ ውስጥ አራት አማራዎችን ሲገድሉ ሶስት ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል (ኢሳት፣ ሰኔ 27, 2013)። በአካባቢው የብሔር ውጥረት ከፍተኛ ሲሆን የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው የሚኖሩ ከአናሳ ብሔር የሆኑ እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በመደበኛነት በመግደል ይወቀሳሉ። ኦነግ-ሸኔ ይህንን ወቀሳ የሚቃወም ሲሆን ይልቁንም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂዎችን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ላልሆኑ ግለሰቦች ሞት ተጠያቂ ያደርጋል (የኢፒኦን ምዕራብ እና ቄለም ወለጋ ግጭት ገፅ ይመልከቱ)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን ባለፈው ሳምንት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ውስጥ በርካታ የልማት ንብረቶችን አውድሟል (ኢሳት፣ ሐምሌ 2, 2013)፡፡ በጉራፈርዳ ወረዳ ዋናው የግጭት ምንጭ የመሬት ጉዳይ ነው (የኢፒኦን ቤንች ሸኮ (ቤንች ማጂ) ዞን ግጭት ገፅ ይመልከቱ)። ጷጉሜ 1, 2013 ላይ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ውስጥ ማለትም ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ 11ኛውን የኢትዮጵያ ክልል ይመስርቱ ወይ በሚለው ላይ ላይ ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል።
መንግስት በአጣዬ እና አከባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት ባለፈው ሳምንት ቀጥሏል። ሰኔ 27, 2013 ላይ በሸዋ-ሮቢት ከተማ ባህላዊ የእርቅ ስብሰባ ተካሂዷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 27, 2013)። በአጣዬ እና ዙሪያው ባሉ መንደሮች ያለው የደህንነት ጉዳይ በአሁኑ ወቅት የሚመራው በፌደራል ኮማንድ ፖስት ነው። ኮማንድ ፖስቱ የኦሮሞ ታጣቂዎች እና ከኦነግ-ሸኔ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እና የፌደራል ወታደሮች ጋር ከተጋጩ በኋላ ሚያዝያ 10, 2013 ላይ የተቋቋመው ነው። የኦነግ-ሸኔ ቃል አቀባዮች ቡድኑ በአማራ ክልል መንቀሳቀሱን አስተባብለዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት -በትግራይ ክልል የሁለትዮሽ ተኩስ አቁም ለማድረግ የፖለቲካ ሁኔታዎችን መረዳት
የፌዴራል መንግሥት የአንድ ወገን ተኩስ አቁም ካወጀ ከአንድ ሳምንት በኋላ ትህነግ በትግራይ ክልል ውስጥ ሁለቱም ወገን የተኩስ አቁም ለማድረግ 7 ቅድመ-ሁኔታዎችን አስቀምጧል (ጌታቸው ረዳ ፣ ሰኔ 27, 2013)። የትህነግ ቅድመ-ሁኔታዎች የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ሃይሎች ከትግራይ ክልል መነሳታቸውን ያጠቃልላል። ትህነግ እንደስልክ፣ መብራት፣ ባንክ፣ ትራንስፖርት፣ እንዲሁም ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦትን የመሳሰሉ የመንግስት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲሰጠው ጠይቋል። በተጨማሪም ቡድኑ ዓለምአቀፍ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ፣ እስረኞች እንዲፈቱ፣ እና የወደፊት ድርድሮች በሚል ባለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መሠረት እንዲሆን ጠይቋል። በተጨማሪም የፌዴራሉ መንግስት በህገ-መንግስቱ መሰረት ብሄራዊ ምርጫዎችን በወቅቱ ማከናወን ያለመቻሉን የገለፀው ትህነግ የፌዴራል መንግስቱ ከጥቅምት 2013 በኻላ ያፀደቃቸው ሁሉም ህጎች ተቀባይነት የላቸውም ብሏል (ጌታቸው ረዳ፣ ሰኔ 27, 2013)። ያስቀመጡት ቅድመ-ሁኔታዎች ካልተሟሉ ታጣቂዎቻቸው መዋጋት እንደሚቀጥሉ እና የትግራይ ያልሆኑ ሀይሎችን ከክልሉ እንደሚያወጡ የትህነግ ተወካዮች አመላክተዋል (ሮይተርስ፣ ሰኔ 29, 2013፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2013)። እነዚህን ለሁለትዮሽ ተኩስ አቁም የተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሐምሌ 2, 2013 ላይ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት እነዚህን ሁኔታዎች “በፍፁም የማይቻሉ” ሲሉ ጠርቷቸዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 2, 2013)።
የፌደራል መንግስት እና ትህነግ ግጭቱ “የፖለቲካ መፍትሄ” እንደሚያስፈልገው የተቀበሉ ሲሆን ይህም ግጭቱ በጦርነት ብቻ ሊፈታ እንደማይችል ሁለቱም እንደተገነዘቡ ያሳያል (ሮይተርስ፣ ሰኔ 29, 2013; ኢቢሲ፣ ሰኔ 28, 2013)። ይህ ግንዛቤ ሁለቱም ቡድኖች ግጭቱን በድርድር ለመፍታት እንዲችሉ በሮችን ሊከፍት ይችላል የሚል ተስፋ እንዲፈጠር አድርጏል።
ሆኖም ግን ወደ ጦርነት እንዲገቡ ያደረጏቸው ምክንያቶች ስር የሰደዱ ስለሆኑ ማንኛውም አይነት የፖለቲካ መፍትሔ ውስብስብ ይሆናል። ለምሳሌ በመንግሥትና በትህነግ መካከል በሚደረጉ ድርድሮች ለመፍታት በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከሚገኘው የምዕራብ ትግራይ ዞን ጋር ይገናኛል። ግጭቱ በጀመረ ሰሞን የአማራ ልዩ ሃይል እና ታጣቂዎች የምዕራብ ትግራይን አካባቢዎች የተቆጣጠሩ ሲሆን የአማራ ክልል ቃል አቀባይ ‘’…በሀይል የተወሰደ አሁን በሃይል ተመልሷል’’ ሲሉ ገልፀዋል (ብሉምበርግ፣ መጋቢት 7, 2013; በተጨማሪም አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 1, 2013 ይመልከቱ)። አካባቢው ከ1983 ጀምሮ በትግራይ ክልል አስተዳደር ስር ነበር።
የምዕራባዊ ትግራይ ዞን ላለፉት 30 ዓመታት ያከራክር የነበረ ሲሆን በአስተዳደሩ ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች የአማራ ብሔርተኝነት እንዲነሳሳ ትልቅ ቦታ ነበረው። በምዕራብ ትግራይ በሚገኙት የወልቃይት ጠገዴ እና ሰቲት ሁመራ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች እና እስራቶችን ተከትሎ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት አካባቢው በአማራ ክልል ስር እንዲተዳደር ጥሪ አቅርበዋል (ፎሪን ፖሊሲ፣ ሚያዚያ 20, 2013፣ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 1, 2013)። የኮሚቴ አባላቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገው ጥረት በ2008፣ 2009፣ እና 2010 ተከታታይ ሰልፎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል። በኦሮሚያ ክልል በ2008 ከጀመረው የቄሮ እንቅስቃሴ ጋር በመጣመር በትህነግ የበላይነት ስር የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር መጋቢት 2010 ላይ አብይ አህመድን እንደጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሾም አስገድደውታል።
በቅርቡ የተከሰቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሞት ያስከተሉ ኩነቶች ለግጭቱ የሚሰጡ የፖለቲካ መፍትሄ ይበልጥ ያወሳስባል። በግጭቱ መጀመሪያ አካባቢ ምዕራብ ትግራይ በሚገኝ ማይካድራ በተባለ ስፍራ ከ600 በላይ አማራዎች ሳምሪ በተባለ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ተገድለዋል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ህዳር 15, 2013፤ ሮይተርስ፣ ግንቦት 30, 2013)። በቅርቡ የወጣ የሮይተርስ ምርመራ በማይካድራ ከትግራይ እና አማራ ብሔሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን መግደላቸውን ገልጿል (ሮይተርስ፣ ግንቦት 30, 2013)። የአማራ ክልል ኃይሎች የምዕራብ ትግራይ ዞንን ከተቆጣጠሩ በኋላ አሜሪካ የዘር ማፅዳት ስትል የጠራችውን የትግራይ ተወላጆችን ከቦታው በግዴታ የመግፋት ድርጊት አካሂደዋል ተብለው ተከሰዋል (ኤፒ፣ መጋቢት 29, 2013)።
በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ትግራይ ዞን የሚገኙ አማሮች በትክክለኛው ቦታቸው እንደሚኖሩ ይናገራሉ ያሳያሉ (ብሉምበርግ፣ መጋቢት 7, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 1, 2013)። የአማራ ኃይሎች ከምዕራብ ትግራይ ዞን በሰላም አይወጡም እንዲሁም ከክልሉ መነሳታቸውን ሊያካትት በሚችል ድርድር ፍላጎት የላቸውም። የፌደራል ኃይሎች ከትግራይ ክልል ከወጡ ወዲህ የአማራ ክልል መንግስት ትህነግ አከራካሪ የሆኑ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ማንኛቸውንም ቦታዎች ለመቆጣጠር ከሞከረ ቡድኑን ለመውጋት ያለውን ዝግጁነት የሚገልፁ በርካታ መግለጫዎችን አውጥቷል። ትህነግ በትግራይ ግጭት ላይ ለነበራቸው ተሳትፎ አማራዎች ላይ ‘’የበቀል’’ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ አሳውቋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 3, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 2, 2013; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 27, 2013፤ ቪኦኤ አማርኛ፤ ሰኔ 22, 2013)፡፡ ባለፈው ሳምንት የትህነግ ታጣቂዎች ወደ ክልሉ ምዕራባዊ ቦታዎች እያቀኑ መሆኑን የሚያሳዩ ዘገባዎች የነበሩ ሲሆን ይህም ግጭቶችን ድጋሚ ለመጀመር እየተዘጋጁ እንደሆኑ ያመለክታሉ (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 29, 2013፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 29, 2013)።
በሚቀጥሉት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ ሌሎች አዝማሚያዎች አሉ፡፡ የትህነግ ሀይሎች በጦርነቱ የመጀመሪያ ወራት ትህነግ ከስልጣን ሲወገድ የፌደራል መንግስቱ የሾመውን የሽግግር መንግስት ረድተዋል የተባሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች እና የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ባለስልጣናትን ገድለዋል ተብለው ተከሰዋል (ኢቢሲ፣ ሰኔ 30, 2013)። የራያ ራዩማ ፓርቲ ተወካይ የፌደራል ወታደሮች ከአካባቢው መውጣታቸውን ተከትሎ ትህነግ ራያ አዘቦን በያዘበት ወቅት 50 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድሏል (ኢቢሲ፣ ሰኔ 30, 2013)። ያልታወቀ ቁጥር ያላቸው የአካባቢው ወጣቶች የትህነግ አጋር በሆኑ ሚሊሻዎች ከተወሰዱ በኋላ የደረሱበት አልታወቀም (ኢቢሲ፣ ሰኔ 30, 2013)። በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቢሮ እንዳስታወቀው በምዕራባዊቷ ሽሬ ከተማ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ከትህነግ ጋር ግንኙነት ባላቸው ኃይሎች ተገድለዋል ተብሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2013)። የትግራይ ግጭት ጥቅምት 2013 ላይ ከመጀመሩ በፊት በክልሉ ውስጥ ወደ 100,000 የሚጠጉ የኤርትራ ስደተኞች ነበሩ (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2013)።
በኤርትራ ድንበር ላይ የሚገኙ የሚያከራክሩ ግዛቶች ችግር ይፈጥራሉ። ከአጎራባች ኤርትራ የመጡ ወታደሮች አከራካሪ ከሆነው የድንበር ከተማ ባድሜ በስተቀር ከትግራይ ክልል ለቀው ወጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ባድሜን ለኤርትራ የወሰነውን የ1994 ኢትዮ–ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ለመቀበል እና ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነው ሰኔ 2010 ላይ ነበር (ዘ ዋሺንግተን ፖስት፣ ግንቦት 28, 2010)። የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ግጭቱ በፊት ወደነበረው ድንበራቸው እንዲመለሱ ትህነግ ያቀረበው ጥሪ ይህንን የፌደራል መንግስት የድንበር ኮሚሽንን ውጤት ለማክበር ያሳለፈውን ውሳኔ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር የሚደረገውን ድርድር የሚያወሳስብ ነው። ይህም ሆኖ ባለፈው ሳምንት የተፈጠሩ አዎንታዊ የሆኑ ሁኔታዎች አሉ። የፌደራል መንግስቱ ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦትን ለማፋጠን የሰብአዊ ድርጅቶች በአዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ዕርዳታ እንዲያደርጉ ፈቃድ ሰጥቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 2, 2013)። በተመሳሳይ የተራእዶ ድርጅቶች የመሬት መጏጏዣ በደህንነት ፍተሻዎች እያለፉ እንዲጠቀሙ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 4, 2013; ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 2, 2013)። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ‘‘በአብዛኛ የትግራይ ክፍል የእርዳታ ስራ ተደራሽነት ተሻሽሏል’’ ሲል የዘገበ ሲሆን ይህም የትህነግ ሃላፊዎች አለምአቀፍ ድርጅቶችን እየተባበሩ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል’’ (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሐምሌ 2, 2013)።
የመንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ለሁለቱም ወገኖች የግጭትን የወደፊት እንድምታዎች እንዲገመግሙ በጣም አስፈላጊ ጊዜን ስለሚሰጥ አሁን ያለው ሁኔታ በድርድር የፖለቲካ መፍትሄ የሚደረስበት እና ግጭቱ እስከወዲያኛው የሚቆምበት ይሆናል የሚል ተስፋ አለ፡፡ ሆኖም ከትህነግ አካባቢን መቆጣጠር እና ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያለው ግንኙነት ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች ነገሮች ያወሳስባሉ። እርስ በእርስ የሚጋጩ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ:- ትህነግ ለሁለትዮሽ የተኩስ አቁም እንደቅድመ-ሁኔታ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች ውስጥ አጥብቆ ድርድር አሁን ባለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መጠየቅና የፌደራል ኃይሎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ መጠየቅ በቀጥታ ይቃረናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህገመንግስት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደአየር መጏጏዣ፣ ሁለት እና ከዚያ በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶችን፣ እና የስልክ አገልግሎቶችን የመሳሰሉ የተለያዩ ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ ነገሮችን የፌደራል መንግስት እንዲያስተዳድር ያዛል (የኢትዮጰያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት፣ 1987፣ አንቀፅ 51)። ስለሆነም የፌዴራል መንግስት ትህነግ በጠየቀው መሰረት ህገ-መንግስቱን አክብሮ ወደ ትግራይ ክልል አለመግባት ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው።
መሻሻል እንዲኖር የክልሉ ህዝብ ቅድሚያ ሊሰጠው እና ግጭት ሊቆም ይገባል። በምዕራብ ትግራይ ለሚገኙ አከራካሪ ቦታዎች የአሁን እና የድሮ ነዋሪዎችን መብቶች ያገናዘበ መፍትሄ ሊገኝ ይገባል። ሆኖም በምዕራብ ትግራይ ዞን ውስጥ በሁሉም ቡድኖች በኩል የሚደረገውን ወታደራዊ መጠናከር ከግምት በማስገባት ይህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚሆን አይመስልም።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች ወቅታዊ ሁኔታ
በጠቅላላ ከ46 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 31 እና ሰባት የግል እጩዎች ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርበዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ከ673 የምርጫ ክልሎች 165 ይመለከታሉ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሰኔ 28, 2013፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ዝርዝር ይመልከቱ)። ከ673 የምርጫ ክልሎች በ70 ውስጥ ምርጫዎች ጷጉሜ 1, 2013 ይካሄዳሉ።
ከቀረቡት ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ከ138 የምርጫ ክልሎች 49 በሚመለከት የተመዘገበበት አማራ ክልል ከፍተኛው ቁጥር ቀርቦበታል። ይህን ተከትሎም ከ104 የምርጫ ክልሎች 40 የሚመለከቱ ቅሬታዎች የቀረቡበት የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልልይከተላል። በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 23 የምርጫ ክልሎች ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ቀርበዋል። በተጨማሪም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ሁለት በኦሮሚያ፣ አንድ በድሬደዋ ከተማ፣ ስምንት በሲዳማ ክልል፣ ስድስት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል፣ ሦስት በጋምቤላ ክልል፣ እና 21 በአፋር ክልል በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ቀርበዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ድጋሚ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን ባለፈው ሳምንትም ቀጥለዋል፡፡ በአፋር ክልል የሚገኙ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች – የአፋር ህዝብ ፓርቲ ፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ፣ የአፋር ህዝብ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ፣ እና የአርጎባ ብሄረሰብ ዴሞክራሲ ንቅናቄ – ምርጫው እንደገና እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል (ቪኦኤ፣ ሰኔ 30, 2013)፡፡ በአፋር ክልል 21 የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ቀርበዋል።
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ነገሌ የምርጫ ክልል ከ139 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ለቀሩት 30 ምርጫ ሐምሌ 1, 2013 ተካሂዷል (ኢቢሲ፣ ሐምሌ 1, 2013)። ባለፈው ወር ድምጽ በሚሰጥበት ጊዜ ሁሉም የእጩ ተወዳዳሪዎች ስም በታተመው የድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ባለመኖሩ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ እንዲዘገይ ተደርጓል፤ ስሙ ያልተካተተው እጩ እራሱን ከምርጫው ስላገለለ ችግሩ እልባት አግኝቷል። በምርጫ አዘጋጆች መካከል የነበረው ያለመግባባት የድምፅ አሰጣጡ እንዲካሄድ እና በሌሎች እንዳይደረግ አድርጏል። በመጨረሻ የተቀሩት ሥፍራዎች ባለፈው ሳምንት ድምጽ ሰጥተዋል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሰኔ 28, 2013)።
ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ይፋዊ ውጤት ሐምሌ 3, 2013 አስታውቋል፡፡ ሰኔ 14, 2013 ላይ ከ547 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ለ465 ውድድር ተካሂዷል። ከእነዚህ 465 መቀመጫዎች ውስጥ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን አሸንፏል። በንፅፅር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አምስት ወንበሮችን ያገኘ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አራት መቀመጫዎችን አግኝቷል፡፡ የግል እጩዎች አራት መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን የጌዲዮ ህዝብ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሁለት ወንበሮችን አሸንፏል (ኢቢሲ፣ ሐምሌ 3, 2013; የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሐምሌ 5, 2013)። ለትግራይ ክልል ከተያዙ 38 መቀመጫዎች ውጭ ለተቀሩት 99 መቀመጫዎች ምርጫ ጷጉሜ 1, 2013 ይደረጋል።3ምርጫው ጷጉሜ 1, 2013 የሚካድባቸውን አካባቢዎች ለማየት ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሰኔ 5, 2013 እስከ ሰኔ 11,2013 ይመልከቱ።
በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡትን ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን ከመረመረ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች የተደረጉ ምርጫዎች በድጋሚ እንዲካሄዱ ወስኗል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ፣ ሐምሌ 5, 2013፤ ኢቢሲ፣ ሐምሌ 3, 2013)። ምርጫዎች በድጋሚ ሲካሄዱ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በድጋሚ የተካሄዱት በ1997 አጠቃላይ ምርጫ ወቅት ነበር። በአማራ ክልል አምስት የምርጫ ክልሎች እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ሶስት የምርጫ ክልሎች ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫዎች በድጋሚ ይካሄዳሉ። ለክልል ምክር ቤቶች ምርጫ በአፋር እና ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች በእያንዳንዳቸው በአንድ እና በአማራ ክልል በሚገኙ አምስት የምርጫ ክልሎች ድጋሚ ይካሄዳል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሐምሌ 5, 2013፤ ኢቢሲ፤ ሐምሌ 3, 2013)።
ከዚህም ባለፈ ምርጫ ቦርድ በ12 የምርጫ ክልሎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች የተሰጡ ድምችን እንደገና ለመቁጠር ወስኗል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሐምሌ 5, 2013; ኢቢሲ፣ ሐምሌ 3, 2013)። ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድጋሚ ቆጠራው በድሬደዋ ከተማ፣ በአማራ ክልል፣ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በእያንዳንዳቸው በአንድ የምርጫ ክልል ይካሄዳል፡፡ የክልል ምክር ቤቶች የድምፅ የድጋሚ ቆጠራው ደግሞ በአፋር ክልል በአምስት የምርጫ ክልሎች፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ሶስት የምርጫ ክልሎች፣ እና በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በአንድ የምርጫ ክልል ይካሄዳል።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡ ወገኖች ፍ/ቤቶች ላይ ይግባኝ ያቀርቡ እንደሆን በአሁኑ ወቅት ግልጽ አይደለም። ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት በሀይለኛ ተቃውሞን የማሰባሰብ ዕድላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃዎች፣ የእስር ስጋት፣ እና በቢሮ ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናትን ድጋፍን ከግምት በማስገባት አነስተኛ ነው።
የአክሌድ ኢፒኦ ቡድን ከድህረ ምርጫ ወቅት ጋር በተያያዘ ያዘጋጀውን ጥልቅ ትንተና ለማየት ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሰኔ 12, 2013 እስከ ሰኔ 18, 2013 እና ልዩ ዘገባችንን ይመልከቱ።