ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
- አክሌድ ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 ድረስ 74 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 326 ሟቾችን መዝግቧል።
- ኦሮሚያ ክልል በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር,180 ሟቾች የተዘገበበት ክልል ነው። አማራ ክልል በ116 የተዘገቡ ሟቾች ቁጥር ይከተላል።
- ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 41 የዚህ አይነት ኩነቶች እና 189 ሟቾች ተዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) እና በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እንዲሁም በአፋር ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል።
- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እንዲሁም ከኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርገው ውጊያ እንደቀጠለ ነው።
- ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ቀጥሏል።
በዚህ ዘገባ ውስጥ
- ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት:- የትግራይ ግጭት የድርድር አጀንዳዎች ፖለቲካዊ ውስብስብነት
ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ወር በትህነግ/ህወሃት እና በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና በአፋር ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የቀጠለ ሲሆን ጦርነቱ በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በርሃሌ፣ ኮነባ፣ መጋሌ፣ ኢሬብቲ፣ እና አባላ አካባቢዎች ላይ እየተካሄደ ነበር። ከግጭቱ ጎን ለጎን በጦርነት ላይ ያሉት ቡድኖች ከርቀት የሚደረጎ ጥቃቶችን ተጠቅመዋል፤ ይህም ቢያንስ በአንድ ክስተት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ሞት አስከትሏል። የካቲት 2 ላይ የኢትዮጵያ ሰራዊት በትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ላይ ካደረገው የአየር ጥቃት በተጨማሪ የካቲት 9 ላይ ከበርሃሌ ከተማ 15 ኪ.ሜ. አካባቢ በሚርቅ ቦታ ላይ በተደረገ የከባድ መሳሪያ ድብደባ 10 የአንድ አፋር ቤተሰብ አባላት ሲገደሉ 13 ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል። ይህንን ጥቃት የቱ ቡድን እንደፈጸመ ግልጽ አይደለም። በተመሳሳይ እለት ትህነግ/ህወሃት በኤረብቲ ወረዳ የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአፋር ታጣቂዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈጽሟል።
የአፋር ክልል ባለስልጣናት ጦርነቱ በድጋሚ ባለፈው ወር ከተጀመረ ወዲህ 430,000 የሚደርሱ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ሲገምቱ፤ ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ መኖሪያ ቤታቸው በከባድ መሳሪያ በመደብደቡ ምክንያት የመኖሪያ ህንጻዎቻቸው የወደሙ ናቸው (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 2, 2014)። በቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 የሰፈሩ ኤርትራውያን ስደተኞችም በድጋሚ በተነሳው ግጭት ተጎድተዋል። ጥር 26 ላይ በትህነግ/ህወሃት እና የአፋር ሃይሎች መካከል ጦርነት በነበረበት ወቅት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በበርሃሌ የሚገኝ የኤርትራ ስደተኞች የሚገኙበትን መጠለያ ጣቢያ አጥቅተው ቢያንስ አምስት ስደተኞችን ገድለዋል (ሮይተርስ፣ የካቲት 11, 2014)። ይህ ጥቃት በትህነግ/ህወሃት ሃይሎች መፈጸሙን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። ቡድኑ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሴቶች ስደተኞችን አፍኗል፣ ጣቢያውንም ዘርፏል። በዚህ ጥቃት ወደ 34,000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ተፈናቅለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 11, 2014)። በዚህም ምክንያት መንግስት በሰርዶ አዲስ የስደተኞች ጣቢያ ገንብቶ ሁሉንም ኤርትራውያን ስደተኞች ከበርህሌ ወደ ሰርዶ የስደተኞች ካምፕ አስተላልፏል (አዲስ ማለዳ፣ የካቲት 29, 2014)።
በተጨማሪም አሁንም በትህነግ/ህወሃት ቁጥጥር ስር ከሚገኙት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ድንበር የሚገኘው የዋግ ኽምራ ዞን ዝቋላ፣ ፃግብጂ፣ እና አበርገሌ ወረዳዎች አንድ አንድ ቀበሌዎች ሰዎች መፈናቀላቸን ቀጥለዋል። እነዚህ ተፈናቃዮች በሰቆጣ ከተማ ተጠልለዋል። በተጨማሪም የሰቆጣ እና ቆቦ ከተሞች ከትግራይ ክልል አላማጣ፣ ኮረም፣ እና ዛታ የተፈናቀሉ ሰዎችንም እያስተናገዱ ነው። ለምሳሌ ሰቆጣ ከተማ ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ53,000 በላይ ተፈናቃዮችን እያስተናገደች ነው (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 6, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር መዋጋት ቀጥለዋል። አክሌድ በየካቲት ወር በምስራቅ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በሁለቱ ቡድኖች መካከል 24 የውጊያ ኩነቶችን መዝግቧል። ኦነግ-ሼኔ በምስራቅ ወለጋ ዞን ለካ ዱለቻ ወረዳ የባንዲራ ቀበሌን መቆጣጠሩን አሳውቋል (የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ የካቲት 19, 2014)። በነዚህ ግጭቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር በዘገባዎች አለመገኘት ምክንያት በውል አልታወቀም።
ባለፈው ወር በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካላት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። የአማራ ታጣቂዎች በምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ 13 ጥቃቶችን ፈጽመው በትንሹ 83 ሰዎችን ገድለዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ በድምሩ 52 ሰዎች የሞተባቸው ስምንቱ ጥቃቶች የተፈጸሙት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነው። ከዚህ ቀደም በዚህ አካባቢ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ አብዛኞቹ ጥቃቶች በኦነግ-ሸኔ የሚፈፀሙ ሲሆን አብዛኞቹ የጥቃት ሰለባዎች ደግሞ የአማራ ተወላጆች ነበሩ። የካቲት 9 ላይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሆሮ ቡሉክ ወረዳ ጉዲና አቡና ቀበሌ የአማራ ታጣቂዎች የኦነግ አመራሮች ዘመዶች ናቸው የተባሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ቤቶች ዘርፈው ስምንት ሰዎችን አፍነው ወስደዋል።
የካቲት 2 ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ዋረ ጃርሶ ወረዳ ሸንኮራ ሸሸንግ ቀበሌ ኦነግ-ሸኔ ከ18 ያላነሱ የአማራ ገበሬዎችን አፍኖ ወስዶ ለማስለቀቅ የተጠየቀውን ሂሳብ መክፈል ካልቻሉት ውስጥ ሰባቱን ገድሏል። በተመሳሳይ እለት ቡድኑ በዋረ ጃርሶ በኮቲቻ አካባቢ የሚያልፍ የትራንስፖርት መኪና ላይ ጥቃት በማድረስ አሽከርካሪውን ገድሏል። ጥቃቱ ከአካባቢው የፖሊስ ሃይሎች ጋር ውጊያ እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን ሌሊቱን ሙሉ ከታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። በተጨማሪም ጥር 30 ላይ በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የመከራ ዳገት (ኤርሻን አኖ) በተባለው አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሦስት የጭነት መኪናዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለው አራት ሌሎች ሰዎች አቁስለዋል። ታጣቂ ቡድኑ የጭነት መኪኖቹ እያጓጓዙት የነበሩትን ምርቶችንም ዘርፈዋል። በተጨማሪም በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ አዲስ አለም ቀበሌ የጉሙዝ ነፃነት ግንባር እና ከኦነግ-ሸኔ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ሰዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ቤቶች አቃጥለው ሶስት ሰዎችን ገድለዋል።
ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ድረስ ባለው ወቅት በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ የ87 ሰዎች አስከሬን የያዘ የጅምላ መቃብር ተገኝቷል። የመንግስት ባለስልጣናት ከአካባቢው በደርዘን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች አሁንም እንደጠፉ መሆኑን ጠቁመዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 30, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 3, 2014)። ይህ አካባቢ ለሁለት ወራት ያህል በኦነግ-ሸኔ ቁጥጥር ስር እንደነበረ ተነግሯል። አብዛኞቹ ተጎጂዎች በ1970ዎቹ በድርቅ ከተጎዱ የአማራ ክልል አካባቢዎች ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሰፈሩ የአማራ ተወላጆች እንደሆኑ ይታመናል። በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ እነዚህን ቦታዎች በተቆጣጠረበት ወቅት 105 የመንግስት ሰራተኞችን ከጊዳሚ እንዲሁም 63 የመንግስት ሰራተኞችን ከአጎራባች የኮንዳላ እና ቤጊ ወረዳዎች አፍኖ ወስዷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 7, 2014)። የቄለም ወለጋ ዞን ኃላፊ ከዲደብሊው አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ታፍነው የተወሰዱት ግለሰቦች በኦነግ-ሸኔ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ጠቁመዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 7, 2014)። የኦነግ-ሸኔ ቃል አቀባይ ይህንን ክስ ውድቅ አድርገዋል (ትዊተር@ኦዳተርቢደብሊውቢኦ፣ የካቲት 1, 2014)።
ባለፈው ወር በኦሮሚያ ክልል ኦነግ-ሸኔን በመቃወም ሁለት የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። የካቲት 9 ላይ በዋረ ጃርሶ ወረዳ ሸንኮራ ሸሸንግ ቀበሌ በአርሶ አደሮች ላይ የተፈጸመውን አፈና እና ግድያ የሚያወግዝ ሰልፍ በጎሃ ጽዮን ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ተካሂዷል። ሰልፈኞቹ በአማራ ክልል ጎሃ ጽዮንን ከባህርዳር ከተማ የሚያገናኘውን የአባይ በርሃ ዋና መንገድ ለሰአታት ዘግተዋል። ሁለተኛው የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደው የካቲት 11 ሲሆን የአቡነ ግንደበረት ከተማ ነዋሪዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን አዋራ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን በመቃወም ቡድኑ “ለኦሮሞ ህዝብ ትግል” በሚል ስም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን መግደል እና ንብረት ማውደም እንዲያቆም ጠይቀዋል (የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ የካቲት 11, 2014)።
በክልሉ በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸሙ ከህግ-ውጪ የሆኑ ግድያዎች ቀጥለዋል። ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ድረስ አክሌድ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የጸጥታ ሃይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የፈጸሟቸውን አራት ጥቃቶችን መዝግቧል። የካቲት 5 ላይ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀልዱ ወረዳ ሺኩቴ ከተማ የአካባቢውን ነዋሪዎች የኦነግ-ሸኔን አባላት መግባችኋል በማለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል። በዚህ ጥቃት የሁለት ህጻናት ህይወት ሲያልፍ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ሰው ቆስሏል። በተመሳሳይ እለት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በአዋራ አንድ እስረኛን ተኩሰው ገድለዋል። ሟቹ ከአንድ ቀን በፊት ኦነግ-ሸኔን ደግፋችኋል በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩ 20 ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። ከሁለት ቀናት በኋላም ጀልዱ ወረዳ ሽኩቴ ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት አንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪን በጥይት ገድለዋል። ግድያው የተፈፀመበት ምክንያት ግን አልታወቀም። በመጨረሻም የካቲት 12 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በኢሉ ገላን ወረዳ ቱሉ አሊዮ ቀበሌ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል 11 ሰዎችን በጥይት ገድለዋል።
በአማራ ክልል በደዋ ጨፋ በሚገኘው ዱዌ ሃራ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ስንቅሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ የኦነግ-ሸኔን ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ፈጽመው 100 ተዋጊዎችን ገድለዋል ተብሏል። የእነዚን ጣቢያዎች መውደም ተከትሎ ከ600 በላይ የኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች መታሰራቸውም ተዘግቧል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 30, 2014)። በታህሳስ 2014 ላይ ትህነግ/ህወሃት ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ከወጣ በኋላ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ መንግስት በወሰደው እርምጃ በደርዘን የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ተገድለዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ የካቲት 8, 2014)። ነሀሴ 2013 ላይ ኦነግ-ሸኔ የፌደራል መንግስትን ለመዋጋት ከትህነግ/ህወሃት ጋር ህብረት መፍጠሩን አስታውቆ ነበር (አልጀዚራ፣ ነሃሴ 5, 2013)።
ከዚህም በተጨማሪ ጥር 30 ላይ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ንፋስ መውጫ ወረዳ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ እና በአካባቢው የታጣቂዎች ጽ/ቤት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የጦር መሳሪያ ዘርፈው እስረኞችን ከማረሚያ ቤት አስመልጠዋል። ማንነታቸው ያልታወቁ 16 ታጣቂዎች ሲገደሉ ሌሎች 20 ደግሞ ተይዘዋል። ሶስት የመንግስት የጸጥታ ሃይል አባላትም ቆስለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 1, 2014)።
በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን በመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚደርሱ ድንበር ዘለል ጥቃቶች ቀጥለዋል። በየካቲት ወር አራት ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን ስድስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። የካቲት 2 ላይ ቡድኑ በአኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ኡኩቡ አካባቢ የሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ሁለት ሴቶች አቁስለው ሶስት ህጻናት አፍነው ወስደዋል። በማግስቱ በአኝዋክ ዞን ጎግ ወረዳ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ሰው ተኩሰው ገድለዋል። የካቲት 4 ላይ በጎግ ወረዳ ጃንጆር ቀበሌ የቡድኑ አባላት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን አጥቅተው ሶስት ሰዎች ገድለዋል። የካቲት 21 ላይ የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ሃይሎች ከአኝዋክ ዞን አቦቦ ወረዳ መንደር 11 እና 12 አካባቢዎች 220 የቀንድ ከብቶችን የዘረፉ የሙርሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በግጭቱ ሁለት ታጣቂዎች ተገድለዋል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት፣ የካቲት 22, 2014)። ሁለቱ ቡድኖች በጎግ ወረዳ ኡቡዋ መንደርም የተዋጉ ሲሆን አንድ የሙርሌ ብሄረሰብ ታጣቂ እና አንድ የክልሉ የጸጥታ ሃይል አባል ህይወት አልፏል። ሌላ የሙርሌ ብሄረሰብ ታጣቂ ቆስሏል። በተጨማሪም ባለፈው ወር ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ሲጓዝ የነበረ ከባድ መኪና አጥቅተው ሹፌሩን እና ረዳቱን ገድለው ነበር። ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር አዲሱ አመት ከተጀመረ ጀምሮ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የተሳተፉባቸው ኩነቶች ቁጥር ጨምሯል። ከታህሳስ 23 በፊት በነበረው አንድ አመት አክሌድ ቡድኑ የተሳተፈበት አንድ ውጊያ ብቻ የመዘገበ ሲሆን ከታህሳስ 23 እስከ የካቲት 21 ድረስ በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የተሳተፉባቸው አምስት ጥቃቶችን፣ ሁለት አፈናዎች፣ እና ሁለት ውጊያዎችን መዝግቧል።
በሶማሌ ክልል የካቲት 8 ላይ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች በፋፋን ዞን በአው ባሬ ፍተሻ ጣቢያ ጋር አልቆምም ያለ የተሳፋሪ ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ሁለት ተማሪዎች ተገድለዋል። ድርጊቱን ተከትሎ ሰልፈኞች በሚቃጠል ጎማ መንገዶችን በመዝጋት ለተጎጂዎች ፍትህ ጠይቀዋል። ባለፈው ወር የጸጥታ ሃይሎች በጅጅጋ በሆቴል ስብሰባ ለማድረግ የተሰበሰቡ ሰዎችን በመበተን በርካታ የቀድሞ የብልጽግና ፓርቲ አባላትን እና ሶስት ጋዜጠኞችን አስረዋል። የፓርቲው የቀድሞ አባላት እንዳሉት የተሰበሰቡት “በክልሉ ፖለቲካ ላይ ለመወያየት እና የክልሉ ህዝብ ላይ ለተጋረጡ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ” ነበር (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥር 30, 2014)። ከሶስቱ ጋዜጠኞች እና አንድ የቀድሞ የፓርቲው አባል በስተቀር ሌሎቹ ከታሰሩ ከአንድ ሰአት በኋላ ተለቀዋል።
ምንም እንኳን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ ቢሆንም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 8 ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በ63 አባላት ተቃውሞ እና 21 ድምፀ ተአቅቦ አንስቶታል (የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የካቲት 8, 2014)። ውሳኔውን የተቃወሙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአፋር እና በአማራ ክልሎች ትህነግ/ህወሃት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ኦነግ-ሸኔ እየተሳተፉበት ያሉትን ግጭቶች በመጠቆም አሁንም ከፍተኛ የጸጥታ ስጋቶች እንዳሉ ገልጸዋል (ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 8, 2014)።
ወርሃዊ ትኩረት፡ የትግራይ ግጭት የድርድር አጀንዳዎች ፖለቲካዊ ውስብስብነት
በሰሜን ኢትዮጵያ በትህነግ/ህወሃት እና ከመንግስት ጋር ግንኙነት ባላቸው ሃይሎች መካከል ያለው ጦርነት ከጀመረ አንድ አመት ተኩል ሆኖታል (የኢፒኦ የትግራይ ግጭት ገጽን ይመልከቱ)። እስከ ሰኔ 2013 ድረስ ውጊያው በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ይካሄድ ነበር። የፌዴራል ሃይሎች ከትግራይ ሰኔ 21, 2013 ላይ ከወጡ በኋላ ግጭቱ በስተደቡብ እና ምስራቅ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ጥቅምት 2014 መጨረሻ ላይ ትህነግ/ህወሃት በአማራ ክልል ያሉት እና ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በ257 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ነበር። ትህነግ/ህወሃት ወደ ደቡብ አቅጣጫ የተጓዘበት ፍጥነት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የመከላከያ ሰራዊቱን እና የክልል ልዩ ሃይል የማስፋፋት ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጎት ነበር። ህዳር 13, 2014 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ከግንባር ሆነው ለመምራት መወሰናቸውን አስታወቁ (ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ህዳር 13, 2014)። በታህሳስ መገባደጃ ላይ የመንግስት ሃይሎች በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ከሞላ ጎደል ሁሉንም አካባቢዎች መቆጣጠር ችለዋል።
ባለፈው ወር ሁለቱ ወገኖች ድርድር እንደጀመሩ የሚገልጹ ጭምጭምታዎች የነበሩ ሲሆን ይህም ትህነግ/ህወሃት ሙሉ በሙሉ ሲፈርስ ማየት በሚፈልጉ ወገኖች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። የትህነግ/ህወሃት መሪ የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “እኛ [ትህነግ/ህወሃት] ከፌዴራል መንግስት ሃይል ጋር መነጋገር ጀምረናል። የርቀት ግንኙነቶች እና ውይይቶች አሉ” ብለው ነበር (ቢቢሲ፣ ጥር 27, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 11, 2014)። የካቲት 15 ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “እስከዚህ ሰአት ድረስ ምንም አይነት ድርድር የለም” ብለዋል። በመቀጠልም ቀደም ሲል ድርድር አለመኖሩ “ከትህነግ/ህወሃት ጋር የመወያየት እድል ግን የለም ማለት አይደለም” ብለዋል (ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 15, 2014)። የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ለድርድር ሊዘጋጅ እንደሚችል ሌላው ማሳያ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በመጋቢት 2014 ባካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ግጭቱን ለመፍታት “አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ” እንደሚጠቀም መግለጹ ነው (ቪኦኤ አማርኛ፣ መጋቢት 4, 2014)።
ምንም እንኳን በሁለቱ ወገኖች መካከል ምንም አይነት ይፋዊ ድርድር ባይኖርም በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ለጊዜው አንፃራዊ መረጋጋት እንዲፈጠር የተካሄደው ‘ሸትል’ ዲፕሎማሲ ትልቅ ሚና የተጫወተ ይመስላል። በአፋር ክልል ውጊያዎች እየተካሄዱ ቢሆንም የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ ተሳትፎ እና ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር ሃይል በትህነግ/ህወሃት ኢላማ ላይ የሚያደርሰው የአየር ድብደባ ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ድረስ ባለው ወቅት ቀንሷል። በ’ሸትል’ ዲፕሎማሲ ውስጥ ሶስተኛ ወገን ወይም ዲፕሎማት በቀጥታ መነጋገር ወይም በድርድር ጠረጴዛ ላይ ለመቀመጥ በማይችሉ ወገኖች መካከል ስምምነት ለመፍጠር ይሞክራሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታ ትህነግ/ህወሃት በ‹‹አሸባሪ›› ድርጅትነት መፈረጁ የተመረጡት ባለሥልጣናት ቀጥተኛ ውይይት ማድረኝ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የአፍሪካ ህብረት፣ ተመድ፣ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ አካላት በ2013 እና 2014 ወኪሎቻቸውን ልከዋል (ቪኦኤ፣ ጥቅምት 29, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥር 7, 2014)። የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ከትህነግ/ህወሃት፣ ፌዴራል መንግሥትና፣ የክልል መንግሥታት ጋር ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በማሰብ ተወያይተዋል። እንደሳቸው ከሆነ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የሰላም ድርድር ቅድመ ሁኔታዎችን ዘርዝረዋል (አፍሪካ ህብረት፣ ጥር 5, 2014፤ በተጨማሩም ተመድ፣ ጥር 11, 2014 ይመልከቱ)። ይህም ሆኖ ግን ሁለቱም ወገኖች “ለድርድር የማይቀርቡ” በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ጦርነቱን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ባለፈው ወር የትህነግ/ህወሃት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በትህነግ/ህወሃት በኩል ለድርድር የማይቀርቡት ጉዳዮችን ዘርዝረው ነበር (ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 11, 2014፤ ቢቢሲ፣ ጥር 27, 2014፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ የካቲት 12, 2014)። እነዚህ ጉዳዮች ከትግራይ ያልሆኑ ሃይሎች ማለትም የአማራ ክልል እና የኤርትራ ሃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት፣ ትግራይን ለመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ማድረግ፣ የትግራይ ታጣቂ ሃይሎች ባሉበት መቀጠል፣ እና በትግራይ ክልል ውድመት ያደረሱትን አካላት ለፍርድ ማቅረብን ይጨምራሉ። ይህ ዝርዝር ከዚህ ቀደም በሰኔ 25, 2013 ላይ ከተለቀቀው የሰላም ስምምነት ቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር አጠር ያለ ነው (ስለ ከዚህ በፊቱ ቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013 ይመልከቱ)።
በፌዴራል መንግስቱ የድጋፍ አወቃቀር መሠረት በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ውስብስብ በሆኑ ነገሮች ምክንያት የፌዴራል መንግስቱም የማይደራደርባቸው ነጥቦች ጋር እየታገለ ነው። ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት እንቅስቃሴውን “የህግ የማስከበር ተልዕኮ” ሲል የሰየመው ሲሆን አላማውም በግጭቱ መጀመሪያ ላይ በትግራይ ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ማዕከል ላይ ለተፈፀመው ጥቃት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሆነ አሳውቋል (ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ጥቅምት 29, 2013)። ነገር ግን ብዙዎች አብይ ይህንን አላማ ለሰላማዊ መፍትሄ ሲባል ለመተው ፍቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ያምናሉ። ታህሳስ 29, 2014 ላይ መንግስት በግጭቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት ተይዘው ከነበሩት የትህነግ/ህወሃት መስራች አባል የነበሩትን ስብሃት ነጋ ጨምሮ ስድስት ከፍትኛ የትህነግ/ህወሃት መሪዎችን ከእስር ፈቷል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ታህሳስ 29, 2014)። ይህ እነዚህ ግለሰቦች ተጠያቂ ሆነው ማየት የሚፈልጉ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች – የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን)፣ እና እናት ፓርቲ – የትህነግ/ህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑ “ለኢትዮጵያውያን ያለ ንቀት ማሳያ” እና “ትህነግ/ህወሃትን በአሸባሪነት የፈረጀውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ የሚጻረር” በመሆኑ መንግሥት ውሳኔውን በመሻር ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባ አስታውቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 2, 2014)። በዚህ ምክንያት ህዝቡ ለመንግስት ያለው ድጋፍ ቀንሷል። ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ውሳኔ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ጥቅም እና ብሔራዊ ጥቅም እንደሚደግፍ እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተሟግተዋል (ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ጥር 1, 2014፤ ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ጥር 9, 2014)።
ሌላው የፌደራል መንግስትን እየተፈታተነ ያለው በምዕራብ ትግራይ ዞን የወልቃይት፣ ሁመራ፣ እና ፀገዴ አካባቢዎች ጉዳይ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ለአስርተ አመታት የአማራ ክልል አካል ለመሆን ፈልገዋል (ፎሪን ፖሊሲ፣ ሚያዚያ 20, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሃምሌ 1, 2013)። ከ1980ዎቹ ጀምሮ የትግራይ ክልል አካል ሆነው አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩት የትህነግ/ህወሃት መሪዎች የአስተዳደር ለውጥ ጥያቄዎችን አልተቀበሉም እንዲሁም የፖለቲካ አመራር የለውጥ ጥሪዎችን በኃይል አጨናግፈዋል። በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በጀመረ ሰሞን የአማራ ክልል ሃይሎች ፍጥነት እነዚህን አካባቢዎች በወታደራዊ ቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ለአማራ ክልል መንግስት ታማኝ የሆነ አስተዳደር መስርተዋል። በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ትግራይ ዞን የሚኖሩ አማራዎች “በትክክለኛው” ቦታቸው እየኖሩ እንደሆነ አጥብቀው ይናገራሉ (ብሎምበርግ፣ መጋቢት 7, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሃምሌ 1, 2013)። በምዕራብ ትግራይ ዞን የትግራይ እና አማራ ተወላጆች የሚኖሩ ሲሆን በጦርነቱ እጅግ የከፋ መፈናቀልና ጥቃቶች የደረሱበት ቦታ ነው። ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች፣ የፋኖ ታጣቂዎች፣ እና የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እጃቸው አለበት (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ህዳር 15, 2013)። ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያለው የሳምሪ ቡድን በማይካድራ ቢያንስ 600 ሰዎችን በመግደል ተከሷል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ህዳር 15, 2013፤ ሮይተርስ፣ ግንቦት 30, 2013)። ከአማራ ክልል ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖችም የትግራይ ተወላጆችን ከዞኑ በግድ በማስወጣት ተከሰዋል (ኤፒ ኒውስ፣ መጋቢት 29, 2013፤ ሮይተርስ፣ ግንቦት 30, 2013)። ከለፈው ታሪኩ እና ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ከነበረ ግጭት ጥቃት አንፃር አብዛኞቹ የአማራ ብሔርተኛ ማህበራት የምዕራብ ትግራይ ዞንን ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ አድርገው ይመለከቱታል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የካቲት 19, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 21, 2014)።
ከምዕራብ ትግራይ ዞን ጋር ጥልቅ ትስስር ያላቸው የአማራ ብሔርተኛ ቡድኖች እነዚህ አካባቢዎች በትግራይ ክልል ስር ልዩ ዞን ከሚሆኑ ወይም ህዝበ-ውሳኔ ከሚካሄድ ይልቅ እነዚህ አካባቢዎች በአማራ ክልል ስር እንዲዋሃዱ አጥብቀው ይጠይቃሉ (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የካቲት 19, 2014)። ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 በነበረው ወቅት, “የወልቃይት ፀገዴ-ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ” ሆኖ የተሾመው ለእነዚህ አካባቢዎች ትክክለኛ አስተዳደር የሚሆን በጀት እንዲለቀቅላቸው ለፌዴራል መንግስቱ ጥያቄ አቅርበዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የካቲት 13, 2014)። መንግስት እነዚህን አካባቢዎች በትግራይ ክልል እንዲተዳደሩ ለማድረግ ከወሰነ በዚህ ውሳኔ ላይ የትጥቅ ተቃውሞዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በተመሳሳይ በደቡብ ትግራይ ዞን የሚኖሩ ራያዎችም በአማራ ክልል ሥር መተዳደር ይፈልጋሉ (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የካቲት 24, 2014)። መንግስት በተመሳሳይ ጊዜ ለእነዚህን ጥያቄዎች እንዴት መልስ እንደሚሰጥ እና ከትህነግ/ህወሃት ጋር ለድርድር እንደሚቀመጥ ግልፅ አይደለም። ባለፈው ወር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እነዚህን አካባቢዎች በተመለከተ መንግስት እንደማይደራደር ጠቁመዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 21, 2014)።
የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል መውጣቱም ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። በአሁኑ ወቅት በመረጃ እጦት ምክንያት የኤርትራ ሃይሎች የትኞቹን አካባቢዎች በቁጥጥራቸው ስር እንዳደረጉ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን አንዳንድ መረጃዎች የሚያመለክቱት የኤርትራ ወታደሮች አወዛጋቢውን የድንበር ከተማ ባድመን መቆጣጠራቸውን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ባድመን ለኤርትራ ያደረገውን የ1994 የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ሰኔ 2010 ላይ ወስኗል (ዘ ዋሺንግተን ፖስት፣ ግንቦት 28, 2014)። ትህነግ/ህወሓት የኤርትራ ሃይሎች ከግጭቱ በፊት ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ያቀረበው ጥሪ የፌዴራል መንግስት የኮሚሽኑን ውጤት ለማክበር የወሰደውን ውሳኔ ችላ ያለ ነው።
የትግራይ ህዝብ ለመገንጠል ህዝበ ውሳኔ የማድረግ መብት አለው። በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (1) መሠረት “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” (የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት፣ 1987)። ሆኖም ለመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ በሁለት ምክንያቶች የተወሳሰበ ነው። አንደኛ የፌዴራል መንግስቱ የትህነግ/ህወሃትን መንግስት ህጋዊ ነው ብሎ ስለማይቀበለው የትግራይ ክልል ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ በህግ የተመረጠ ህግ አውጪ የለውም። በህገ መንግስቱ መሰረት የመገንጠል ጥያቄው በሚመለከተው የክልሉ የህግ አውጪ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ መጽደቅ አለበት (የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት፣ አንቀጽ 3919(4); በተጨማሪም የትግራይን መገንጠል በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከህዳር 4, 2014 እስከ ህዳር 10, 2014 ይመልከቱ)። የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ከፌዴራል መንግስት እውቅና ውጪ በጷጉሜ 2012 ላይ ክልላዊ ምርጫ አካሂደዋል። በሕገ መንግሥቱና በሌሎች የምርጫ ሕጎች መሠረት የፌዴራልና የክልል ምርጫዎችን የማካሄድ ሥልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው (የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት፣ 1987፣ አንቀጽ 102 (1)፤ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ህግ ቁጥር 1133/2011፣ አንቀጽ 7(1) ይመልከቱ)። ሁለተኛ የትግራይ ክልል ውስብስብ ተፈጥሮ እና የደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ ዞኖች ይካተቱ ወይም አይካተቱ የሚለው ጉዳይም አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዮች እና በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉትን የተወሳሰቡ ግጭቶችን ከግምት በማስገባት በትህነግ/ህወሃት እና በፌዴራል መንግስት መካከል የሚደረግ ማንኛውም ይፋዊ ድርድር ላይኖር ይችላል። የተኩስ አቁም ስምምነት በለመኖሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ እንደገና የመቀጠል እድሉ ሰፊ ሲሆን በተፋላሚ ወገኖች እና በግጭቱ አካባቢ በሚኖሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ አደገኛ የሆነ መዘዝ ያስከትላል።