በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሰኔ 17, 2014 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 3,033
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 16,832
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,546
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሰኔ 11 እስከ 17, 2014 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 15
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 252
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 203
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ውስጥ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል መካከል ውጊያ ተመዝግቧል። በጥቁር እንጪኒ ወረዳ ድሬ ኢንጪኒ እና ቢሎ አብዪ ከተሞች፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ወንጂ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ሆሴ ቀበሌ በኦነግ–ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ ተመዝግቧል። በፊንፊኔ ልዩ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ደርባ ከተማ ኦነግ–ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ጋር ተዋግቷል። ሰኔ 15 አካባቢ የኦነግ–ሸኔ አባላት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ በጋሞ ጅባት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት አድርሰዋል። ቡድኑ አምስት ወታደሮችን መግደሉን እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ወታደሮችን ማቁሰሉን አሳውቋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ሂዳቡ አቦቴ ወረዳ ጨለንቆ በተባለው ቦታ ሰኔ 17 ቀን አማፂ ቡድኑ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር ተዋግቷል። ውጊያው የተከሰተው የኦነግ–ሸኔ አባላት በሰሜን ሸዋ ዞን ሂዳቡ አቦቴ ወረዳ ኤጅሬ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ወዘሚ መንደር ከጉንዶ መስቀል ወደ አዲስ አበባ ሰላማዊ ዜጎችን ሲያጓጉዙ የነበሩ ቢያንስ አራት አውቶብሶችን እና አንድ የጭነት መኪናን በማስቆም ወደ አልታወቀ ቦታ ወስደው 370 ሰዎችን ካፈኑ በኃላ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ሃይሎች ወደ አካባቢው ገብተው ከአማፂ ቡድኑ ጋር ተዋግተው 360 ታጋቾችን ማስለቀቅ ችለዋል። ሁለት ባለሀብቶችን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ግን አሁንም በቡድኑ ታግተው እንደሚገኙ ተነግሯል።
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ሳምንት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ሁለት ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ሰኔ 17 ቀን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጎሮ ወረዳ ጉራራ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ባልታወቀ ምክንያት ሶስት ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ ቀበሌ የተፈፀመው ሁለተኛው ጥቃት ከዚህ በታች በሚገኘው በሳምንታዊ ትኩረት ስር ተብራርቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ሃይሎችን ያሳተፉ በርካታ የውጊያ ኩነቶች በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ሰኔ 15 አካባቢ በትግራይ ክልል ደቡባዊ ትግራይ ዞን ራያ አላማጣ ወረዳ በዋጃ አካባቢ ትህነግ/ህወሓት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተዋግተዋል። በቅርቡ በአማራ ክልል የተደረገውን “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች አካባቢውን ለቀው ከወጡ በኋላ የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ሰኔ 1 ቀን አካባቢውን ተቆጣጥረው ነበር (ስለ “ህግ ማስከበር ዘመቻው” የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014 ይመልከቱ)። ሆኖም ሰኔ 3 ቀን የፋኖ አባላት ዳግም ወደ አካባቢው መግባት ሲጀምሩ የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ካለምንም ውጊያ አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል። በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች እና የፋኖ ሚሊሻዎች ተዋግተዋል። ሰኔ 15 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ በጀሮታ ቀበሌ የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ከተዋጉ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በዙሪያው ያሉትን አረንገቦ፣ አገዳ እና አዲሱ መንደሮችን ጨምሮ ቀበሌውን ተቆጣጥረዋል። በግጭቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሲሞቱ እና ሲቆስሉ ከ160 በላይ ሰዎች ደግሞ አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። የትህነግ/ህወሓት ሃይሎችም የሰላማዊ ሰዎችን ንብረቶች ዘርፈዋል። በተጨማሪም ሰኔ 15 እና 16 ሁለቱ ቡድኖች በሰሜን ወሎ ዞን በጊዳን ወረዳ ወትወት ቀበሌ ተዋግተዋል። ከሰኔ 16 እስከ 18 ድረስ በሰሜን ወሎ ዞን በቆቦ ወረዳ በስሚዛ ጊዮርጊስ፣ መቅነት ጋሪያ እና ጃን አሞራ ቀበሌዎች የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ አማራ እና ፋኖ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተው ብዙም ሳይቆይ እነዚህን ቀበሌዎች ተቆጣጥረዋል። ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል (አዲስ ማለዳ፣ ሰኔ 18፣ 2014)።
በተጨማሪም ሰኔ 15 ቀን የሱዳን ጦር ሃይል እና ማንነቱ ያልታወቀ የኢትዮጵያ ሃይል በአወዛጋቢው አል ፋሽጋ ክልል ውስጥ ከአል አሲራ በስተምስራቅ በሚገኘው አል ኩሬይሻ አካባቢ ተዋግተዋል። አንድ የሱዳን ጦር ሃይል አባል ሲቆሰል ሌሎች ሰባት ደግሞ የት እንዳሉ እንዳልታወቀ ተዘግቧል (ሱዳን ትሪቡን፣ ሰኔ 16, 2014)። ሰኔ 20 ቀን የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እነዚህን የሱዳን ጦር ሃይል ምርኮኞች እና አንድ ሲቪል ሰው ገድሏል ሲል ከሷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 20, 2014)። የኢትዮጵያ መንግስት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው እንደማይገኝ በመግለፅ ይህንን ክስ ውድቅ አድርገዋል (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሰኔ 20, 2014፣ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 21, 2014)።
ባለፈው ሳምንት ሰኔ 15 ቀን ትህነግ/ህወሓት በነዳጅ እጥረት ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ የከለከለ ሲሆን በአባላ (አፋር) በኩል ወደ መቀሌ በሚወስደው መንገድ ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች እርዳታውን ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ማድረሳቸውን ግን ቀጥለዋል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሰኔ 16,2014፣ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 15, 2014)። ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች በየቀኑ ወደ መቀሌ ይበሩ ነበር። የፌዴራል መንግስት “የነዳጅ እጥረት ወሬ ትህነግ/ህወሓት ሠራዊቱን ለሌላ ዙር ግጭት ለማንቀሳቀስ የሚጠቀምበት ድብቅ አጀንዳ ነው” ሲል የትህነግ/ህወሓትን የነዳጅ እጥረት ክስ ውድቅ አድርጏል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሰኔ 16, 2014)። ይሁን እንጂ ሰኔ 16 ቀን የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) ጋር ከተነጋገረ በኋላ በትግራይ ክልል ውስጥ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማከፋፈል እንዲረዳ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደ ክልሉ እንዲገባ ተስማምቷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 16 ቀን 2014)።
በጋምቤላ ክልል ሰኔ 12 ቀን በአካባቢው ‘መጤ’ የሚባሉት – ደገኞች – በጋምቤላ ከተማ ‘መጤ’ የሚባሉት ብሔር ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ግድያ በመቃወም ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ መንግስት ድምፃቸውን እንዲሰማ እና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ልዩ ሃይል በሰልፈኞቹ ላይ ተኩስ ከፍተዋል። የደረሰው ጉዳት አይታወቅም። ሰኔ 7 ቀን በኦነግ–ሸኔ፣ በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) እና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል በከተማዋ የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይል እንደሆኑ የሚገመቱ የጸጥታ ሃይሎች በጋምቤላ ከ10 ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆችን በጥይት መትተው መግደላቸው ተነግሯል (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 4 እስከ 10, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 ይመልከቱ)።
በመጨረሻም በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወምበራ ወረዳ ባህላዊ የሠላምና የዕርቅ ሥነ–ሥርዓት ተካሂዷል። በሥነ–ሥርዓቱ ላይ ከ11 ቀበሌዎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሰኔ 17, 2014)። የመተከል ዞን በኢትዮጵያ ውስጥ ተደጋጋሚ ግጭቶች ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦን የመተከል ግጭት ገፅ ይመልከቱ)። ከዚህም በተጨማሪ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች በቡርጂና በኦሮሞ ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ከኮንሶ፣ ጌዲዮ፣ ቦረና እና ገብረባል የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች እየጣሩ ነው። ግንቦት 27 ቀን በቡርጂ ልዩ ወረዳ የሶያማ ከተማ ገበያ ላይ የቡርጂ ብሔር ተወላጆች ከጉጂ ዞን የመጡ 10 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ደብድበው የገደሉ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል። ይህ ጥቃት የተፈፀመው አንድ የቡርጂ ብሔር ተወላጅ የት እንደሆነ ባልታወቀ ቀበሌ ውስጥ ከጉጂ ዞን በመጡ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ተገድሏል የሚል ወሬ ከተናፈሰ በኋላ ነው። ነገር ግን እንደ አካባቢው ባለሥልጣናት ከሆነ ይህ ግለሰብ የተገደለው በኦነግ–ሸኔ ነው (ስለዚህ ኩነት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 ይመልከቱ)። በዚህ በኦሮሞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀመው ግድያ ተሳትፈዋል የተባሉ 70 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቡርጂ ልዩ ወረዳ ባለስልጣናት ገልፀዋል (ቪኦኤ አማርኛ፤ ሰኔ 16, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የቶሌ ግድያ
ሰኔ 11 ቀን በምዕራብ ወለጋ ዞን በጊምቢ ወረዳ ጊምቢ እና ነቀምቴ ከተማዎችን በሚያገናኘው A4 አውራ ጎዳና ላይ ያለው ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በጉቱ፣ ጨርቆሳ፣ ስልሳው፣ በገነ፣ ጫካው ሰፈር እና ሃያው አካባቢዎች የኦነግ–ሽኔ አባላት ከ200 ያላነሱ አብዛኛዎቹ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን ተኩሰው በመግደል ተከሰዋል (ኤፒ ኒውስ፣ ሰኔ 12, 2014)። በቅርቡ በወጡ ዘገባዎች መሰረት ጥቃቱ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ቦሎ ጂንጋፎይ (ምዥጋ) ወረዳ ስር በሚገኘው ሴ ቀበሌም ተዛምቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 20, 2014)። በዚህ ምክንያት ከ3,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው በአርጆ ጉደዱ እና በኤፍሬም ከተሞች ተጠልለው ይገኛሉ (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 18, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 13, 2014)። የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ለአማጺ ቡድኑ መረጃ በመስጠት እና ጥቃቱን እንዲፈጽም ቡድኑን በመምራት የተጠረጠሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 18, 2014)።
አንዳንድ ዘገባዎች የሟቾች ቁጥር በአጠቃላይ ከ500 በላይ ሊሆን እንደሚችል እና ከተጎጂዎቹ መካከል ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመንግስት ታጣቂዎች እና በኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት “በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት” መድረሱን ጠቁሞ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመከላከል መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቋል (ኢሰመኮ፣ ሰኔ 12, 2014)። የኦነግ–ሸኔ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በዚህ ጥቃት የኦነግ–ሸኔ ሃይሎችን ተሳትፎ ውድቅ በማድረግ “ገለልተኛ ምርመራ” እንዲደረግ ጠይቋል (ኦኤልኤ የህዝብ ግንኙነት፣ ሰኔ 13, 2014)። በመንግስት ላይም ክስ ቀርቦበታል። የአማራ ማህበር በሰሜን አሜሪካ በቅርቡ የተፈፀሙት ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ መፈጸማቸውን ገልጿል (አልጀዚራ፣ ሰኔ 18, 2014)።
ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ገና በምርመራ ላይ ቢሆንም፣ ግድያ የተፈፀመው በመንግስት እና በኦነግ–ሸኔ ሃይሎች መካከል ተጠናክሮ ባለው ጦርነት እንዲሁም ድርጊቱ በተፈፀመበት ቀን ጭምር በሁለቱ ወገኖች መካከል በነበረ ጦርነት ወቅት መሆኑን ልብ ማድረግ የሚገባው ነው (ኤፒ ኒውስ፣ ሰኔ 12, 2014)። ከቶሌ ጥቃት ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የኦነግ–ሸኔ ሃይሎች በጋምቤላ እና ደምቢ ዶሎ ከተሞች ላይ ያደረሱትን ጥቃቶች ጨምሮ የተቀናጀ ጥንካሬያቸውን ለማሳየት በጊምቢ ከተማ እና አካባቢዋ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ነበር (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 7, 2014)። እነዚህ በዋና ዋና የከተማ ማዕከላት ላይ ቡድኑ ያደረሳቸው የመጀመሪያዎቹ ትልልቅ ጥቃቶች ናቸው። በመንግስት እና በኦነግ–ሸኔ ሃይሎች መካከል ጠንከር ያለ ውጊያም ከቶሌ ጥቃት ጥቂት ቀደም ብሎ ተዘግቧል (ኤፒ ኒውስ፣ ሰኔ 18, 2014)። ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ባሳተመው ንግግር የኦነግ–ሸኔ ዋና አዛዥ ጃል መሮ በሚያዝያ ወር የተካሄደውን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ መንግስት ኦነግ–ሸኔ ተደምሰሷል ሲል ያለውን ለማስተባበል በነዚህ ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን አመላክቷል (ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ ሰኔ 17, 2014፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዝያ 1, 2014)።
ባለፉት ሁለት አመታት በኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰብ አባላት መካከል የሚነሱ ግጭቶች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች እየጨመሩ መጥተዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይት፣ ግንቦት 24, 2014)። በኦነግ–ሸኔ እና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ጦርነት የጸጥታው ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችም እየጨመሩ መጥተዋል። አክሌድ በኦሮሚያ ክልል ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ወደ 50 የሚጠጉ ጥቃቶችን ቢያንስ 630 የሚሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሞቱበትን ኩነቶችን መዝግቧል። ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ውስጥ የሚገኝ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሰፈራዎችን ኦነግ–ሸኔ አጥቅቶ ቢያንስ 150 የሚሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ህይወት ማለፉ ተነግሯል። መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን በባቦ ጋምቤላ ወረዳ ቦኔ ቀበሌ አማራዎች እንደሆኑ የሚገመቱ 28 ሰላማዊ ሰዎች ኦነግ–ሸኔ እንደሆኑ በተገመቱ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ስለተፈጸመው የጅምላ ግድያ የተለያዩ አካላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች የተፈጸሙትን ግድያዎች አውግዘዋል (ፌስቡክ፣ አብይ አህመድ አሊ፣ ሰኔ 13, 2014)። መንግስት በክልል እና በፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች በኦነግ–ሸኔ ላይ የሚወሰደው የተቀናጀ ዘመቻ እንደሚቀጥል አረጋግጧል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሰኔ 13, ቀን 2014)። በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ኦኤችሲአር) የኢትዮጵያ መንግስት “በምዕራብ ወለጋ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ” እንዲያደርግ አሳስቧል (ኦኤችሲአር፣ ሰኔ 16, 2014)። በተጨማሪም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ኦነግ–ሸኔ ያደረሰውን ጥቃት እና በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን ሰብአዊ ፍላጎት ለማጣራት ሁለት ቡድኖችን አቋቁሟል (የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 16, 2014)።
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ግድያውን አውግዘዋል (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ሰኔ 13, 2014፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ ሰኔ 13, 2014)። ሰኔ 14 ቀን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወለጋና በሌሎችም አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው ግድያ ላይ ለመወያየት የእለቱ አጀንዳ ላይ እንዲካተት ያቀረቡትን ጥያቄ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አልቀበልም በማለቱ ፓርላማውን ረግጥው ወጥተዋል (ፌስቡክ፣ ደሳለኝ ጫኔ፣ ሰኔ 14, 2014)። ሌሎች ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኦነግ ፓርቲ እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ክስተቱ በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር–ኦነግ/አባዎ፣ ሰኔ 15, 2014፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ– ኦፌኮ፣ ሰኔ 15, 2014)። ሰኔ 17 ቀን በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቶሌ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በማውገዝ ተቃውሞ ሰልፍ አደርገዋል። በዚህ ጥቃት ምክንያት በሀገሪቱ ያለው ውጥረት ጨምሯል፣ እንዲሁም በታሪክ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በአማራ እና በኦሮሞ ማህበረሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ይባስ አሽቆልቁሏል።
ማስተካከያ፡- ቀደም ሲል የወጣው የዚህ ሳምንታዊ ቅጂ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገላል ወሃ በተባለው አካባቢ በሱዳን ታጣቂ ቡድን፣ በትህነግ/ህወሓት ደጋፊ ታጣቂዎች እና በአማራ ታጣቂዎች መካከል የነበረ የውጊያ ዘገባ ያካተተ ነበር። የተረጋገጠ መረጃ ባለመገኘቱ ምክንያት ይህ ኩነት ከዚህ ሪፖርት ላይ እንዲሁም ከአክሌድ የመረጃ ቋት ላይም ተሰርዟል።