ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መጋቢት 30, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,827
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,604
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,110
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2014 እስከ መጋቢት 30, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 17
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 91
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –23
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ሃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መካከል የሚካሄዱ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን ባለፈው ሳምንት 10 ውግያዎች መከሰታቸው ተዘግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኦነግ-ሸኔ ላይ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን አዲስ የጋራ “ኦፕሬሽን” መጀመሩን አስታውቋል (ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 1, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 3, 2014)። መጋቢት 24 እና 25 ላይ ኦነግ-ሸኔ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ አቅራቢያ ኢትዮጵያን ከኬንያ በሚያገናኘው አውራ ጎዳና ላይ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል። መጋቢት 28 እና 29 ላይ ሁለቱ ቡድኖች በምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬ ወረዳ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ እንዲሁም ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ውስጥ ተዋግተዋል። ኦነግ-ሸኔ በደገም ወረዳ 45 የመንግስት ጦር አባላትን መግደሉን ተናግሯል (ኦኤምኤን፣ መጋቢት 30, 2014)። ይህ በገለልተኛ ውገን አልተረጋገጠም። መጋቢት 30 ላይ እነዚህ ቡድኖች በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በወንጪ ወረዳ ቺቱ ቀበሌ እና አመያ ወረዳ ዳሌ ቀበሌ ላይ ተዋግተዋል።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካላት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። መጋቢት 24 ላይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ በዲጋሉ የገጠር መንደር የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አራት ሰዎችን ገድለው የበርካታ ገበሬዎችን ቤቶች አቃጥለዋል። በተመሳሳይ ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ወለጋ ዞን ጂማ አርጆ በተባለው ቦታ የጅማ አርጆ አባ ገዳዎች ሊቀመንበርን ከመኖሪያ ቤታቸው አፍነው ከወሰዱ በኋላ ገድለዋቸዋል። መጋቢት 26 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ ወረዳ ቢሌ ማሊማ ቀበሌ በዳሪሙ እና አቦሮ ማረሚያ ቤቶች ታስረው የነበሩ ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። ሟቾቹ የታሰሩት በኦነግ-ሸኔ አባልነት ተጠርጥረው ነበር። በማግስቱ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጅማ ገነቴ ወረዳ አዲለቃ ቱሉቻቢ በተባለ ቦታ ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ባልታወቀ ምክንያት ተኩሰው ገድለዋል። መጋቢት 27 ላይ በምስራቅ ባሌ ዞን ለጌ ሂዳ ወረዳ የቤልቱ ከተማ ነዋሪዎች “በከተማቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ” ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ተኩስ በመክፈት እና ተቃዋሚዎችን በመምታት ሰልፉን በትኗል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተቃዋሚዎች የቆሰሉ ሲሆን ሰልፉን አዘጋጅተዋል የተባሉ ከ30 በላይ ሰዎች ደግሞ ታስረዋል።
በተጨማሪም መጋቢት 25 ላይ በሲዳማ ክልል ጭሪ ወረዳ ሀሌላ እና ሱቻ ቀበሌዎች እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻምበል እና ወሮ ቀበሌዎች በኦሮሞ እና በሲዳማ ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት አምስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 15 ቆስለዋል ። ግጭቱ የተፈጠረው ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በሲዳማ ክልል ጭሪ ወረዳ ሃሌላ ቀበሌ የአካባቢውን የሲዳማ ሽማግሌ ከገደለ በኋላ ነው።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ሚኒዮ እና ድሬ ቀበሌዎች ኦነግ-ሸኔ ስምንት የአንድ ቤተሰብ አባላትን ገድሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናትን አፍኖ ወስዷል እንዲሁም ቤቶች አቃጥሏል፣ ዘርፏል። በተጨማሪም የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ 1 ወረዳ ተምበራ ኪዋ መንደር ሁለት ወንድማማቾችን ጨምሮ አራት የወልቃይት ተወላጆችን በእርሻ ላይ ሳሉ በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። መጋቢት 24 ላይ ስድስት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ ውስጥ የሚገኝ ኤርትራዊ ስደተኞች ወደሚገኙበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያ በመግባት በስደተኞች ላይ ጥይት ተኩሰው ስምንት ሰዎችን አቁስለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሚያዚያ 2, 2014)። የጥቃቱ ምክንያት አልታወቀም።
ባለፈው ሳምንት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሀይማኖት እና ከአስተዳደር እርከኖች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በተመለከተ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል። መጋቢት 25 ላይ በኦሮሚያ ፊንፊኔ ልዩ ዞን አቃቂ ወረዳ ቆራ በተባለ ሰፈራ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ እንደሆኑ የገለጹ ወጣቶች የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን (የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን) “በድምፅ ብክለት” እና የአምልኮ ቦታ ባለቤትነት ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት መስኮቶችን እና የቤት እቃዎችን ሰብረው የእምነቱን ተከታዮች ላይ ጥቃት አድርሰውባቸዋል። ሁኔታውን ለማረጋጋት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጣልቃ ገብቷል። በግርግሩ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል። በአቃቂ ወረዳ ገላን ከተማም በአካባቢው ባለስልጣናት እና በገላን ከተማ ስር በሚተዳደረው በጨፌጡማ ቀበሌ ሀይማኖታዊ ቅርስ አገኘን በሚሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መካከል የተፈጠረ አለመግባባትን ተከትሎ ውጥረት ነግሷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ መጋቢት 30, 2014)። የአስተዳደሩ ባለስልጣናት እንዳሉት ቦታው ለመንግስት ፕሮጀክት የተከለለ ነው። ነገር ግን ቡድኑ የአካባቢው ባለስልጣናት አካባቢውን መጠቀም እንዲችሉ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል። የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ቡድኑን ቅርሶቹን በአቅራቢያው ወደሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዲወስድ ቢጠይቅም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አሁንም ቅርሶ የተገኙበትን ቦታ እንደያዙ ናቸው። በአዲስ አበባ ሙስሊም ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ጸሎት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳያደርጉ በመከልከላቸው መጋቢት 30 ላይ “መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባቱን” በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መጋቢት 30, 2014)። ሚያዚያ 4 ላይ ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጭ የቀትርን ሰላት እንዲሰግዱ ፈቃድ መሰጠቱን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ወጥተዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሚያዚያ 4, 2014)።
መጋቢት 28, 2014 ላይ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በኦሞ ዞን ኮንታ ወረዳ የዞን አስተዳደር ለመመስረት የጠየቁ የአሪ ብሄረሰብ አባላት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር አንዳንድ ቤቶችን አቃጥለዋል። በአደጋው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ቆስለዋል። አንዳንዶች የግጭቱ ምክንያት የኦሞ ዞን ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ስብሰባ የአሪ ብሄረሰብ ጥያቄዎችን ለውይይት ባለማቅረቡ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ሰጥተዋል። የዞኑ አስተዳደር ኃላፊዎች ለዚህ ስህተት ይቅርታ ጠይቀው ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት በመሞከር ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት አድርገዋል (ቲክቫህ-ቤተሰብ፣ ሚያዚያ 2, 2014)። ሆኖም ግጭቱ በሳምንቱ መጨረሻ በጂንካ፣ ቶልታ እና ማይፀር ከተሞች እና አካባቢ ቀጥሏል።3 እነዚህ ኩነቶች በአክሌድ አሰራር መሰረት ተመዝግበው በሚቀጥለው ሳምንት የመረጃ ቋት ውስጥ ይካተታሉ። በዚህም ምክንያት ሚያዚያ 2 ላይ የሰዓት እላፊ የታወጀ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ ሁከቱን እንዲቆጣጠሩ ተጠርተዋል (ብስራት ሬዲዮ፣ ሚያዚያ 3, 2014)። አራት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ከ130 በላይ ሰዎች በግጭቱ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል (ቲክቫህ-ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 3, 2014)። መጋቢት 29 ላይ ከጉራጌ ዞን የተውጣጡ የማረቆ ብሄረሰብ አባላት በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ የማረቆ ወረዳ ከጉራጌ ዞን ተነጥሎ ልዩ ወረዳ ተብሎ እንዲታወቅ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ማረቆና መስቃን ወረዳን የሚያዋስኑ ዘጠኝ ቀበሌዎች እንዲካለሉም ጠይቀዋል። ቀደም ሲል በእነዚህ ሁለት ወረዳዎች በድንበር ውዝግብ ምክንያት ከፍተኛ ግጭቶች ሲከሰቱ የነበረ ሲሆን አለመግባባቶችን ለመፍታት የባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል (ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 4, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የምዕራብ ትግራይ ዞን፡ ለሰላም እንቅፋት ነው?
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግጭት ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት ከሆኑት በጣም አስቸጋሪ ጉዳዮች አንዱ የምዕራብ ትግራይ ዞን ሁኔታ ነው። በዞኑ ውስጥ ለአስርት አመታት በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) አመራር ስር የኖሩ አማራዎች በትግራይ ተወላጅ አመራሮች የሚደርስባቸውን መድሎ እና ከባድ እንግልት በማማረር በራሳቸው ማህበረሰብ ለመተዳደር ሲጠይቁ ቆይተዋል። በትህነግ/ህወሃት እና በመንግስት መካከል ጥቅምት 2013 ላይ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት እንኳን የአካባቢው ‘ባለቤትነት’ ለረጅም ጊዜ ሲያከራክር የነበረ ሲሆን በምዕራብ ትግራይ ውስጥ ብሄር ተኮር ጥቃት እንዳለ በተደጋጋሚ ይነገር ነበር።
ግጭቱ በ2013 በተቀሰቀሰበት ወቅት ከአማራ ክልል የመጡ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች ምዕራብ ትግራይን በፍጥነት በመቆጣጠር አካባቢውን የአማራ ክልል አካል አድርጎ የሚያስተዳድር ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቋሙ። በአገዛዙ ከትህነግ/ህወሃት ጋር አብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ከፍተኛ አድሎ ተፈጽሞባቸዋል (የምዕራብ ትግራይ ዞን ውስጥ ያለውን ግጭት በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦን የትግራይ ግጭት ገጽ) ይመልከቱ)።
ባለፈው ሳምንት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ ዞን “በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች” ያሉትን በማውገዝ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። በዘገባው ድርጅቶቹ ወደ 400 ከሚጠጉ ሰዎች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ በመመሰረት ጦርነቱ በተጀመረ ጊዜ (በጥቅምት 2013 ላይ)፣ በቀጣዮቹ ሰባት ወራት (ከጥቅምት 2013 እስከ ሰኔ 2013)፣ እንዲሁም ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 በነበረው ወቅት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ዘርዝረዋል (አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ መጋቢት 27, 2014)። ግኝቶቹ የአሜሪካ መንግስት ቀደም ሲል የአማራ ሃይሎች በምዕራብ ትግራይ ዞን “ስልታዊ የዘር ማጽዳት ዘመቻ” አድርገዋል ሲል ያቀረበውን ውንጀላ አስተጋብቷል (ቪኦኤ፣ የካቲት 21, 2013)።
በትህነግ/ህወሃት የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግስት የጋራ ዘገባውን ውጤት ተቀብሎ ገለልተኛ ምርመራ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በተቋቋመው አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ እንዲካሄድ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስትን እንዲያስገድድ ጠይቋል (የትግራይ የውጪ ጉዳይ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 30, 2014)። የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ዘገባውን አውግዞ ውጤቱን “አድሏዊ” እና “እጅግ ያልተረጋገጡ ድምዳሜዎች የተደረሱበት” ሲል ገልጾታል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 3, 2014)። የኢትዮጵያ መንግስት ዘገባው “ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ” ወቀሳ እንዳደረገ እና አሳሳቢ የሆኑ ውስጣዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን የተመለከተበትን መንገድ ላይ ጥያቄ አቅርቧል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን አገልግሎት፣ መጋቢት 28, 2014)። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል/የሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ዘገባ የተለቀቀው በጎንደር ዩንቨርስቲ (በአማራ ክልል) ተመራማሪዎች ትህነግ/ህወሃት አካባቢውን በተቆጣጠረበት ወቅት ገድለዋቸዋል የተባሉ የአማራ ተወላጆች የጅምላ መቃብር መገኘቱን ላይ የተፃፈውን ሌላ ዘገባ ተከትሎ ነው። ዘገባው ትህነግ ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት በተባሉት የምዕራብ ትግራይ ዞን ባሉ አማራዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ሲል ይከሳል (አማራ ኢዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 25, 2014)።
የምዕራብ ትግራይ ዞን ፖለቲካ ሁኔታ በዞኑ ውስጥ በሁሉም ወገኖች የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ ያደርገዋል። ከተከዜ ወንዝ በስተምዕራብ ያለው የዞኑ ግዛት ለዘላቂ ሰላም “ትልቅ እሾህ የሆነ እንቅፋት” ይፈጥራል (አልጀዚራ፣ ሚያዚያ 4, 2014)። ለፌዴራል መንግስቱ በምዕራብ ትግራይ ዞን ላይ ከትህነግ/ህወሃት ጋር የሚደረግ ድርድር በአማራ ክልል የሚገኙ አጋሮቹን ሊያስከፋ ይችላል (በትግራይ ግጭት የድርድር አጀንዳዎችን ላይ ያለውን ፖለቲካዊ ውስብስብነት ለመረዳት ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014ን ይመልከቱ)። ይህ ጉዳይ በእርግጥም ለመንግስት በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ መንግስት ከትህነግ/ህወሃት ጋር በሚስጥር ድርድር ላይ ነበር የሚል ጭምጭምታ ያወጡ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል (የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን፣ መጋቢት 13, 2014)። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሃይሎች አሁንም ከተዳከመው ሁኔታቸው እያገገሙ ሲሆን ትህነግ/ህወሃትን ለመከላከል በአብዛኛው በአማራ ክልል ሃይሎች ላይ ተንተርሰዋል። ይህንን ድጋፍ ማጣት ለፌዴራል መንግስቱ እና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንድነት ከፍተኛ ጉዳት ይኖረዋል።
በትህነግ/ህወሃት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው የተኩስ አቁም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥም ሲቀጥል በምዕራብ ትግራይ ዞን ያሉ አከራካሪ ግዛቶች ጉዳይ ይፋዊ ድርድር ለማካሄድ እንዳይችሉ እንቅፋት ከሚፈጥሩ ጉዳዮች አንዱ ነው። ይህንን ጉዳይ መፍታት፣ በሁሉም ወገኖች ለተፈፀሙ በደሎች ምላሽ መስጠት እና በከፍተኛ ባለስልጣናትን እና በአካባቢው ሁከት የሚፈጥሩ ቡድኖችን የሚያሳትፍ ስምምነት ላይ መድረስን ይጠይቃል። ይህ ጉዳይ በአግባቡ እስኪፈታ ድረስ በአካባቢው ግጭት መቀጠሉ አይቀርም።