ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሚያዚያ 14, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,875
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,781
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,152
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከሚያዚያ 8, 2014 እስከ ሚያዚያ 14, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 25
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 95
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –5
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት ሚያዚያ 9 እና 10 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች የፋኖ እና የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ በዘምቦ፣ አዲስ አለም እና ነጌሶ ቀበሌዎች እንዲሁም በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ቀወት ላይ ውጊያዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በኦሮሚያ ልዩ ዞን በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ወሰን ኩርኩር፣ ሙጤ ፋጫ እና ጥቁሬ ዋዳዎ ላይ ውጊያዎች ነበሩ። ሳምንታዊ ትኩረታችን በእነዚህ ኩነቶች ላይ ያተኩራል። በተጨማሪም ሚያዚያ 12 ላይ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የተቀበረ የታንክ ቅምቡላ ፈንድቶ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ሰው አቁስሏል።
በኦሮሚያ ክልል በኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በምስራቅ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በጉጂ ዞኖች የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ሚያዚያ 11 እና 12 ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሌ እና ወለንጪቲ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ የቦሴት ወረዳ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል። በቦሌ ከተማ 12 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ህይወት ማለፉ የተገለፀ ሲሆን በቦሴት ወረዳ ግጭት በተከሰተባቸው ሌሎች አካባቢዎችም የደረሰው ጉዳት በውል አይታወቅም። ሚያዚያ 9 ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ሂዳቡ አቦቴ ወረዳ ኦነግ-ሸኔ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት አድርሶ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ገድሏል። ከአራት ቀናት በኋላ ሁለቱ ቡድኖች በሰሜን ሸዋ ዞን ጃርሶ ወረዳ ኦሴ እና ኩዩ ወረዳ ዳዬ ዊሊንጮ ላይ ተዋግተዋል። ኦነግ-ሸኔ በኦሴ ስምንት ወታደሮችን መግደሉን እና 15 ወታደሮችን ማቁሰሉን እንዲሁም በዳዬ ዊሊንጮ 15 ገድሎ 20 ማቁሰሉን አሳውቋል (ኦኤሜን፣ ሚያዚያ 15, 2014)። ይህ በገለልተኛ ወገን ሊረጋገጥ አልቻለም። ሚያዚያ 12 ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደ በረት ወረዳ ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ሲዋጉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በማግስቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡነ ግንደ በረት ወረዳ ዶጎማ ቂቢ ቀበሌ በኦነግ-ሸኔ ኢላማዎች ላይ ባደረገው በሰው አልባ አውሮፕላኖች የታገዘ የአየር ድብደባ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል። በጉጂ ዞን ጎራ ዶላ ወረዳ በሃርኬሎ ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግቷል። ቡድኑ 26 ወታደሮችን እንደገደለ እና 29 ወታደሮችን ማቁሰሉን ተናግሯል (ኦኤምኤን፣ ሚያዚያ 13, 2014)። ሆኖም ይህ በገለልተኛ ወገን ሊረጋገጥ አልቻለም።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች የተሳተፉባቸው ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ሚያዝያ 10 ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሴት ወረዳ ካዋ ገበያ ቀበሌ የፋኖ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ግለሰቦች አምቡላንስ አስቁመዋል። ሶስት የጤና ባለሙያዎችን እና ሹፌሩን ከመኪናው አውርደው ከደበደቡ በኋላ አምቡላንሱን አውድመዋል። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ቡርቃ ሶሬማ የአማራ የብሄረሰብ ታጣቂዎች እና የፋኖ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍተው የገበሬዎችን ቤት አቃጥለው፣ በርካታ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል እንዲሁም ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ገድለዋል (ኦቢኤን፣ ሚያዚያ 10, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል በኦነግ-ሸኔ ላይ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ተመዝግበዋል። ሚያዚያ 10 ላይ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በጊንዶ ከተማ የአመያ ወረዳ ነዋሪዎች ኦነግ-ሸኔ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ያደረሱትን ጥቃት አውግዘው ሰልፍ ወጥተዋል። በማግስቱ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢንጪኒ ከተማ የአዳ በርጋ ወረዳ ነዋሪዎች ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን እና አካባቢው በድጋሚ የተቀሰቀሱ ግጭቶች
በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን በኢትዮጵያ ውስጥ ተደጋጋሚ ሁከትና ብጥብጥ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። ከ2010 ጀምሮ በአካባቢው በርካታ ግጭቶች የተቀሰቀሱ ሲሆን ይህም መሰረተ ልማቶችን ወድሟል፣ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን አፈናቅሏል፣ እንዲሁም የሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። በA2 አውራ ጎዳና ላይ የሚገኝ ዋና ቦታ እንደመሆኑ አካባቢው በአማራ፣ ኦሮሞ እና አፋር ብሄረሰቦች የታሪክ ይገባኛል ጥያቄዎች ይነሳበታል። ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሱ ግጭቶች በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል (በቅርቡ ስለተከሰተው ግጭት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 1, 2014 እስከ ሚያዚያ 7, 2014 ይመልከቱ)።
የአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተመሰረተው በ1983 እና 1984 በተደረገው የሽግግር ወቅት መጀመሪያ ላይ ለኦሮምኛ ተናጋሪው ህዝብ የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው ኦነግ ላደረገው ጫና ምላሽ ነው (ሳራ ቫግሃን፣ 1995))። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በግዛቱ እና ግዛቱን በሚያስተዳድሩ በአማራ ክልል ስር ባሉ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በየጊዜው ለሚነሱ ግጭቶች መነሻ ሆነዋል። በተጨማሪም በኦሮሞ ብሄረሰብ እና በአፋር አርብቶ አደሮች መካከል በግጦሽ ምክንያት በየጊዜው ግጭት ይከሰታል።
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በድጋሚ ተቀስቅሷል። በኦሮሚያ ልዩ ዞን በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ወሰን ኩርኩር፣ ሙቴ ፋጫ እና ትኩሬ ዋዳዎ ላይ ግጭት ነበር። በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ ዘንቦ፣ አዲስ አለም እና ነጌሶ ቀበሌዎች እንዲሁም በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ቀወት ውስጥ ግጭት ተመዝግቧል። ማን እንደተሳታፈ እና ማን ግጭቱን እንደጀመረ የሚቃረኑ መረጃዎች ያሉ ሲሆን ዘገባዎች በእነዚህ ወረዳዎች በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ 20 ሰዎች መሞታቸውንና 48 ሰዎች መቁሰላቸውን ያመለክታሉ። በሰሜን ሸዋ ዞን 125 ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን ከ3,000 በላይ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል እንዲሆም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ከሶስት ቀበሌዎች ተፈናቅለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ሚያዚያ 13, 2014)።
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ዘምቦ ቀበሌ ሞላሌ መንደር በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረው የመሰረተ ልማት ውድመት ከፍተኛ ነው ። ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ከደሴ ከተማ የሚያገናኘው ዋና መንገድ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለቀናት ተዘግቷል። በሸዋ ሮቢት ከተማ በዋናው A2 አውራ ጎዳና ላይ የሚገኙ የህዝብ ተቋማት እና የንግድ ማዕከላትም ተዘግተዋል። የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ፌዴራል ፖሊስ ውጊያውን ለመቆጣጠር ገብተዋል። ግጭቱን ለመቆጣጠር በተደረገው ዘመቻ ቢያንስ ሁለት የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች አባላት በአንዱ ቡድን ተገድለዋል። በኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ መሠረት ግጭቱ የተቀሰቀሰው ኦነግ-ሸኔ በወረዳው አንድ አርሶ አደር ላይ ጥቃት በማድረስ ከገደለ በኋላ ነው። ይህ ክስ በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ውድቅ የተደረገ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎችን በወረዳው በሚገኙ እረኞች ላይ ጥይት ተኩሰዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሚያዚያ 13, 2014)። ከዚህ ቀደም በሚያዚያ ወር 2013 ውስጥ ኦነግ-ሸኔ እና የአካባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው አጣዬ ከተማ እና አካባቢው ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በአካባቢው በተደጋጋሚ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት አጣዬ ከተማ ሙሉ በሙሉ ወድማለች (በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች መካከል ስላለው ውጥረት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013 እና የኢፒኦን የግጭት ማብራሪያ ገጽ የከሚሴ ግጭት ገጽን ይመልከቱ)።
በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ዳግም ያገረሸው ግጭት በግዛት፣ ብሔራዊ አቅጣጫ እና የብሔረሰቦች የይገባኛል ጥያቄዎች የሚጣመሩበት በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ግጭቶች ማሳያ ነው። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በአካባቢው የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከአማራ ክልል የተወጣጡ ታጣቂዎች የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲፈርስ አጥብቀው እንደሚጠይቁ ያምናሉ (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 11, 2014)። ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል በተወጣጡ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ፉክክር በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ካሉ አደገኛ አዝማሚያዎች አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በህወሓት እና በፌዴራል መንግስት ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ቢቀንስም ሌሎች ትንንሽ ግጭቶች በመላ ሃገሪቷ ተቀስቅሰዋል። አብዛኛዎቹ ትንንሽ ግጭቶች ከግዛት እና ሃብት ጋር የተያያዙ ቢሆኑም ትልቅ የፖለቲካ ግጭቶችም ቦታ አላቸው። በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ኢትዮጵያውያን በተቋቋመው ብሄራዊ የውይይት ኮሚሽን በኩል ሀገራዊ አቅጣጫቸውን፣ የአስተዳደር ዘይቤያቸውን እና የውስጥ ድንበራቸውን ይወስናሉ። በአማራ ክልል ባለው ኦሮምያ ልዩ ዞን በመሳሰሉ ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች የፖለቲካ ክርክር ነጥቦች ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን ፍትሃዊ እና ግልፅ የውሳኔ አሰጣጥ እስካልተደረገ ድረስ ውጊያው እንደሚባባስ ይጠበቃል።