በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 8, 20141 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 3,100
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 17,701
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 8,016
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከሐምሌ 2 እስከ 8, 20142በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ብዛት: 22
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 190
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የተዘገቡ የሟቾች ቁጥር: 33
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች እንደቀጠሉ ነው። ባለፈው ሳምንት አክሌድ በክልሉ ውስጥ አራት እንደዚህ ያሉ ኩነቶችን መዝግቧል። አብዛኛዎቹ ከህግ አግባብ ውጪ የተፈፀሙ ግድያዎች የተመዘገቡት በምስራቅ ወለጋ ዞን ነው። ሐምሌ 3 ቀን በምስራቅ ወለጋ ዞን በቢላ ስዮ ወረዳ ሃሮ ጉዲሳ ውስጥ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር መረጃ አጋርቷል በሚል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት አንድ ወጣት ተኩሰው መግደላቸው ተነግሯል። በተመሳሳይ ሐምሌ 5 ቀን በምስራቅ ወለጋ ዞን በሊሙ ወረዳ ሙካ ሮባ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ሚሊሻዎች ሰባት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል።ተጎጂዎቹ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተወንጅለው ነበር። በምስራቅ ወለጋ ዞን ሃሮ ሊሙ ወረዳ ባሪሶ ቀበሌ ውስጥ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ሐምሌ 6 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ የመንግስት ኃይሎች ሁለት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። በተጨማሪም ሐምሌ 6 አካባቢ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በካዋ ገበያ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁለት ወንድማማቾችን በተመሳሳይ ክስ በጥይት ተኩሰው ገድለዋል።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ሁለት ውጊያዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ሐምሌ 6 አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ውስጥ ባልታወቀ ቦታ በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ አድርጓል። የመንግስት ሃይሎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ታጣቂዎችን መግደላቸውን እና አምስት ኤኬኤም መሳሪያዎች፣ ሁለት የእጅ ቦምቦችን፣ 200 ጥይቶችን፣ 164 የብሬን ጥይቶችን፣ አራት የወገብ ቀበቶዎችን እና 12 የክላስተር ጥይቶችን መያዙን አስታውቋል። የፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በምስራቅ ሸዋ ዞን ባልታወቁ አራት ወረዳዎች ውስጥም በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማድረጋቸውም ተዘግቧል። የመንግስት ኃይሎች 129 የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን መግደላቸውን እና 17 የቡድኑን አባላት መማረካቸውን ተናግረዋል።
ኦነግ-ሸኔ በደቡብ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተከሰቱ ሌሎች ድርጊቶችም ተሳትፏል። ሐምሌ 6 ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት በቡርጂ ልዩ ወረዳ ዋለሜ ቀበሌ አራት አርሶ አደሮችን ገድለው አምስት አቁስለዋል። የታጠቀው ቡድን ወደ 50 የሚጠጉ የቀንድ ከብቶችንም መዝረፉ ተዘግቧል። ሆኖም አማፂ ቡድኑ ክሱን አስተባብሏል። በተመሳሳይ ዕለት የኦነግ-ሸኔ አባላት በአማሮ ልዩ ወረዳ ባልታወቀ ገጠራማ አካባቢ አንድ አርሶ አደር ገድለዋል ተብሏል። አማፂ ቡድኑ በዚህ ጥቃትም እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 8, 2014)።
በአማራ ክልል ባለፈው ሳምንት በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የመንግስት ኃይሎች ከኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። እነዚህ ኩነቶች በሳምንታዊ የትኩረት ክፍል ውስጥ በዝርዝር ተብራርተዋል። በተጨማሪም የቅማንት ብሄረሰብ ታጣቂዎች እና ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሐምሌ 2 ቀን በምዕራብ ጎንደር መተማ ወረዳ ሹመት መንዶቃ (ቦርኒ) መንደር ገብተው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ስድስት ሰዎችን ሲገደሉ አራት ሰዎችን አቁስለዋል። ታጣቂዎቹ ከ1,500 በላይ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈው የሰላማዊ ሰዎችን ንብረቶች አውድመዋል። ሐምሌ 5 ቀን በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ከተማ ማንነቱ ባልታወቀ ቡድን የተጣሉ ፈንጂዎች በቁራሌዎች ከተሰበሰቡ በኃላ ፈንጂዎች በገበያ ማሃል በመፈንዳታቸው 11 ሰላማዊ ሰዎች ቆስለዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ዳንጉራ ወረዳ በብርቱካን እና በሲሳይ መንደሮች የፋኖ ታጣቂዎች ሁለት የአገው ብሄረሰብ ተወላጆችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል ተብሏል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የክልሉ ፖሊስ ከጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) አባላት ጋር በካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ ደዴሳ ቀበሌ ተዋግተው ቀበሌውን ተቆጣጥረዋል። ከግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ጅምሮ ይህንን ቀበሌ እና ሌሎች በምዥጋ ወረዳ የሚገኙ አምስት ቀበሌዎችን ጉህዴን ተቆጣጥሮ ነበር። ሐምሌ 6 አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ኃይሎች በመተከል ዞን ደባጤ ወረዳ የጉህዴን አባል የሆነን ሰው ተኩሰው ገድለዋል። ይህ ሰው ወደ ከተማዋ የገባው ከመንግስት ጋር ለመደራደር የቀረበለትን ጥሪ ተከትሎ ነው። ባለፈው ሳምንት የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ፖሊስ በአሶሳ ከተማ የሰዓት እላፊ አዋጁን ጥሰዋል የተባሉ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል። የክልሉ መንግስት በሐምሌ 1 ቀን በከተማው የም|ሸት የሰዓት እላፊ አውጇል። የሰዓት እላፊው ከመታወጁ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በአሶሳ ከተማ ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን ጥቃት ለማድረስ እያቀደ መሆኑን ጠቁመው ነበር (ኢቢሲ፣ ሰኔ 30, 2014)።
በመጨረሻም ሐምሌ 2 ቀን በአፋር ክልል በአውሲ-ዞን 1 በአዳር ወረዳ ካሳ ጊታ አካባቢ ማንነቱ ባልታወቀ ቡድን የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ የአራት ታዳጊዎችን ህይወት ቀጥፏል። ባለፈው ወር በአውሲ-ዞን 1 ጭፍራ አካባቢ በደረሰ የተቀበረ ፈንጂ ፍንዳታ አንድ ህጻን ሲሞት ሌላ ሰው ቆስሏል። እነዚህ ፈንጂዎች በመንግስት እና ትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ኃይሎች መካከል ከ2013 እስከ ታህሳስ 2014 ድረስ በከካባቢው በነበረው ውጊያ የተተዉ የፈንጂ ቅሪቶች ሊሆኑ ይችላሉ።
ሳምንታዊ ትኩረት – ውጊያዎች በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በድጋሚ መቀስቀስ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች በድጋሚ ተቀስቅሰዋል። ከሐምሌ 3 እስከ 5 ድረስ የመንግስት ኃይሎች እና የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ በኤፈራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በርሀ ስላሴ፣ አርሶ አምቦ (ዘምቦ) እና ወይና ቀበሌዎች በኦሮሚያ ልዩ ዞን ጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ በጤ ቀበሌ ተዋግተዋል። የክልሉ ልዩ ኃይል እና የፌዴራል ኃይሎች ውጊያውን ለመቆጣጠር ወደ ስፍራው ተሰማርተዋል። ቢያንስ ስድስት ሰዎች እና 19 የፀጥታ ኃይል አባላት መሞታቸው ተነግሯል። በተጨማሪም ሐምሌ 7 ቀን በጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ በባቴ አርዳጋ ቀበሌ የፋኖ እና የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከኦሮሞ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በነዚህ ውጊያዎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። በአካባቢው መረጋጋት ለማምጣት የጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ መስተዳድር በሐምሌ 4 ቀን የምሽት የሰዓት እላፊ እና ሌሎች ገደቦችን አውጇል (የጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን፣ በሐምሌ 4, 2014) ።
የአካባቢው ነዋሪዎች ይህ እንደ አዲስ ላገረሸው ጦርነት መንስኤ የተለያየ ምክንያት ያቀርባሉ። የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እጃቸው እንዳለበት እና ውጊያውን አነሳስተዋል ሲሉ ይከሳሉ። በአንፃሩ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች የገበሬዎችን ከብቶች በሃይል ለመውሰድ ሞክረዋል ያሏቸውን የመንግስት ኃይሎች ተጠያቂ ያደርጋሉ (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 6, 2014)። ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ውጊያው የተቀሰቀሰው ከብቶች ወደ ታረሰ መሬት ከተለቀቁ በኋላ ነው። አንድ ዘገባ እንደገለጸው ውጊያው የተጀመረው ስድስት የታጠቁ የመንግስት የፀጥታ ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱ አንድ አርሶ አደርን ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ነው (ሪፖርተር፣ ሐምሌ 6, 2014)።
በዚህ አካባቢ የሚነሱ ውጊያዎች ብዙ ጊዜ በግዛትና በአስተዳደራዊ አለመግባባቶች ይከሰታሉ። በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን የፖለቲካ መሪዎች እንደ ልዩ ዞን ከተቋቋሙበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ዞኑ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች በነፃነት እራሳቸውን አስተዳድረዋል። በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት በአማራ ክልል ወሰን ውስጥ ቢወድቅም ዞኑ የሚገኙ የኦሮሞ ነዋሪዎች የሚተዳደሩት በልዩ ድንጋጌዎች ሲሆን ይህ ደግሞ ከአማራ ክልል ባለስልጣናት ጋር ቀጥተኛ ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። በርካታ አርብቶ አደር የሆኑት ኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በውሃ እና በግጦሽ መሬቶች ምክንያት በአካባቢው ከሚገኙ የአማራ እና የአፋር ተወላጆች ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ። የኦነግ-ሸኔ እጅ አለበት የተባለውም ጉዳዩን እንዲወሳሰብ ያደርገዋል። ቀደም ሲል ቡድኑ በአካባቢው ይንቀሳቀሳል የሚለውን ውንጀላ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና የቡድኑ ቃል አቀባይ ውድቅ ተደርገዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ መጋቢት 15, 2013)። በኋላ ላይ ይህ ማስተባበያ የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ወደ ደቡብ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሲገቡ፣ ድንገተኛ እና አጭር የነበረው “የጋራ ዘመቻ” በታወጀበት ወቅት ውድቅ ተደርጎ ነበር (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 22, 2013)። በዚህ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ታጣቂ ቡድኖች እና በኦነግ-ሸኔ አዛዦች መካከል ያለው ግንኙነት ከዚህ ቀደም በተሰጠው ማስተባበያ እና የቦታ እንቅስቃሴ እገዳ ምክንያት አጠራጣሪ ነው። አንዳንድ ታጣቂዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ትስስሮች ሊኖራቸው ቢችልም እነዚህ የኦሮሞ ቡድኖች እራሳቸውን እንደ ኦነግ-ሸኔ እና ለኦሮሞ ራስን በራስ የማስተዳደር እና ታሪካዊ መሬትን ለመቆጣጠር ካለው የፖለቲካዊ ዓላማው ጋር እራሳቸውን ሊያስተሳስሩ ይችላሉ (በዚህ አካባቢ ስለሚፈጠሩ ግጭቶች ለበለጠ መረጃ የኢፒኦን የከሚሴ ግጭት ገፅ ይመልከቱ)።