በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥቅምት 19, 2014)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,123
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,408
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,731
በቁጥር (ከጥቅምት 13, 2014 እስከ ጥቅምት 19, 2014)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 25
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 70
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 11
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ) እና የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ በስተደቡብ አቅጣጫ ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በተከታዩ ክፍል እንደተዘረዘረው ትህነግ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን ተከትሎ በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል (ፋና ብሮድካስቲንግ ፣ ጥቅምት 23, 2014)። ከዚህ ቀደም ብሎ ባለፈው ሳምንት በትህነግ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል፣ እንዲሁም የአማራ ታጣቂዎች መካከል በአማራ ክልል ኩታበር፣ ተሁለደሬ፣ ቦሩ ስላሴ፣ ደላንታ፣ እና ደሴ ከተማ የሚካሄዱ ውጊያዎች ቀጥለዋል። በተጨማሪም ውጊያዎች በአፋር ክልል ጭፍራ ተመዝግበዋል። የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ በደቡብ ወሎ ዞን ከትህነግ ሃይሎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ለመሳተፍ በርካታ ግለሰቦች የአማራ ታጣቂዎችን እየተቀላቀሉ ነው።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችን በአየር ማጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አራት የአየር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን ሁለት በመቀሌ እንዲሁም በማይጸምሪ እና አዳዋ በእያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ የአየር ጥቃት አድርሷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልልም በትህነግ ሃይሎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽሟል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥቅምት 16 እና 18 ላይ ትህነግ ደሴ ከተማን አራት ጊዜ በከባድ መሳሪያ ደብድቧል።
በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መዋጋት ቀጥለዋል። ጥቅምት 15 እና 16, 2014 ላይ የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በዶቢ ቀበሌ በሦስት የወታደር መኪኖችን እና በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ ዙሪያ የሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱ ተዘግቧል። ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች መካከል በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ጭናቅሰን ወረዳ ጪንሃህሳን ውስጥ መዋጋታቸው ተዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውሳጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ጥቅምት 16 እና 17, 2014 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ ጎልቦ ቢቲም ቀበሌ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል አራት ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል። ጥቅምት 17, 2014 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ልጃቸውን ኦነግ-ሸኔን እንዲቀላቀል ልከውታል ያሉትን ቤተሰብ ንብረት የሆነን ቤት ማቃጠላቸው ተዘግቧል። ጥቅምት 13, 2014 ላይ የነቀምቴ ከተማ ሥራ ፈጠራ ጽ/ቤት ኃላፊ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ማንነቱ ባልታወቀ የታጠቀ ግለሰብ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል። ከዚህ ቀደም ከኦነግ-ሸኔ ተገንጣይ በሆነው የአባ ቶርቤ ታጣቂዎች በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ገድለዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አራት ሰልፎች ተካሂደዋል። ከሰልፎቹ አንዱ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ቀሪዎቹ በኦሮሚያ ክልል ተካሂደዋል። ጥቅምት 15, 2014 ላይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ለታሰረ መሪያቸው ድጋፍ ለማሳየት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ጥቅምት 11, 2014 ላይ የፓርቲው መሪ በእስር ቤት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ጥቅምት 11, 2014)። በኋላ በእስር ቤት አብረዋቸው ከታሰሩ ግለሰብ ጋር መጋጨታቸው ተነግሯል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 13, 2014)። የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር ከመስከረም 2013 ጀምሮ በሽብር ክሶች በፍርድ ቤት ክርክር ላይ የሚገኙ ሲሆን ደጋፊዎቻቸው ክሶቹ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው ብለው ያምናሉ (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጷጉሜ 5, 2013)።
ጥቅምት 13, 2014 ላይ የጪንሃህሳን ከተማ ነዋሪዎች በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ጪናክሰን ወረዳ “በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሱ ህጋዊ ያልሆኑ ግድያዎችን” በማውገዝ የመንግስት ሃይሎችን የሚቃወም ሰልፍ አካሂደዋል (ኦኤምኤን፣ ጥቅምት 14, 2014)። የክልሉ ፖሊስ ሃይሎች 11 ሰልፈኞችን ሰልፉን አዘጋጅተዋል በሚል ክስ በቁጥጥር ስር አውሏል። ጥቅምት 18, 2014 ላይ የጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ እና ሊበን ወረዳ ነዋሪዎች መንግስት “በድርቅ ምክንያት በዜጎች እና እንስሳት ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ያቁም” እንዲሁም “በፀጥታ ሃይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰውን የዘፈቀደ ግድያ እና እስር” አውግዘው ሰልፍ አካሂደዋል (ኦኤምኤን፣ ጥቅምት 19, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አሌ ልዩ ወረዳ በከርከርቴ፣ ማደሪያና ግዛባ፣ እና ሄጄና ቀበሌዎች ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን በጥይት ገድሏል። በአሌ ልዩ ወረዳ አካባቢ ባለፉት ጥቂት አመታት ግጭቶች በየጊዜው ይቀሰቀሳሉ (የኢፒኦን ሰገን አካባቢ ህዝብ ዞን ግጭት ገጽን ይመልከቱ)።
ሳምንታዊ ትኩረት: ትህነግ ደሴ እና ኮምቦልቻን መቆጣጠሩን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ3በዚህ ክፍል ከተካተቱት ኩነቶች ውስጥ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የተፈጸሙት በአክሌድ የኩነቶች ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም። የአክሌድ የኩነቶች ዝርዝር እስከ ጥቅምት 19, 2014 ያለውን ያካትታሉ። ከጥቅምት 20, 2014 እስከ ጥቅምት 26, 2014 የተፈጸሙ ኩነቶች በቀጣዩ ሳምንት ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ።
በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ትህነግ ከኩታበር እና ተሁለደሬ ከተሞች በስተደቡብ ወደ ደሴ መግፋቱን ተከትሎ በአንድ በኩል በትህነግ እና በሌላ በኩል ደግሞ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች፣ እና የአማራ ታጣቂዎች የሚካሄደው ውጊያ ተባብሷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ጥቅምት 20, 2014 የትህነግ ሃይሎች ከወሎ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ባሉት አካባቢዎች ባለፈው ቀን ውጊያ ካደረጉ በኋላ የደሴ ከተማን መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 20, 2014)። የመንግስት ሃይሎች የመልሶ ማጥቃት ጀምረው ከጥቂት ሰአታት በኋላ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ተናገሩ (ኢፒኤ፣ ጥቅምት 20, 2014)።
በማግስቱ የትህነግ ሃይሎች ደሴ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር በማጠናከር በደቡብ ምስራቅ ኮምቦልቻ ከተማን ተቆጣጠሩ (ጌታቸው ረዳ፣ ጥቅምት 21, 2014)። የፌደራል መንግስቱ ጥቅምት 22, 2014 ላይ ባወጣው መግለጫ ትህነግ በኮምቦልቻ ከተማ ከ100 በላይ ወጣቶችን መግደሉን በመግለጽ ደሴ እና ኮምቦልቻ ማጣታቸውን በተዘዋዋሪ መንገድ አምነዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 22, 2014)። ትህነግ በኮምቦልቻ ሰው መግደሉን አስተባብሏል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 22, 2014)።
ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ማጣቱ ለፌዴራል መንግስቱ ትልቅ ጉዳት ነው። ደሴ ወደ ምስራቅ ወደ አፋር ክልል እና ወደ ደቡብ ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በሚያመሩ ዋና ዋና የትራንስፖርት መስመሮች መገናኛ መንታ መንገድ ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። ከከተማዋ በስተደቡብ በኩል ካለፈው አመት ጀምሮ በሁከትና ብጥብጥ የተጠቃው የአማራ ክልል ኦሮሞ ልዩ ዞን ይገኛል (የኢፒኦን የከሚሴ ግጭት ገጽ ይመልከቱ)። የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ-ሸኔ) ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ የቡድኑ የሰሜን እዝ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰንባቴ እና ከሚሴ ከተሞች መንቀሳቀሱን የተናገሩ ሲሆን ይህም ከትህነግ አጋሮቻቸው ጋር በአካል ለመገናኘት ቅርብ አድርጓቸዋል (ኦዳ ታርቢ፣ ጥቅምት 21, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥቅምት 22, 2014)።
በቅርብ ጊዜ በህወሃት የተደረጉ መግፋቶች በአማራ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ባለስልጣናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአማራ ክልል ባለስልጣናት የመንግስትን አገልግሎት በመግታት በጀት እና የሰው ሃይል ከትህነግ ጋር ለሚደረገው ውጊያ እንዲያውሉ አዟል። በተጨማሪም የመንግስት እና የግል መኪናዎች እና የጦር መሳሪያዎች በሙሉ ተደራጅተው የትህነግን እንቅስቃሴ ለመግታት ለሚሰሩ ሃይሎች ድጋፍ እንዲውል አዟል። ክልላዊ የሆነ የሰዓት እላፊ የተጣለ ሲሆን ይህም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ነው (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 21, 2014)። ጥቅምት 23, 2014 ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል (ኢፒኤ፣ ጥቅምት 23, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥቅምት 23, 2014)። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሳሪያ የያዙ ነዋሪዎች መሳሪያቸውን በአቅራቢያው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲያስመዘግቡ እንዲሁም ሰዎች በአስተዳደር ማእከላት በመሰባሰብ ሰፈሮችን ለመከላከል እንዲዘጋጁ አበረታቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለዚህ ደረጃ የደረሰባቸው እና የትህነግን ግስጋሴዎች መቋቋም ያልቻለባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቭዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር የፌደራል ባለስልጣናት በመንግስት ደጋፊ ታጣቂዎች የተደረገውን መሰባሰብ “በአግባቡ ለማስርተዳደር አለመቻላቸው” ሽንፈት እንዳስከተለ አምነዋል (ፋና ብሮድካስቲንግ፣ ጥቅምት 23, 2014)። በትግራይ ክልል የነበረው ዘመቻ ውድ በመሆኑ ምክንያት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል እንዲሁም የወታደርም ሆነ ትጥቅ እጥረት እንዳለበት ግልጽ ነው።
ከመላው አማራ ክልል የተውጣጡ ታጣቂዎች ስትራቴጂክ የሆነችውን ከተማ እንደገና ለመቆጣጠር ወደ ደሴ ግንባር እየተጓዙ ነው (ኢፒኤ፣ ጥቅምት 18, 2014)። ምንም እንኳን የትህነግ ሃይሎች ወደ ወሎ (ምስራቅ አማራ) ዘልቀው መግባት ቢችሉም የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ግን አሁንም ለክልሉ መንግስት ታማኝ በሆኑ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ናቸው። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር የሚተባበሩት የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች በጭፍራ (አፋር ክልል) ከትህነግ ጋር እየተዋጉ ሲሆን ትህነግ በአፋር ክልል ያሉ አካባቢዎችን በድጋሚ ለመያዝ ያደረጋቸውን ተጨማሪ ጥረቶች መመከት ችለዋል። በመጪዎቹ ሳምንታት ከመንግስት ጋር የሚተባበሩ ቡድኖች ተጨማሪ ግዛት ላለማጣት ሲሞክሩ ግጭት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።